ይህን ቡድን ካዋቀሩ አንዱ የሆኑት ቃሲል ሱሌማይኒ ባግዳድ ውስጥ ከተገደሉ አምስት ዓመት ተቆጥሯል
የምስሉ መግለጫ,ቡድኑን ካዋቀሩት አንዱ የሆኑት ቃሲል ሱሌይማኒ ባግዳድ ውስጥ ከተገደሉ አምስት ዓመት ተቆጥሯል

ከ 6 ሰአት በፊት

በኢራን የሚደገፈው የአሳድ መንግሥት መውደቅ ‘አክሲስ ኦፍ ሬዚስታንስ’ ለሚባለው ቡድን ጥሩ ዜና አይደለም።

ይህ ጥምረት በመካከለኛው ምሥራቅ ቁልፍ ከሆኑት አንዱ ነው።

ይህን ቡድን ካዋቀሩ አንዱ የሆኑት ቃሲል ሱሌይማኒ ባግዳድ ውስጥ ከተገደሉ አምስት ዓመት ተቆጥሯል።

የኢራን ልዩ ኃይል ኮማንደር ነበሩ። ኢራን በቀጠናው ያላትን እንቅስቃሴ በመንደፍ ዋነኛው ሰውም ነበሩ።

ሱሌይማኒ ከመገደላቸው ከሦስት ወራት በፊት ለኢራን አብዩት ዘብ ምሥጢራዊ ንግግር አድርገው ነበር። “አክሲስ ኦፍ ሬዚስታንስ በቁጥርም በተግባርም የሚስፋፋበትን” መንገድ የተመለከተ ንግግር ነበር።

ይመሩት ስለነረው ኩድስ ፎርስ ንግግር አድገውም ነበር።

ከመገደላቸው አስቀድሞ “የኢራን አብዮት ዘብ ይህንን ተቃዋሚ ኃይል በቁጥርና በድርጊትም አሳድጓል። በደቡብ ሊባኖስ ከነበረው 2000 ስኩዌር ኪሎሜትር ወደ ግማሽ ሚሊዮን ስኩዌር ኪሎሜትር እንዲሸፍን ተደርጓል። ይህ የተቃውሞ ኃይል ድንበር ተሻጋሪ እንዲሆን የኢራን አብዩት ዘብ አስችሏል። ኢራቅ፣ ሶሪያ እና ሊባኖስን ማዳረስ ተችሏል” ብለዋል።

‘አክሲስ ኦፍ ሬዚስታንስ’ የተባለው የተገዳዳሪ ኃይሎች ቡድን የሱሌይማኒ ስኬት ተደርጎ ነው የሚወሰደው።

እአአ ከ1980 ወዲህ ኢራን በቀጣናው እየተስፋፋች ነው። በሊባኖስ የሺዓ ንቅናቄ አካል የሆነው ሄዝቦላህን መመሥረት ተችሏል። ይህም እስራኤልና አሜሪካን ለመገዳደር ነው።

እአአ በ2003 አሜሪካ ኢራንን ስትወር እና የአረብ ስፕሪንግ በ2011 ሲነሳ ቀጣናው በውጥረት ተሞላ።

በኢስላሚክ ስቴት የተነሳው የሱኒ አክራሪ ንቅናቄም ይጠቀሳል።

ኢራን እነዚህን አጋጣሚዎች ተጠቅማ በቀጣናው ያላትን ጫና ለማሳደግ ሞክራለች።

የኢራን አብዮት ዘብ በሶሪያ መሠማራቱና በኢራቅና ሊባኖስ ያሉት የሺዓ ታጣቂዎች ኢራን በሜድትራኒያን ድንበር እንድትስፋፋ መንገድ ከፍቷል። ወደ እስራኤል ግዛትም ቀርባለች።

በሂብሩ ዩኒቨርስቲ ኦፍ ጀሩሳሌም የሚሠራው ፕ/ር ዳንኤል ሶብልማን እንደሚለው በ2003 አሜሪካ ኢራቅን ከመውረሯ በፊት ኢራን በቀጣናው ይዞታዋ ይሰፋል የሚለው የሚታሰብ አልነበረም።

“የኢራቅ ጦርነት ኢራን ከኢራቅ፣ ከሶሪያና ከሊባኖስ ጋር እንድትተሳሰር አስችሏል። ሄዝቦላህ በሊባኖስ የኢራን ዋነኛ ስኬት ሆነ። አክሲስ ኦፍ ሬዚስታንስ መሠረቱም ይሄ ነው” ይላል።

