
ከ 5 ሰአት በፊት
ብዙም ያልተለመደ ካንሰር እንዳለባት በመታወቁ ስምንት የአካል ክፍሎቿ እንዲወገድላት የተደረገች ሴት ህክምናዋን ጨርሳ ወደ ሥራዋ ተመለሰች።
በዩናይትድ ኪንግደም ዌስት ሱሴክስ ሆርሻም ነዋሪ የሆነችው ፌይ ሉዊዝ እአአ በ2023 ትርፍ አንጀቷ ላይ ዕጢ ከተገኘ በኋላ ስለቀብር ሥነ ሥርዓትቷ ዕቅድ ማውጣት ጀምራ ነበር።
“የቀዶ ህክምናዎች ሁሉ ቁንጮ” ከተባለለት ህክምና በኋላ ግን ከካንሰር ነጻ በመሆኗ ወደ ጋትዊክ አየር ማረፊያ ሥራዋ መመለስ ችላለች።
“የበሽታው ምንም አይነት ምልክት እንደሌለብኝ መስማት ለእኔ ትልቁ የገና ስጦታዬ ነበር” ብላለች።
ባለፈው ዓመት የገና በዓል ሰሞን እንደገና ወደ ሥራዋ መመለስ ስለመቻሏ እርግጠኛ እንዳልነበረች ሉዊዝ አክላ ተናግራለች።
“ሥራው በጣም ጉልበት የሚፈልግ ቢሆንም ግን የአቪዬሽን ዘርፍን እወዳለሁ። እናም ወደ ሥራየየ በመመለሴ ደስተኛ ነኝ” ስትል ለቢቢሲ ራዲዮ ሱሴክስ ተናግራለች።

የቀድሞዋ ሞዴል በአውሮፓውያኑ 2023 ነበር ህመም የጀመራት። መጀመሪያ ላይ የወር አበባ ችግር እንደሆነ ብታስብም በአልትራሳውንድ በተደረገላት ምርመራ የኦቫሪ ሲስት (የእንቁላል ዕጢ) ተገኘባት።
ችግሩን ለማስተካከል ቀዶ ጥገና ከተደረገላት በኋላ “የሚያስፈራውን ካንሰር የሚለውን ቃል ሰማሁ” ብላለች። ሴዶማይክሶማ ፕሪቶኒ (በሆድ ውስጥ ዝልግልግ የመሰለ ንጥረ ነገር እንዲከማች የሚያደርግ ያልተለመደ ዕጢ) እንዳለባት ተነገራት።
ዕጢው ተቀድዶ የካንሰር ህዋሶች በሰውነቷ ላይ በማሰራጨቱ ሉዊዝ ስምንት የአካል ክፍሎቿን እንድታስወግድ የሚያግዛት ቀዶ ህክምና ለማድረግ ተገደደች።
በቀዶ ጥገናው ላይ የሐሞት ከረጢት፣ ትርፍ አንጀት፣ ኦቫሪ፣ ማህፀን፣ የሆድ ቱቦ፣ የሆድ ዕቃዋን ጨምሮ የተወሰነውን የጉበቷን የዲያፍራም እና የዳሌዋን ክፍል ማስወገድን ያካትታል።
በዚህ ምክንያትም በየዓመቱ በህዳር ወር ምርመራ ማድረግ ትቀጥላለች።
“በሚያሳዝን ሁኔታ እያንዳንዱን ውጤት መጠበቅ የመጪዎቹን የገና በዓሌን ሊያበራው ወይም ሊያጨልም የሚችል ይሆናል። ዋናው ነገር ወደፊት መግፋት እና ተስፋ አለመቁረጥ ነው” ትላለች።
“አንዳንድ ቀናት በተስፋ መቁረጥ ውስጥ እዘፈቃለሁ። አሁን አሁን ግን የበለጠ ብሩህ ቀናትን እያገኘሁ ነው” ብላለች።

በአሁኑ ወቅት ወደ ሥራዋ ተመልሳ ‘ካንሰር ሪሰርች ዩናይትድ ኪንግደም’ለተሰኘው የእርዳታ ድርጅት ገንዘብ ማሰባሰብ ችላለች።
ለበጎ አድራጎት ድርጅት ገንዘብ ለማሰባሰብ በስታንመር ፓርክ ብራይተን በተዘጋጀው ሬስ ፎር ላይፍ የሩጫ ውድድር ላይ ተሳትፋ ውድድሩን አጠናቃለች።