

January 5, 2025
ወደ 252 ገጣሚያንና ጸሐፍት ተወዳድረው በ1984 ዓ.ም. የፀደቀው በአሥር ስንኞችና በ45 ቃላት ተቀምሮ የቀረበው የዜግነት ክብር የሚለው የኢትዮጵያ ሕዝብ መዝሙር ስለኢትዮጵያዊነት ጥልቅ ሐሳብ መያዙን ገጣሚው ይናገራል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያዊነት ሰውነት ነው›› ሲል ይናገራል፡፡ ዛሬ በሥራ ላይ ያለውን የኢትዮጵያ ሕዝብ መዝሙር ግጥምን የጻፈው ደረጀ ይርጋ የዛሬ ስድስት ዓመት ከብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር ባደረገው ቃለመጠይቅ፡፡ ‹‹ኢትዮጵያዊ መልካም ነገሮችን የሚያደርግ ሰው ነው፤›› የሚለው ገጣሚው፣ መሠረተ ፅኑ ሰብዕናን ያልሻርን›› የሚለው የመዝሙሩ ስንኝ ከሁሉ በላይ ወሳኝና ኢትዮጵያዊነት በደንብ የተገለጸበት ቦታ እንደሆነ ይጠቁማል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያዊያን የፈለገ ብንጋጭ ብንጣላም ሆነ ምንም ነገር ቢፈጠር፣ ከሰብዕና በታች ወርደን አናውቅም፡፡ ዓድዋ ላይ ያ ሁሉ ሕዝብ ከእኛም ከጠላትም አለቀ፡፡ ነገር ግን በዓድዋ ተራሮች የወደቁ የጠላት ወታደሮች ከወገን ሰማዕታት ጋር በአንድ ጉድጓድ እንዲቀበሩ በማድረግ ለዓለም ኢትዮጵያዊያን የተጎናጸፍነውን የሰብዕናን ጥግ አሳየን፡፡››

በሊባኖስ ቤሩት የሃይማኖት ፖለቲካን መሠረት ያደረገ የእርስ በእርስ ጦርነት በጦፈበት እንዲሁም ሶማሊያ በተፈረካከሰችበት ወቅት፣ በኢትዮጵያ የደርግ መንግሥት ተገልብጦ ኢሕአዴግ የገባበት ወቅት መሆኑን የሚጠቁመው ጸሐፊው፣ አገሪቱ እንደ ሌሎች አገሮች እንዳትፈረካከስ በከባዱ ይሠጋ እንደነበር ያመለክታል፡፡ ‹‹ከዕለታት አንዱ ቀን ሁሉም ተገልብጦ ኢሕአዴግ ገባ፡፡ ነገር ግን የተፈጠረ ኮሽታ አልነበረም፡፡ ምን ሆኖ ነው ብዬ ወደ ፒያሳ አካባቢ ስሄድ፣ አዲስ መትረየስ የታጠቀ የደርግ ወታደር ቁጭ ብላ ለምትመዘግብ ሴት የኢሕአዴግ ታጋይ መሣሪያ ሲያስረክብ አየሁ፡፡ ወዲያውም ራበኝ ሲላት ውይ ብላ ተንሰፍስፋ እንጀራ ስታመጣለት ተመለከትኩ፡፡ ይህን መሰሉ ሁነት በሌላ አገር ቢሆን ሊከሰት የሚችል ነው ብዬም ጠየኩ፡፡ የፈለገ ጠላትነትና መገዳደል ቢኖር እንዲህ ያለውን ሰብዓዊነት የተሞላበት መተዛዘንና መተሳሰብ ከኢትዮጵያ ውጪ የትም መመልከት እንደማይቻል ተረዳሁ፡፡ ኢትዮጵያዊነትን ሳስብ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሰብዕናው ከፍ ያለ ሰው ነው የሚታየኝ፤›› በማለት የተረከው ደረጀ፣ ይህንኑ በግጥሙ ማካተቱን ገልጾ ነበር፡፡
ቀኝ ጌታ ዮፍታሄ ንጉሤ ከጻፉት የንጉሡ ዘመንም ሆነ አሰፋ ገብረ ማሪያም ከደረሱት የደርግ ዘመን መዝሙሮች በተለየ ሁኔታ፣ የወቅቱን የፖለቲካ አይዲዎሎጂ ሳይበርዝ ለረዥም ዘመን ሁሉንም አግባብቶ ሊዘመር የሚችል ግጥም ማቅረቡን ገጣሚ ደረጀ ይናገራል፡፡ የዜግነትን ክብር በማጉላት ሁሉንም ለማስተሳሰር መሞከሩን፣ ሰላም፣ ፍትሕና ነፃነትን በጉልህ በመዘርዘር ፍቅርና አንድነት የሚፈጠረው በእነዚህ መሠረታዊ ቁም ነገሮች መሆኑን ለማመልከት መሞከሩን ያብራራው ደረጀ ይሁን እንጂ፣ በሁሉም ሰው ዘንድ የሚጠብቀውን ዓይነት መግባባትና አቀባበል መዝሙሩ አለመፍጠሩ እንደ አገር ድክመት እንደሆነ አውስቷል፡፡
‹‹የደርግ መዝሙር ወደ 12 በሚሆኑ የኢትዮጵያ እንዲሁም በሦስት የውጭ ቋንቋዎች ተተርጉሞ ራሱን የቻለ ጥራዝ ታትሞ ተሠራጭቶለታል፡፡ የአሁኑ መዝሙር ይህን መሰል ነገር አልተደረገለትም፡፡ አንተን የሚወክል መዝሙር ይህ ነው ብለህ ለሰጠኸው ሕዝብ በራሱ ቋንቋ ጽፈህ ልትሰጠው ይገባል፡፡ የሚመለከተው አካል ስለብሔራዊ መዝሙሩ ምንነት ሁነቶችን ለምን አያዘጋጅም” ሲል የሚያነሳው ጸሐፊው፣ መዝሙሩ አገር የሚያግባባ፣ መኩሪያና፣ ብሔራዊ መገለጫ (National Symbol) መሆን ያልቻለው አንዱ በዚህ የተነሳ መሆኑን ይተርካል፡፡ መዝሙሩን በይፋ ሲዘምሩ የሚታዩ ሰዎች ጥቂት የሆኑትና በብሔራዊ መዝሙር ጉዳይ መግባባት ያልተቻለው በዚሁ ምክንያት የተነሳ መሆኑንም ይገልጻል፡፡