የመን በእርስ በእርስ ጦርነት ስትናጥ መዲናዋን ጨምሮ ቁልፍ ከተሞች ለኢራን ቅርብ በሆኑ የሺዓ ታጣቆዎች እጅ ገቡ።

እስራኤልን የከበቡ ኃይሎች

በቀጣናው በዋናነት የሺዓ ቡድንና የተወሰኑ ሱኒ ቡድኖች ጥምረት ተደርጎ ነው ‘አክሲስ ኦፍ ሬዚስታንስ’ የሚወሰደው።

እንደ ሐማስና ኢስላሚክ ጂሃድ ያሉ ቡድኖች በመካከለኛው ምሥራቅ ያለውን የምዕራባውያን ጫና እና እስራኤልን ለመገዳደር ይሞክራሉ።

ይህ ቡድን የሊባኖሱ ሄዝቦላህ፣ የኢራቅ ሺዓ ታጣቂዎች፣ የየመን ሁቲ አማጽያን እና በሶሪያ የአል-አሳድ አስተዳደር ይገኝበታል። የኢራን ዋነኛ ቀጣናዊና ፖለቲካዊ መሣሪያ ነው።

የዚህ ቡድን ድጋፍ ባይኖር የአሳድ መንግሥት ቀድሞ ይወድቅ ነበር።

‘ሪንግ ኦፍ ፋየር’ ወይም የእሳት ቀለበት በሚል ይህ ቡድን እስራኤልን ከቧል።

እስራኤልና አሜሪካን በዋናነት ኢራን የምትቃወምበት መሣሪያ ነው።

በቡሽ ዘመን በአፍጋኒስታንና ኢራቅ የተጀመሩ ጦርነቶች፣ በኦባማ ዘመን የተደረሰው የኢራን የኒውክሌር ስምምነትና በሶሪያ የኢራን አብዮት ዘብ ያለው ሚና ተደማምረው ኢራን ያላትን ቀጣናዊ ቦታ አጉልተዋል።

‘አክሲስ ኦፍ ሬዚስታንስ’ የተጠናከረውም በዚህ መንገድ ነው።

የትራምፕ ብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ጆን ቦልተን እንደሚለው፣ ኢራን በዚህ ቡድን አማካይነት ወታደራዊ እንቅስቃሴዋን ለማስፋት ያደረገችው ጥረት የተሳካ ነው።

“ኢራን አክሲስ ኦፍ ሬዚስታንስ የምትለውና ሱሌይማኒ ‘የእሳት ቀለበት’ በሚል በቁድስ ፎርስ አማካይነት የጀመሩት እስራኤልን የመክበብ ጥረት ነው። በቢሊዮን ዶላር አውጥተውበታል። ሄዝቦላህ ሲመሠረት የተጀመረ ነው። ይህ ንቅናቄ ከኢራን የኒውክሌርና ባለስቲክ ሚሳዔል ግንባታ ጋር ሲደመር ስኬታቸውን ያሳያል” ይላል።

ሱሌይማኒና አጋሮቻቸው

የኢራን ተጽዕኖ

ከአምስት ዓመት በፊት ፕሬዝዳንት ትራምፕ ሱሌይማኒ እንዲገደሉ አዘዙ።

‘አክሲስ ኦፍ ሬዚስታንስ’ ላይ ጫና ያሳደረ ውሳኔ ነው።

ትራምፕ በድጋሚ ወደ ሥልጣን ሲመጡ ኢራን በሁለት አሥርታት ያልታየ መዳከም ውስጥ ናት።

ትራምፕ ፕሬዝዳንት ሳሉ ኢራን ላይ ከፍተኛ ጫና ለማሳደር ከኒውክሌር ስምምነቱ አሜሪካን አስወጥተዋል።

በኢራን ላይ ባለፉት ሰባት ዓመታት የፋይናንስ ቀውስ አስከትሏል።

ጫናው ላይ የሱሌይማኒ መገደል ኢራን በቀጣናው ያላት ተጽዕኖን አዳክሞታል።

የጋዛ ጦርነት ደግሞ ሌላ ፈተና ሆኖባታል።

የሐማስ አመራሮች መገደል፣ በጋዛ የወታደራዊ መሪዎች ግድያ፣ የሄዝቦላህ መሪ ሐሰን ናስረላህ በቤሩት መገደልና የሺዓ ቡድን መሪዎች ዒላማ መደረግ ኢራን እስራኤልን ለመገዳደር የሚያስችላትን አቅም እያዳከመ ነው።

