በጨረታ የተሸጠው ብሉፊን ቱና

ከ 5 ሰአት በፊት

በጃፓኗ ቶኪዮ የሞተር ብስክሌት ክብደት እና ስፋት ያለው ብሉፊን የተባለ ቱና በ207 ሚሊዮን ዩን ተሸጧል።

ገንዘቡ ወደ ዶላር ሲመነዘር 1.3 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ነው።

የቶኪዮ የሱሺ (ጥሬ ዓሳ) ሬስቶራንቶች ናቸው ግዙፉን ዓሳ የገዙት። ብሉፊን ቱና እጅግ ተወዳጅ ከሆኑ ዓሳዎች መካከል ነው።

ቶዮሱ በተሰኘው የቶኪዮ የዓሳ ገበያ በየዓመቱ ጨረታ ይካሄዳል። ከዚህ ቀደም እንዲህ ያለ ውድ ዓሳ ተሽጦ አያውቅም።

ኦኖዴራ ግሩፕ የተባለው ጨረታውን ያሸነፈው ድርጅት 276 ኪሎ ግራም የሚመዝነውን ዓሳ በሬስቶራንቶቹ እንደሚሸጥ አስታውቋል። የድርጅቱ ሬስቶራንቶች

ሚሼሊን በተባለው ዓለም አቀፍ እውቅና ሰጪ ድርጅት የተመዘገቡ ናቸው።

ቱናው የተጠመደው አዎሞሪ በተባለው የጃፓን ግዛት ነው።

ከኦኖዴራ ኃላፊዎች አንዱ የሆኑት ሺንጂ ናጋዎ “ቱናው መልካም ዘመን ይዞ ይመጣል” ብለዋል ሲል ኤኤፍፒ የዜና ወኪል አስነብቧል።

ኃላፊው አክለው ቱናው የሚበሉ ሰዎች አዲሱ የፈረንጆቹ ዓመት መልካም እንዲሆንላቸው ተመኝተዋል።

ጨረታውን ያሸነፈው ድርጅት ባለፉት አምስት ዓመታት ከፍተኛ ወጪ የሚያወጣውን ዓሳ በጨረታ በመግዛት ይታወቃል።

ባለፈው ዓመት በነበረው ጨረታ 114 ሚሊዮን የን አውጥቶ ቱና መግዛቱ ይታወሳል።

በፈረንጆቹ 2019 278 ኪሎ ግራም የሚመዝን ብሉፊን ቱና በ333.6 ሚሊዮን የን መሸጡ አይዘነጋም። በወቅቱ ይህን ያህል ገንዘብ አውጥቶ ቱና የገዛው “ቱና ኪንግ” በመባል የሚታወቀው ጃፓናዊው የሱሺ ሬስቶራንት ባለቤት ኪዮሺ ኪሙራ ነበር።

ቶዮሱ የዓሳ ገበያ በ1935 ነው የተከፈተው። በዓለማችን እጅግ ግዙፉ የዓሳ ገበያ እንደሆነ ይገመታል። በየቀኑ ቱና በጨረታ የሚሸጥበት ገበያም ነው።

እሑድ በነበረው ጨረታ ቱና ብቻ ሳይሆን ሌሎች የባሕር እንስሳትም ለገበያ ቀርበው ነበር።