ገጣሚ ደረጀ ካለው በተጨማሪ በዛሬይቱ ኢትዮጵያ በብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ፣ በብሔራዊ ቋንቋ፣ በብሔራዊ ሕገ መንግሥት፣ በፌደራላዊ የፖለቲካ ሥርዓት አወቃቀርና በሌሎችም መሠረታዊ አገራዊ ጉዳዮች፣ ዜጎቿ መግባባት ሲሳናቸው በገሀድ የሚታይ ሀቅ ነው፡፡ ባለፉት 30 ዓመታት ዜጎች መሠረታዊ በሆኑ አገርን በሚወክሉ ጉዳዮች እንደተነታረኩ ነው ኢትዮጵያ የኖረችው፡፡
ሌላው ቀርቶ አንድ ቤተሰብም ቢሆን የጋራ ግብና የጋራ ራዕይ ሳይኖረው መኖር አይችልም ቢባልም፣ ኢትዮጵያዊያን ግን በብሔራዊ ጥቅምም ሆነ በብሔራዊ ደኅንነት አጀንዳዎች ላይም እየተነታረኩ መኖር መቀጠላቸው ይነገራል፡፡ ኢትዮጵያዊያን ከሚያስተሳሥራቸው ኢትዮጵያዊ ከሆነ የጋራ እሴት ይልቅ ለሚያለያያቸው የቡድን ማንነት ቅድሚያ በመስጠታቸው ብሔራዊ ስሜት ተዳከመ፣ ኢትዮጵያዊነት ጠወለገ፣ ብሔራዊ ማንነት ወደ ብሔር ተኮር ዘረኝነት ተቀየረ የሚል ሥጋት በተደጋጋሚ ሲነሳ ይደመጣል፡፡
ገጣሚ ደረጀ ኢትዮጵያዊነት እንደሰው መልካም አድራጊነት ነው ብሎ ቢናገርም ነገር ግን እርሱ ያን ቃለ መጠይቅ ከሰጠ በኋላ ባለፉት ስድስት ዓመታት በኢትዮጵያ ብዙ አሰቃቂ ሁኔታ መከሰቱ የአደባባይ ሀቅ ነው፡፡ አንዳንዶች ከኢትዮጵያዊነት የወጣ ወይም ኢትዮጵያዊነትን የማይመጥን የሚሉት እጅግ አሰቃቂ የጭካኔ ዓይነት በኢትዮጵያ በቅርብ ዓመታት ተከስቷል፡፡ በጌዲዎ በረሃብ ሕዝብ ሲፈጅ ታይቷል፣ በቡራዩ ሕዝብ በተኛበት ተጨፍጭፏል፣ በሻሸመኔ ሰው ተዘቅዝቆ ሲሰቀል የታየ ሲሆን፣ በአማራና በሐረሪ ክልሎች ሰው በእሳት ሲነድና አስከሬን አስፋልት ላይ ሲጎተት ታይቷል፡፡ በጅግጅጋ ቄስ በእሳት እንዲነድ ሲደረግ፣ በሐዋሳ ሰው በቆንጨራ ሥጋው ሲዘነጠል፣ በአሶሳ በዱላ ሲቀጠቀጥ፣ በወለጋ በብሔር ማንነቱ ተለይቶ ሕዝብ ሲጨፈጨፍ፣ በአጠቃላይ በመላው ኢትዮጵያ ብዙ ክፉ ነገር ሲደረግ ቆይቶ፣ በስተመጨረሻ ደግሞ የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ፈነዳ፡፡ ይህን ጊዜም ኢትዮጵያዊያን ሰብዓዊነት የተሞሉ ለሰብዓዊነት የሚጨነቁ መሆናቸው ቀርቶ ሰብዓዊነትን ያጎደሉና ከሰብዓዊነት የወረዱ ሆነው የሚኖሩ ሕዝቦች ናቸው የሚል ገጽታ በዓለም መድረክ አተረፉ፡፡ ከቀራቅር እስከ ዳንሻ፣ ከአክሱም እስከ የጭላ፣ በትግራይ፣ አፋርና አማራ ክልሎች ዓለም ይሰማዋል ተብሎ የማይጠበቅ አሰቃቂ መገዳደል በኢትዮጵያ ተከሰተ፡፡
ይህን ጊዜ ኢትዮጵያ እንደ አገር አስተሳስሮ ያቆማት የአንድነት ገመድ ሊበጠስ ጫፍ ደረሰ ተባለ፡፡ ኢትዮጵያዊነት በደምና በመገዳደል የተፈጠረ ሁሉም ያልተቀበለው ማንነት በመሆኑ እንጂ አገሪቱ ወደዚህ አስከፊ አዘቅት እንደማትገባም ብዙ ተተረተ፡፡ ኢትዮጵያዊነት በኢሕአዴግ ዘመን በተዘራው የብሔር ፖለቲካ ክፍፍልና ልዩነት እየተዳከመ መጥቶ በስተመጨረሻ ወደመበታተን አፋፍ ሲጠጋ የተፈጠረ አሳዛኝ ትራጀዲ እንደሆነም ብዙ ሲባል ሰነበተ፡፡
ከዚህ አለፍ ሲልም ኢትዮጵያዊነት የሚባል ማንነትም ሆነ ዕሳቤ ኖሮ የማያውቅ ነው ብለው የሚዘባበቱ ሀያሲያንና ተንታኞች ተበራከቱ፡፡ ብሔር ብሔረሰብና ሕዝቦች እንጂ ኢትዮጵያዊ የሚባል ማንነት የውሸት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ወይም ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚሉ ሰዎች በውሸት ማንነት የተሸፈኑ ናቸው፡፡ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ነን የሚሉ ጭምብላቸው ሲገለጥ የብሔር ማንነታቸው የሚታይ እንጂ ኢትዮጵያዊነት የሚል ማንነት ኖሯቸው አይደለም በሚል ብዙ ትችትና ውርጅብኝ ወደዚህ አቅጣጫ መወርወር ጀመረ፡፡
በእርግጥ ግን ኢትዮጵያዊነት የሚባለው አስተሳሳሪ ብሔራዊና አገራዊ ማንነት አለ ወይ የሚለውም ከናካቴው መጠየቅ ጀመረ፡፡ ዛሬ ላይ ትግሬ፣ አማራ፣ ኦሮሞ፣ ሲዳማ፣ ሶማሌ፣ ጉራጌ፣ አፋር፣ ወላይታ፣ ሀዲያ፣ ከምባታ፣ ጋሞ፣ ጎፋ፣ ሲልጤ…ወዘተ እየተባለ አንዴ በቋንቋ ሌላ ጊዜ በብሔር ማንነት ከሚከፋፈለው የአገሪቱ የፖለቲካ ቅርምት በዘለለ የጋራ ነው የሚባለው ኢትዮጵያዊነት ቦታም ሆነ ገበያ ያጣ የፖለቲካ ሀሊዮት ነው የሚል ከባድ ሙግትም ሲነሳ ቆይቷል፡፡