ዶ/ር ዳንኤል እንደሚለው፣ የሄዝቦላህ ወታደራዊ አቅም መዳከም ኢራን በቀጣናው ያላትን ሚና የሚጎዳ ነው።

“ለዓመታት ሄዝቦላህ በአክሲስ ኦፍ ሬዚስታንስ ውስጥ ኃያሉ ነበር። አሁን ግን ይህ ቡድን ቀጣይነቱ ጥያቄ ውስጥ ነው። የቀጣናው ኃይል ወደ ኢራን እንዲያጋድል ቡድኑ አግዟል። አሁን ግን ሁኔታው ተቀልብሷል” ይላል።

ኢራን በቡድኑ ያላት ሚና በአሳድ መንግሥትም የሚደገፍ ነበር። የአሳድ መንግሥት መውደቅ ቡድኑንና ኢራንን የሚያዳክም ነው።

የደኅንነት አማካሪው ጆን “ማንም ያልጠበቀው የአሳድ መውደቅ ለኢራን ኪሳራ ነው። ሄዝቦላህ ከኢራን ሚሳዔልና ሌላም መሣሪያ የሚያስተላልፍበት መንገድም ያጣል። በእስራኤል ጫና ውስጥ ያለው ሄዝቦላህ የአቅርቦት እጥረት ይገጥመዋል” ይላል።

ሐሰን ናስረላህ በእስራኤል ጥቃት የተገደሉበት ቦታ
የምስሉ መግለጫ,ሐሰን ናስረላህ በእስራኤል ጥቃት የተገደሉበት ቦታ

የቡድኑ ቀጣይ እጣ ፈንታ

ኢራን በዚህ ቡድን የነበሯትን ኮማንደሮችና መሪዎች አጥታለች። ከአጋሮቿ ጋር የሚኖራትን ቀጣናዊ ግንኙነትም ጥያቄ ውስጥ ወድቋል።

ኢራን በእስራኤልና በአሜሪካ ላይ ጥቃት ለማድረግ የሚኖራት ቡድን የኢራቅ ሺዓ ታጣቂዎችና የየመን ሁቲ አማጽያን ናቸው።

ኢራን በሶሪያና በሌሎችም የቀጣናው ግጭቶች በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር አፍስሳለች። በአንድ ወቅት በአካባቢው ኃያል የነበው ‘አክሲስ ኦፍ ሬዚስታንስ’ አሁን እጣ ፈንታው አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል።

ትራምፕ ሥልጣን ሲይዙ በአሜሪካና በኢራን መካከል ስምምነት ካልተደረሰ ትራምፕ ለኢራን ከቻይና እና ኢራቅ የሚሄደውን ነዳጅ ለመግታት ዝተዋል።

የሺዓ ታጣቂዎችን እንደሚያስወግዱም ተናግረዋል።

የኢራን መሪ አያቶላህ አሊ ካሚኒ “በተገዳዳሪ ኃይሉ ላይ ጫና ባሳደራችሁ ቁጥር የበለጠ ታነሳሱናላችሁ። የአክሲስ ኦፍ ሬዚስታንስ እንቅስቃሴ ከመቼውም በላይ በቀጣናው ይሰፋል” ሲሉ በቅርቡ ተናግረዋል።

ኢራን በቡድኑ ያጣችውን ቦታ መልሳ ለመያዝ ያላትን ውጥን ጠቁመዋል።

በእስራኤል ጦር የቀድሞ ስለላ ባለሙያ የነበው ኢብራሂም ሌቪን እንደሚለው፣ ቡድኑ የበቀል ስሜቱ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው አሁን ነው።

መሪዎቹ ቀድሞ የነበራቸው ይዞታ መልሶ ለማግኘት ሙከራም ያደርጋሉ።

“ሶሪያን ቢያጡም ኢራን ወደ ሶሪያ የሚወስዳትን መንገድ ለማደስ ትሞክራለች። የአሳድን መንግሥ የጣለው የኤችቲኤስ መሪ በሶሪያ እንዲንቀሳቀሱ እንዲፈቅድ ሊጠይቁ ይችላሉ” ይላል።

“በመካከለኛው ምሥራቅ ፖለቲካ ሁነኛ ወቅት ነው። የእስራኤልና ፍልስጤም ግጭትን ለመፍታት ዕድል ይኖር ይሆናል። ፖለቲከኞች የጦርነቱን ዳፋ ተረድተው አማራጭ በመፈለግ ቀጣናውን ወደተሻለ ሁኔታ መውሰድ መቻል አለባቸው” ሲል ባለሙያው ያስረዳል።