
ከ 5 ሰአት በፊት
መንግሥታዊው የሩሲያ ጋዜጣ ኢዝቨስቲያ ሪፖርተር በዩክሬን ጥቃት መገደሉን ሩሲያ አስታወቀች።
ጋዜጠኛው የተገደለው ሩሲያ በተቆጣጠረቻት በዩክሬን ምስራቃዊዋ ግዛት ዶኔትስክ ነው።
ሩሲያ የዩክሬን ጦር ጋዜጠኛውን አሌክሳንደር ማርቴምያኖቭን አነጣጥሮ ገድሎታል ስትል ወንጅላለች።
ዩክሬን ጥቃቱን በተመለከተ እስካሁን የሰጠችው አስተያየት የለም።
ሪፖርተሩን የጫነ የሲቪል መኪና በድሮን ጥቃት እንደተፈጸመበት ኢዝቪስቲያ ጋዜጣ አስታውቋል።
በዚሁ ጥቃት ሌሎች አራት የሚዲያ ሰራተኞች መቁሰላቸው ተነግሯል።
“የዩክሬን ጦር የኢዝቨስቲያ ጋዜጠኛ የሆነውን አሌክሳንደር ማርተምያኖቭን የጫነ የሲቪል መኪና ላይ የድሮን ጥቃት ፈጽሟል” ሲል ጋዜጣው በቴሌግራም ቻናሉ ላይ ዘግቧል።
ተሽከርካሪው ላይ ጥቃት በተፈጸመበት ወቅት ሩሲያ በተቆጣጠረቻት ሌላኛዋ የዩክሬን ግዛት ሆርሊቭስካ የነበረን ውጊያ ጋዜጠኛው ዘግቦ እየተመለሰ እንደነበር የሩሲያ የመንግሥት የዜና አገልግሎት ሪያ አስነብቧል።
- በመሬት መንቀጥቀጥ ወቅት ምን አይነት ጥንቃቄ ልናድርግ ይገባል?ከ 6 ሰአት በፊት
- እስራኤልና አሜሪካን የሚገዳደረው በኢራን የሚመራው ቡድን በቀጣይ ምን ይጠብቀዋል?ከ 6 ሰአት በፊት
- ‘የአምባገነኗ’ ዮዲት ጉዲት ታሪክን የሚዳስሰው የባና ደስታ የድምፅ ድራማ4 ጥር 2025
ሁለት የሪያ ዘጋቢዎች እንዲሁም ብሎክኖት ዶኔትስክ የተባለ የዜና ወኪል ሁለት ጋዜጠኞች በተሽከርካረው ውስጥ የነበሩ ሲሆን እነሱም በተፈጸመባቸው ጥቃት እንደተጎዱ እና ህክምና ላይ እንደሆኑ ተዘግቧል።
አሌክሳንደር ማርቴምያኖቭ በኢዝቨስቲያ ጋዜጣ ከአውሮፓውያኑ 2014 ጀምሮ የሰራ ሲሆን ባለፈው ዓመትም በዩክሬን የድሮን ጥቃት ቆስሎ ነበር። ከዚህ ጉዳት ካገገመ በኋላ ወደ ስራ መመለሱን ጋዜጣው ዘግቧል።
የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማሪያ ዛካሮቫ ድርጊቱን “ሆን ተብሎ የተፈጸመ ግድያ” ሲሉ ፈርጀውታል። የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ መንግሥት ከሚፈጽማቸው “ደም አፋሳሽ ወንጀሎች ውስጥ አንደኛው አሰቃቂ ጥሰት” ሲሉ ቃል አቀባይዋ አውግዘዋል።
የአውሮፓ ህብረት ኢዝቨስቲያ እና ሪያን ጨምሮ በርካታ የሩሲያ ሚዲያዎችን “የሩሲያን ፕሮፓጋንዳን በማዛመት እና የዩክሬኑን ወረራ በመደገፍ” ወንጅሎ አግዷቸዋል።
አሌክሳንደር ከመገደሉ በፊት ዓለም አቀፉ የጋዜጠኞች ፌዴሬሽን ሩሲያ በዩክሬን የፈጸመችውን ወረራ ተከትሎ ቢያንስ 21 ዩክሬናውያን ጋዜጠኞች መገደላቸውን አስታውቆ ነበር።