ኢትዮጵያዊነት የሚባል የጋራ ማንነትና እሴት አለ ከተባለ ኢትዮጵያ በሚባለው በአንድ ጂኦግራፊያዊ ግዛት ወይም ሉዓላዊ አገር ውስጥ የሚኖሩ ሕዝቦችን ማስተሳሰርና አንድ አድርጎ በሰላምና በትብብር ለማኖር ለምን ተሳነው የሚለው ጉዳይ ዛሬ ላይ በሰፊው ይጠየቃል፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን ደግሞ ኢትዮጵያዊነት ለይስሙላ ወይም ለፖለቲካ ትርፍ ማጋበሻ የሚውል ሸቀጥ እየሆነ ነውም ይባላል፡፡ የቅርብ ጊዜ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ታሪክን እንደ ምሳሌ የሚያነሱ ሰዎች በርካታ ፖለቲከኞች ጠባብ የብሔር ፖለቲካ አላዋጣ ሲላቸው ኢትዮጵያዊነት የሚለውን መቆመሪያ ካርታ እየተጠቀሙበት ነው በማለት ይናገራሉ፡፡ ይህን ደግሞ በኢትዮጵያ የመጣው የፖለቲካ ለውጥን ተከትሎ በፖለቲካ ገበያው ብቅ ብቅ ያሉ ፖለቲከኞችን የፖለቲካ አቋም መከረባበት ምሳሌ በማድረግ ነው የሚያቀርቡት፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) እንቅስቃሴ ውስጥ ግንባር ቀደም ተሳታፊ ከነበሩት አንዱ መላኩ ተገኝ (ዶ/ር) ኢትዮጵያዊነት ቀደም ባለው ዘመን አሁን ካለው ፍፁም የተሻለ ትርጓሜና የፖለቲካ ሥነ ምግባር ነበረው ይላሉ፡፡ ‹‹ኢትዮጵያዊነት አገራችን ነፃነቷን አስከብራ መኖር ከጀመረችበት ጊዜ ጀምሮ ሁሉንም አሰባሳቢ ግብ ነበረ፡፡ ሙሶሎኒ ነፃነታችንን ከተፈታተነ በኋላ ግን ለአገር ወይም ለኢትዮጵያዊነት ለመሞት ለነፍሳቸው የማይሳሱ ሰዎች እንዳሉ ሁሉ በባንዳነት ተሠልፈው ኢትዮጵያን የሚወጉ ሰዎች መኖራቸውም ዕውን ሆነ፡፡ ነፃነት ከተመለሰ በኋላ ለኢትዮጵያ የተዋደቁ ተረስተው ባንዳው ወገን ሹመትና ሽልማት ማግኘቱ ደግሞ የኢትዮጵያዊነት ዋጋ ስንት ነው የሚል ጥያቄ የፈጠረ ሆነ›› በማለት ሰዎች ለኢትዮጵያዊነት ሲከፍሉት የነበረውን መስዋዕትነት አንዳንድ የፖለቲካ ብልጣ ብልጦች እንዴት መጠቀሚያ ሲያደርጉት እንደኖሩ ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያዊነት ብዙዎች የሚሞቱለት አሰባሳቢ ርዕዮተ ዓለም መሆኑን በርካቶች መስክረዋል፡፡ ኦጋዴን ላይ ከመላው ኢትዮጵያ የመጣ የኢትዮጵያ ጀግና ደሙን የገበረው፣ ባድሜ ላይ ከመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የተገኙ ልጆች በፈንጂና መትረየስ የረገፉት፣ በማይጨው ጦር ግንባር ብዙዎች አጥንታቸውን የከሰከሱትና የተዋደቁት ለኢትዮጵያዊነት ብለው መሆኑ ያግባባል፡፡ ህዳሴ ግድብን በአሁኑ ዘመን ተባብረው እየገነቡት እንዳሉት ሁሉ ጥቁር አምበሳ ሆስፒታልን አንድ ብር አዋተው የዛሬ 50 ዓመት ያሠሩት ኢትዮጵያዊያን ለጋራ አገራዊ ግብ ብለው መሆኑም በምሳሌነት ይቀርባል፡፡ ይሁን እንጂ በቅርብ ጊዜ ከሰፊው የጋራ ማንነትና ዕሴት ይልቅ በሰፈርና በክልል በታጠረ ዕሳቤ ውስጥ ሁሉም ወድቋል፣ ይህ ደግሞ ከኢትዮጵያዊነት ሥነ ልቦና ማሽቆልቆል ጋር ሲያያዝ ነው የሚታየው፡፡ ዛሬ ዛሬ ይባስ ብሎ ኢትዮጵያዊነትን አቀነቅናለሁ፣ አሰባሳቢ አገራዊ አጀንዳ ወይም የአገረ መንግሥት ህልውና ጉዳይን የሚመለከት ሐሳብ ይዤ መጥቼያለሁ የሚል የፖለቲካ ኃይል ልክ እንደ ሐሰተኛ ነብይ በጥርጣሬ የሚታይበት የታሪክ አጋጣሚ ላይ አገሪቱ የደረሰች ነው የሚመስለው፡፡
እንደ ለማ መገርሳ ያሉ ፖለቲከኞች ከጥቂት ዓመታት በፊት ‹‹ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው እያሉ የፖለቲካ ሿሿ ሕዝቡን ሠሩት›› የሚል ሀሜት ሲነሳባቸው ጠንከር ያለ ምላሽ ሲሰጡ ተደምጠው ነበር፡፡ ‹‹ኢትዮጵያዊነት ለማለት ማንም ውል ያስገባኝ የለም›› የሚል መልስ የሰጡት ለማ ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው ያሉት ከልባቸው አምነውበት እንጂ ለምላስ ወይም ለፖለቲካ ጮሌነት አለመሆኑን አስረግጠው ሲናገሩ ተደምጠው ነበር፡፡
ለማ ብቻ ሳይሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) እና ሌሎችም ፖለቲከኞች የከንፈር ኢትዮጵያዊ ፖለቲከኞች በሚል ስማቸው ሲብጠለጠል ይሰማል፡፡ ኢትዮጵያዊነትን ወይም አገራዊ አንድነትን እናቀነቅናለን የሚሉ ፖለቲከኞች ‹‹አሀዳዊያን›› የሚል ለስድብ የተጠጋ ፍረጃ ሲሰጣቸውም ይታያል፡፡ ‹‹መነሻችን አማራነት መድረሻችን ኢትዮጵያዊነት›› ከሚሉ የፋኖ ኃይሎች ጀምሮ የአንድነት ወይም አገራዊ ፖለቲካን ያቀነቅናሉ ተብለው የሚታሰቡ ኃይሎች በአብዛኛው በኢትዮጵያዊነት ጭምብል የተሸፈኑ የብሔር ፖለቲከኞች ወይም የውሸት ኢትዮጵያዊያን ናቸው የሚል ጥቅል ፍረጃ ሲካሄድባቸው ይስተዋላል፡፡
ይህ ሁሉ ውዝግብ የታሪክ መነሻ ሊኖረው እንደሚችል የሚጠቅሱት መላኩ (ዶ/ር) በደርግ ዘመን በኢትዮጵያዊነት ጥላ የተፈጠረውን ችግር ያስታውሳሉ፡፡ ንጉሡ ከነፃነት በኋላ ባንዳ አስጠግተው ለኢትዮጵያ መስዋዕት የሆኑትን መግፋታቸው በዚያን ዘመን ወጣቶች በተለይም በተማሪዎች አለመወደዱን ያነሳሉ፡፡
‹‹የተማሪዎች እንቅስቃሴ ኢትዮጵያዊነት ለሚለው ፖለቲካ አዲስ ትርጉም የሰጠ ነበር፡፡ ኢትዮጵያዊነት የውጪ ጠላትን ታግሎ መሰዋዕት ሳይሆን ሰፊውን ሕዝብ በጭቆናና በደል እንዲማቅቅ ያደረገውን በዝባዥ ሥርዓት መታገል ነው ብለው አብዮተኞች ተነሱ፡፡ አገር ወዳድነት ለተጨቆኑ ሕዝቦች መቆም ነው ብለው በጋራ በኢትዮጵያዊነት ጥላ ተሠለፉ፡፡ በኢትዮጵያ የሃይማኖትና የማንነት እኩልነት እንዲከበር ተሰው፡፡ ብዙ መስዋዕትነት ከፍለው ሥርዓቱን አስወገዱት፡፡ ሆኖም ደርግ ኢትዮጵያ ትቅደም የሚል መፈክር አስቀድሞ በአቋራጭ አራት ኪሎ ገባ፡፡ ኢትዮጵያ ትቅደም ያለውና የኢትዮጵያ ዋስም ጠበቃም ከእኔ በላይ ለአሳር ብሎ የተነሳው ደርግ እጅግ አስፈሪ አምባገነናዊ ሥርዓት ፈጠረ፡፡ ብዙ የኢትዮጵያ ልጆችን ጨፈጨፈ፡፡ በዚህ የተነሳ እሺ ባይነት ወይም አድር ባይነት መንፈስ ነገሠ፡፡ ደርግን ፍራቻ ብቻ ብዙዎች ኢትዮጵያ ቅደሚ እያሉ መዘመር ሲመርጡ ሌሎች የደፈሩ ደግሞ ጫካ ገብቶ መዋጋት ሆነ ምርጫቸው፡፡ ያን ጊዜም ኢትዮጵያዊነት እውነተኛ ሚዛኑ ጠፍቶ በአድር ባይነት ተተካ፡፡ ከደርግ በተቃራኒ ሆነው ኢትዮጵያ ትውደም እያሉ በጠብመንጃ ሲዋጉ የኖሩት ተገንጣይ ኃይሎች ኢትዮጵያን አምርረው እንደጠሉ ነው አራት ኪሎ የደረሱት፡፡ ይህን ጊዜ ግን ባንኩም ታንኩም በእጃቸው ስለገባ ኅብረ ብሔራዊ ኢትዮጵያን እንገነባለን የሚል አዲስ ፕሮጀክት ጀመሩ፡፡ ኅብረ ብሔራዊ ኢትዮጵያዊነት ቢሉም አብዛኞቹ ተገንጣይ ኃይሎች ኢትዮጵያን በመጥላትና በመውጋት በትግል የኖሩ ጠባብ ብሔረተኛ ኃይሎች መሆናቸው ከ30 ዓመታት በኋላ በመጨረሻ ተጋልጧል፤›› በማለት ነበር የኢትዮጵያዊነት ሀሊዮት ዑደትን ያስረዱት፡፡
በለውጡ ሰሞን ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት የሚሉ የፖለቲካ ዲስኩሮች ጎላ ብሎ በሚደመጡበት ወቅት በሕዝቡ ዘንድ የተፈጠረው ፖለቲካዊ ንዝረት የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡ ብዙዎች ከመከፋፈልና ከመናቆር ወጥታ አንድነቷ የጠነከረ አገር ሊኖረን ነው ብለው ለውጡን ሊደግፉ ከመላው ዓለም ተሰባሰቡ፡፡ የለውጡ ኃይል (ወይም ቲም ለማ ይባል የነበረው ለውጡን ከፊት ሲመራው የነበረው ከፍተኛ አመራር) የኢትዮጵያን ህልውና ማስቀጠልና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን መገንባት እስከቻለ ድረስ ከለውጡ ጎን እንቆማለን ብለው የተሰበሰቡ የፖለቲካ ኃይሎች እጅግ ብዙ ነበሩ፡፡
ይሁን እንጂ በዚህ ወቅትም ቢሆን የለውጡ ኃይል በምላሱ ኢትዮጵያ ቢልም ዋና ድብቁ አጀንዳው ግን ኢትዮጵያን ከፋፍሎ መሸጥ ነው የሚል ከጨለምተኝነት የሚመደብ ጥርጣሬ ያሳደሩና ትችት የሚያሰሙ ጥቂቶች ነበሩ፡፡ የለውጡ ኃይል ነባሩን ፌደራላዊ ሥርዓት እንዲሁም የብሔሮችን የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት ደፍጥጦ በሒደት ያለፈውን የነፍጠኛ ሥርዓት ለመትከል የመጣ ነው የሚሉ ኃይሎችም እንዲሁ ቅሬታ ሲያሰሙ ነበር፡፡ ይህ ሁሉ ግን ለውጡ የኢትዮጵያ ህልውና ለማስጠበቅም ሆነ ዴሞክራሲያዊ መሠረት ለመጣል ይበጃል ብለው ለአገራዊ ግብ ተሰባስበው ለውጡን ሲደግፉ ከነበሩ ወገኖች ቁጥር ጋር ሲነጻጸር እጅግ አነስተኛ ስለነበር የለውጡ ኃይል ሰፊ ቅቡልነትና ድጋፍ አግኝቶ ለተወሰኑ ዓመታት ለመቀጠል አልተቸገረም ነበር፡፡
በሒደት ግን በአገሪቱ ግድያዎች በዙ፣ ግጭቶች በረከቱ፣ የሰዎች ሕይወት አደጋ ላይ መውደቁ እየሰፋ ሄደ፣ ሞት ጨመረ፣ ውድመት በረከተ፣ በአጠቃላይ አገሪቱ በቀውስ አዙሪት ውስጥ ተዘፈቀች፡፡ ይህ ደግሞ ለውጡ አገራዊ አንድነትንና ህልውናን ያፀናል ብሎ ተስፋ ያሳደረውን ኃይል መከፋፈልና ጥርጣሬ ላይ መጣል እንደጀመረ ይነገራል፡፡ በሒደት የተፈጠረው ከባድ ጦርነትና የፖለቲካ ምስቅልቅል ደግሞ ብዙ ዓይነት የፖለቲካ አሠላለፍ ለውጦችን በዚህ አገር ይዞ መጥቷል፡፡ አሁን ላይ በለውጡ ላይ ጥርጣሬን ቀድመው ያሳደሩ ኃይሎች ድሮም ብለን ነበር የሚል ትችት ሲያሰሙ ነው የሚደመጠው፡፡ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ያሉ በመጨረሻ የእጃቸውን አገኙ ሲሉም ይደመጣል፡፡
ለውጡን ሲደግፉ የቆዩ ደግሞ ‹‹ኢትዮጵያዊነት ደካማ ጎናችንና መጠቂያችን›› በሚል ስሜት አገሪቱ አሁን የምትገኝበትን አሳሳቢ አደጋ ለውጡን ከደገፉበት አጋጣሚ ጋር እያነጻጸሩ ሲፀፀቱ ነው የሚታየው፡፡ ይህ አጋጣሚ ኢትዮጵያ የሚል የፖለቲካ አጀንዳ ይዞ የመጣ ኃይል ሰፊ ድጋፍ አሰባስቦ በአቋራጭ የአራት ኪሎ ሥልጣን ከተቆናጠጠ በኋላ ሕዝብ ከሚፈልገው በተቃራኒ የራሱን ፍላጎት እየጫነ የሚመራበትን ምቹ መደላድል ለመፍጠር መጠቀሚያ እየሆነ ነው የሚል ድምዳሜ በብዙዎች ዘንድ እንዲፈጠር ያደረገ መሆኑም ይነገራል፡፡
ኢትዮጵያዊነት የሚለው አገራዊ አንድነት ላይ ያተኮረ ፖለቲካ ሰፊ የሕዝብ ድጋፍ የሚያስገኝ ስለሆነ ወይም ደርግን ጨምሮ በኢትዮጵያ የተፈራረቁ መንግሥታት ሥልጣን ለማፅናት የተጠቀሙበት ፖለቲካ ስለሆነ ብቻ ነው የሚፈለገው ወይ የሚልም ጥያቄ ይነሳበታል፡፡ ኢትዮጵያ አንድነቷ አደጋ ላይ በወደቀበት በዚህ ወቅት የኢትዮጵያ ህልውና ያሳስበኛል ብሎ የሚመጣ ኃይል የተሳሳተ አጀንዳ ይዞ የተነሳ ነው ተብሎ አይበየንም፡፡ ይሁን እንጂ የኢትዮጵያን አንድነት መታደግ ሲል እስከምን ድረስ ለመሄድ የቆረጠ ነው የሚለው ጥያቄ ያስነሳል፡፡ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ የሚለው ከልቡ አምኖበትና የአገር አንድነት አሳስቦት ነው ወይስ ከጀርባው የተደበቀ ከፋፋይ የብሔር ፖለቲካ አጀንዳ አንግቦ የሚለው ብዙ ሙግት የሚያስነሳ ጉዳይ መሆኑ አይቀርም፡፡
በለውጡ የመጀመሪያ ወቅቶች ለውጡን ሲተቹ ከነበሩና በኢትዮጵያ የነፍጠኛ ሥርዓት ዳግም ለመትከል እየተሞከረ ነው የሚል ነቀፋ እስከማሰማት የደረሱት ፖለቲከኛ ጃዋር መሐመድ በአንድ ወቅት ‹‹ኢትዮጵያዊያን ከምኒልክ ዘመን ጀምሮ በከፍታ የሚጠቀስ የጋራ ታሪክ የለንም›› ብለው መናገራቸው ታላቅ የፖለቲካ አቧራ አስነስቶ ነበር፡፡ ጃዋር ባለፉት ስድስት ዓመታት በኢትዮጵያ ከተፈጠረው የፖለቲካ ምስቅልቅል ጋር ስማቸው ተያይዞ የሚነሳ፣ ኢትዮጵያዊ ብሔረተኝነትንና የኦሮሞ ፖለቲካን በሚመለከት እጅግ በርካታ አወዛጋቢ ጉዳዮችን ሲያነሱ የቆዩ ፖለቲከኛም ናቸው፡፡
ይህ ሁሉ አልፎ ግን ከሰሞኑ የአገር ህልውና እንዳሳሰባቸው ሲናገሩ መደመጥ ጀምረዋል፡፡ የአገረ መንግሥት መፍረስ፣ የኢትዮጵያ አንድነት መዳከምና ለአደጋ መጋለጥ ያሳሰባቸው መሆኑን በጉልህ እያሰሙ ይገኛል፡፡ ጃዋር በጥቂት ዓመታት ልዩነት ይህን ያህል ጽንፍ የወጣ የአቋም ልዩነት እንዴት ሊያመጡ ቻሉ የሚለው እያነጋገረ ነው፡፡ ጃዋር ካላቸው ተፅዕኖና ተሰሚነት አንፃር የእሳቸው አቋም መቀየር ጎልቶ ቢነገርም በተለያዩ አቅጣጫ የተሠለፉ ኢትዮጵያዊነትንና አገራዊ አንድነትን በተመለከተ ፍፁም የተለየ አቋም ሲያራምዱ የቆዩ የፖለቲካ ኃይሎች በዚህ ዙሪያ አመለካከታቸው መለወጡን ሲያንፀባርቁ እየታየ ነው፡፡ ይህ ከምን የመነጨ ነው የሚለው ደግሞ ብዙ እያነጋገረ ነው የሚገኘው፡፡
ዲፕሎማትና የሶሺዎሎጂ ተመራማሪ የሆኑት፣ በደርግ ዘመን በብሔረሰብ ጥናት ኢንስቲትዩት ጭምር ያገለገሉት ፍሰሐ አስፋው (ዶ/ር) ይህ ጉዳይ ብዙ ምክንያት ያለው ሊሆን እንደሚችል ይናገራሉ፡፡ ‹‹አንደኛ ኢትዮጵያዊነት የሚለው አጀንዳ የተለያዩ የፖለቲካ አጋርነቶችን ለመፍጠር ያግዛል፡፡ ሁለተኛ ጠንካራ የፖለቲካ ድጋፍ አሰባስቦ ሥልጣን ለመቆናጠጥ የተሻለው መንገድ ሆኖም ሊታይ ይችላል፡፡ ኢትዮጵያ ልትፈርስ ነው የሚለው ሥጋት በእርግጥ ተጨባጭነት ያለው አሳሳቢ ጉዳይ ነው፡፡ ከአገር መሪው አፍ ጭምር የኢትዮጵያ መበታተን ጉዳይ በተደጋጋሚ ነው የሚሰማው፡፡ ይህ ተጨባጭ ሀቅ በሆነበት አገር ማንም ፖለቲከኛ የኢትዮጵያን ህልውና እንታደግ ብሎ ቅስቀሳ ማድረግ ቢጀምርና ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ቢል ከልቡ ባይሆን እንኳን ሰፊ ድጋፍ ለማግኘት አዋጪ መሆኑን በመተማመን ነው፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡
ኢትዮጵያን በሁሉም አቅጣጫ ተዘዋውረው የብሔረሰቦችን ማንነት፣ ሥነ ልቦና፣ ታሪክና ባህል በማጥናት ያሳለፉት ፍሰሐ (ዶ/ር) በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢ ሲኬድ ሰዎች የአገር አንድነትን የሚመለከት ጥያቄ ሲያነሱ እንዳልተመለከቱ ይገልጻሉ፡፡ ‹‹በየቦታው ስትሄድ እኔ የእከሌ ብሔር አባል ነኝ ሲል ሳይሆን የተወለደበትን ቀዬና አካባቢ ስም ነበር ሰው የሚጠራው፡፡ የሐረር፣ የጂማ፣ የጎጃም፣ የወሎ፣ የወለጋ…ወዘተ ሰው ነኝ የሚል ስም ለራሱ የሚሰጥ ነበር ሕዝቡ፡፡ የፖለቲካ ኢሊቱ ኢሕአዴግ ሲገባ ግን ይህን መረዘው፡፡ አንተ ከዚህ ወገን ነህ፣ እከሌ ደግሞ ከዚያ ወገን ነው የሚል በሥርዓተ ትምህርት ጭምር የተደገፈ የዘር ፖለቲካ ማጥመቅ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ተፈረደበት፡፡ በሕገ መንግሥቱ ኢትዮጵያ ከሚለው አስተሳሳሪ ማንነት ይልቅ ብሔር ብሔረሰቦች የሚል የአገር ባለቤትነትና የፖለቲካ ሥርዓት እንዲፀና ተደረገ፡፡ ይህ አገር አልባ እንዲሆኑ በማሰብ በኢትዮጵያዊነት ላይ የተካሄደ ታላቅ ወንጀል ነው ለእኔ፤›› በማለትም የኢትዮጵያዊነት ሥነ ልቦናና ዕሴት ተመታ ያሉበትን የታሪክ አጋጣሚ አስረድተዋል፡፡
ዛሬ ላይ ማንም ፖለቲከኛ በብሔር ወይ በቡድን ቢደራጅ አይፈረድበትም የሚሉት ፍሰሐ (ዶ/ር) በቡድን መደራጀት አላዋጣ ሲለው ደግሞ የኢትዮጵያዊነት ብሔረተኝነት ካባ ደርቦ የፖለቲካ ቁማር ለመብላት ቢጣጣርም እንዲሁ አይፈረድበትም ይላሉ፡፡
ግንቦት 1991 በለንደን በተደረገውና በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ምክትል ጸሐፊ ሄርማን ኮህን ዋና አስተባባሪነት በተደረገው የሰላምና የሽግግር ኮንፍረንስ ላይ የኢትዮጵያን ዕጣ ፈንታ ለመወሰን የተገኙት የወቅቱ የፖለቲካ ልሂቃን ታሪካዊ ስህተት መፈጸማቸውን ብዙዎች ያስታውሱታል፡፡ በኤርትራ ተሰነይ ከዚያ ቀደም የተካሄደው መለስ ዜናዊ፣ ሌንጮ ለታና ኢሳያስ አፈወርቂን የመሳሰሉ የኢሕአዴግ፣ ኦነግና የኤርትራ ነፃነት ግንባር አመራሮች የታደሙበት ስብሰባ ላይ ሦስቱ ኃይሎች ሁሉንም ነገር ጨርሰውት እንደነበር ብዙ ማስረጃ ይቀርብበታል፡፡ ደርግን አሸንፈናል ብለው የደመደሙት ኢሕአዴግ፣ ኦነግና የኤርትራ አርነት ግንባር የኢትዮጵያን ዕጣ ፈንታም ሆነ የኤርትራ መገንጠል ጉዳይን ተሰነይ ላይ ወስነው ለንደን ላይ በድል አድራጊነት መንፈስ መቅረባቸውን በወቅቱ የነበሩ ልሂቃን ሲናገሩት ይደመጣል፡፡
ኦነግና ኢሕአዴግ ተሻርከው ሰፊዋን ኢትዮጵያን ሊገዙ፣ ኤርትራን ከኢትዮጵያ ገንጥሎ የመምራቱን ባለቤትነት ደግሞ ሻዕቢያ ሊወስድ ተስማምተው ከጨረሱ በኋላ የለንደኑ ጉባዔ መጠራቱን የሚጠቅሱ በርካታ ሲሆኑ ይህ ታሪካዊ የፖለቲካ ስህተት ደግሞ በዋናነት በአሜሪካ ድጋፍ በእነ ሄርማን ኮህን አስፈጻሚነት ይመራ እንደነበር ይገልጻሉ፡፡
በተማሪዎች ንቅናቄ ያለፉት፣ ደርግ ሲመጣም የኢትዮጵያ ጭቁኖች አብዮታዊ ትግል (ኢጭአት) ፓርቲን ከመሠረቱትና ከመሩት አንዱ የነበሩት ታዋቂው የሕግ ምሁር፣ ፖለቲከኛና ጸሐፊ አቶ አሰፋ ጫቦ ጭቆናን መታገል የሚለው ሐሳብ የዚያን ዘመን ልሂቃንን አሰባስቦ ለማቆየት እንዳልቻለ የኢጭአትን ውድቀት መሠረት አድርገው ይናገራሉ፡፡ ኢሕአዴግ ደርግን ተክቶ ሥልጣን ሲይዝ የሽግግሩ ምክር ቤት ተሳታፊ እንዲሆኑ መጋበዛቸውን ያስታውሳሉ፡፡ በዚህ ወቅት የተፈጠሩ ነገሮችን ኢትዮጵያ አሁን ከገጠማት ፖለቲካዊ ችግር ጋር አዛምደው የሚገልጹት አቶ አሰፋ ሄርማን ኮህን በጊዜው ራሱን የሻዕቢያ፣ ኦነግና ኢሕአዴግ የጡት አባት አድርጎ ያይ እንደነበር ይጠቅሱታል፡፡
‹‹አንተ ከየትኛው ጎሳ ነህ ብሎ አንድ ቀን ጠየቀኝ›› የሚሉት አቶ አሰፋ ‹‹ኢትዮጵያዊ ነኝ›› ሲሉት ‹‹አንተ ገና አልገባህም›› ብሎ እንደመለሰላቸውም መስክረዋል፡፡ በሽግግር ምክር ቤት ውስጥ ብዙ ቢጮሁም በተሰነዩ ስብሰባ አለፍ ሲልም በለንደኑ ጉባዔ የኢትዮጵያም ሆነ የኤርትራ ዕጣ ፈንታ ተወስኖ ስለነበር ትርጉም አልነበረውም የሚሉት አቶ አሰፋ ዛሬም ቢሆን በኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ዘንድ የሚያወያይና የሚያግባባ አቋም የጠፋው በዚያ የተነሳ መሆኑን አውስተዋል፡፡
‹‹የኢትዮጵያ የተቃዋሚ ፖለቲካ ኃይሎች በአገሪቱ የተፈጠረውን የብሔር ብሔረሰቦች ፖለቲካዊ ሥርዓት ካልተቀበሉ የሚል አቋም ላይ ቆሟል፡፡ ተቃዋሚዎች ደግሞ የብሔር ፖለቲካው አገሪቱ በዘር እንድትከፋፈል ያደረገና ሊያፈርሳት የሚችል ነው የሚል አቋም ይዘዋል፡፡ ይህ የመነጋገሪያ ዕድል የማይሰጥ ፅንፍ የወጣ የፖለቲካ አቋም ነው፤›› የሚሉት አቶ አሰፋ ይህ ደግሞ አሁን ያለውን የፖለቲካ ልዩነት አስታርቆ የአገር አንድነትን ጠብቆ ለማስቀጠል ፈታኝ መሆኑን ይገልጹታል፡፡
የኢትዮጵያ አፈጣጠር ከዓለም አገሮች አፈጣጠር ታሪክ የተለየ ሆኖ ለምን በዘመኑ የፖለቲካ ልሂቃን እንደሚቀርብ የሚጠይቁት አቶ አሰፋ ‹‹ሰዎቹ ናሽናል ስቴት መኖሩን ይረሱታል፡፡ በመላው ዓለም ብዙ አገሮች የተፈጠሩት በኃይል ነው፡፡ የኢትዮጵያም ከዚያ የተለየ አይደለም፡፡ ማዕከላዊ መንግሥት ብዙዎቹ ሲመሠርቱ የተጠቀሙት በጠብመንጃ ነው፡፡ ጀርመንም ሆነ ጣሊያንና ሌሎች አገሮችን ታሪክ እንይ፡፡ በእኛም አገር የመጣንባቸውንና የዛሬይቱን ኢትዮጵያ ቅርፅ የፈጠሩ የታሪክ ክስተቶችን ከምኒልክም አልፈን እንመልከት፡፡ የኦሮሞ ወደ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ መስፋፋትም ሆነ የግራኝ አህመድ ዘመቻዎች ኃይል ወይም ጉልበት የመጠቀም መንገድን የተከተሉ ነበሩ፡፡ ዘመናዊው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ታሪክ ከእነዚህ ወይም ከሌሎች አገሮች ታሪኮች የተለየ ሆኖ ለምን ይታያል፤›› በማለት አከራካሪ የሆነ የፖለቲካ ነጥብን ያነሳሉ፡፡
በሀቀኝነት ተነጋግሮና ተግባብቶ እያደገ የሚሄድና ለረዥም ዘመናት የሚሠራ የፖለቲካ ሥርዓት በኢትዮጵያ መፍጠር እንደሚበጅ የሚመክሩት አቶ አሰፋ በ40 ዓመታት የሦስት መንግሥታት መፈራረቅና የደረሰው ቀውስ ሁሉንም ሊያስተምረው እንደሚገባ ይጠቁማሉ፡፡ ‹‹ለሰለሞናዊው የዘውድ መንግሥት 251ኛ ሲባሉ የኖሩትና ሥልጣን ከዘራቸው እንደማይወጣ በሕገመንግሥት ጭምር ያስከተቡት አፄ ኃይለ ሥላሴ በአንዴ ሲገረሰሱ ዘለዓለም መግዛት እንደማይቻል አየን፡፡ ደርግ ሥር ነቀል አብዮት ብሎ መጣ፡፡ ነገር ግን ብዙም ሳይጓዝ ከሰመ፡፡ ኢሕአዴግ የብሔር ብሔረሰቦች የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት ባለቤት አደረግኩ ብሎ የሚነቀንቀው እንደሌለ ቢናገርም አሁንም ቢሆን ፖለቲካዊ ቅራኔዎችና ችግሮች አልተፈቱም፡፡ በ40 ዓመታት ካየነው ውጣ ውረድ በመማር ለሁሉም የሚበጅ ሥርዓትን በመነጋገር መፍጠር ነው የሚሻለው፤›› ሲሉም መክረዋል፡፡
በደርግ ዘመን ተቋቁሞ በነበረው የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች ጥናት ኢንስቲትዩት ውስጥ የሠሩት ከሕግ እስከ ፖለቲካ ሳይንስ የተማሩትና ሀሰን ኡመር አብደላ በሚል የብዕር ስም በጦቢያ መጽሔት ላይ የታሪክ ቀመስ ትንተናዎችን በማስነበብ የሚታወቁት አቶ ዩሱፍ ያሲን በኢትዮጵያ የተፈጠሩ የማንነት ግጭቶችን ለመፍታት በደርግ የመጨረሻ ዓመታት የተሞከሩ ጥረቶችን በሰፊው ያወሳሉ፡፡ ደርግ ከነበረው ግፊትም ሆነ ተነሳሽነቱን በመውሰድ የኢትዮጵያ ብሔረሰቦችን ታሪክና ማንነት የሚያጠና እንዲሁም ራስን በራስ የማስተዳደር መብት የሚባለውንና የሕዝቦች መብትን የተመለከቱ ሲያጋጩ የቆዩ ጥያቄዎችን የሚፈታ የአስተዳደር ሥልት የሚያመነጭ ተቋም መፍጠሩን ያመለክታሉ፡፡
ተሳትፎ ባደረጉበት በኢንስቲትዩቱ ከተጠና በኋላ ሦስት አራት የሚሆኑ የአስተዳደር መዋቅር የመፍጠር አማራጮችን ጨምሮ የሕገ መንግሥት ረቂቅንም አርቅቆ የማቅረብ ሥራም መሥራቱን ይናገራሉ፡፡ በተለይ በወቅቱ የትጥቅ ግጭት የሚካሄድባቸውንና ችግር አለባቸው ተብለው የተለዩ አምስት አካባቢዎችን ራስ ገዝ የማድረጉ ዕቅድ በዚህ ወቅት መቅረቡንም ያመለክታሉ፡፡
ኤርትራ፣ ትግራይ፣ አሰብ፣ ድሬዳዋና ኦጋዴን ከፊል ራስ ገዝ ሆነው እንዲመሠረቱ እንዲሁም ወደ 25 የሚሆኑ ሌሎች ክልሎች ያሉት አስተዳደራዊ መዋቅር በዚህ መሠረት እንደተፈጠረ የሚናገሩት ዩሱፍ ሆኖም ደርግ በኢሕአዴግ በመተካቱ ነገሩ በጅምር መፍረሱን ይናገራሉ፡፡ በቦታው የተተኩት ኢሕአዴጎች የኢንስቲትዩቱን የጥናት ውጤቶችና ምክረ ሐሳቦች በራሳቸው መንገድ በመተርጎም ለእነሱ አመቺ የሆነውን የዛሬውን በዘር ክልሎች የተከፋፈለ አስተዳደራዊ መዋቅር ወደመፍጠር እንደገቡ ነው የገለጹት፡፡
‹‹ሰዎች አንድ የሚያደርጋቸውና የሚያሰባስባቸው ጉዳይ ላይ ከማተኮር ይልቅ አናሳ ማንነቶቻቸው ላይ ወደ ማጋደል ከሄዱ ሁሌም ግጭት ይፈጠራል፡፡ ሃይማኖት፣ ብሔር፣ ቋንቋ፣ መደብ፣ ፆታ፣ እየተባለ ሰዎች በአናሳ ማንነቶቻቸው ላይ የተመሠረተ የፖለቲካ አይዲዎሎጂ ላይ የተመሠረተ የፖለቲካ እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ መፍቀድ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለምም ግጭት ሲፈጥር ነው የታየው፡፡ አናሳ ማንነት ላይ የተመሠረተ ፖለቲካ ሁሌም ቢሆን አሰባሳቢና የጋራ በሆነው ኅብረብሔራዊ ማንነትን የሚፈታተን መሆኑ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአውሮፓም ሆነ በሌሎች አካባቢዎች ተሞክሮ ተረጋግጧል፡፡ ዜግነትን እንዲሁም አገራዊ አንድነትን መሠረት ያደረገው አሰባሳቢ ብሔረተኝነት የፈለገ ቢሆን በቡድን ማንነቶች ሲፈተን ይታያል፤›› በማለት የሚያስረዱት ዩሱፍ ኢትዮጵያ የገጠማትና ዛሬም የአገርን ህልውና እየተፈታተነ የሚገኘው የዚያ ግጭት ውጤት መሆኑን ይናገራሉ፡፡
ሰዎች በቡድን ስብስቦች ውስጥ መደራጀትን የራስን ዕድል በራስ ከመወስ መብት ጀምሮ፣ ለዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶቻቸው መከበር የተሻለ መንገድ ነው ብለው ቢቀበሉትም ነገር ግን በብሔርም ሆነ በሃይማኖትና በቋንቋ መደራጀትን ክልክል ባደረጉ አገሮች ውስጥ ዜጎች ኢትዮጵያዊያን ዛሬ አገኘን ከሚሉት ፍፁም የተሻለ ነፃነትም ሆነ ዕድገት የመጎናጸፍ ዕድል ማግኘታቸው ዓለም በገሀድ የሚያየው የማይታበይ ሀቅ መሆኑን አቶ ይሱፍ የአገሮች ስምን በመጥቀስ ሞግተዋል፡፡ ‹‹መብት ወይም ነፃነትን የመጎናጸፍ ፍላጎት በባህሪው የሰው ልጆች የማይቋረጥ ፍላጎት ነው፡፡ ሰዎች ዛሬ ያገኙትን መብት ይዘው ቀሩኝ ለሚሏቸው መብቶች መከበር መታገላቸው ሁሌም የኖረ ሀቅ ነው፡፡ ኢሕአዴጎች የብሔሮችን የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት አስከበርን ቢሉም እሱም ቢሆን ተሸራርፎ እንጂ ምሉዕ ሆኖ አያውቅም፡፡ በዚህ ላይ የሰዎች የነፃነት ፍላጎት በዚያ የሚገታ ብቻ ባለመሆኑ ከቀደሙት ሥርዓቶች በተሻለ የብሔረሰቦችን መብት ያረጋገጠ ነው የተባለው ኢሕአዴግ ከአንድ ትውልድ በላይ ዕድሜው መሻገር አልቻለም፤›› በማለት ያስቀምጣሉ፡፡ ይህ ዑደት የፈጠረው ፍጭት ደግሞ ዛሬ ላይ የሁሉም ዜጎች መኖሪያ የሆነችውን ኢትዮጵያ አንድነት መፈታተኑን ያሰምሩበታል፡፡ ሰዎች ከአናሳ ማንነት ስብስብ ፖለቲካ ወጥተው አሰባሳቢ በሆነው የዜግነት ፖለቲካ ላይ ቢያተኩሩ ይቀሩናል የሚሉትን የሰብዓዊም ሆነ ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር አመቺ ዕድል እንደሚፈጠርና የአገሪቱም አንድነትና ህልውና ተጠብቆ እንደሚቀጥል ዋስትና መሆኑን ነው የሚመክሩት፡
ኢትዮጵያዊነት አሰባሳቢ ማንነት በአንድ አገር ልጅነት የሚል ርዕስ የሰጡትን ዳጎስ ያለ መጽሐፍ በ2009 ዓ.ም. ለንባብ ያበቁት ለምፅዋና ለአሰብ አማካይ ቦታ በምተገኝ ጢኦ በተባለች የቀይ ባህር ዳርቻ መንደር የተወለዱት ዩሱፍ ያሲን ኢትዮጵያ ብዝኃ ማንነቶች ያለውን ሕዝቧን በሰላም አሰባስቦ ለማኖር የሚያስችል ቀመር ማፈላለጉ እንደማያቅታት ነው የሚገልጹት፡፡ የአገሪቱ ሕዝቦች ከሚያራርቅ ይልቅ የሚያስተሳስሩ ብዙ የጋራ ዕሴቶች ያላቸው መሆኑ ይህን ሥራ እንደሚያቀለው በመጥቀስ ፖለቲካዊ ቁርጠኝነቱና ሙሉ ፈቃዱ ካለ ለዚህ እንደማታንስ ነው በመጽሐፋቸው የሚተርኩት፡፡