ልጇን ይዛ ጠረጴዛ ስር የተሸሸገች ሴት

ከ 6 ሰአት በፊት

በኢትዮጵያ ባለፉት ወራት በተለይ በአዋሽ ፈንታሌ አካባቢ በየቀኑ ተደጋጋሚ የመሬት መንቀጥቀጥ እየተከሰተ ነው።

በአዋሽ ተፋሰስ አካባቢ በሚገኙ ሠፍራዎች የመሬት መሰንጠቅ ተከስቷል። ዶፈን በተባለው ተራራ ላይ ደግሞ መሬት ፈንድቶ ጋዝ እና ድንጋይ ሲተፋ ታይቷል። በበርካታ ሥፍራዎች ፍል ውሀ እየፈለቀም ይገኛል።

በተለይ በአዋሽ፣ መተሐራ እና አቦምሳ አካባቢዎች የሚከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ ንዝረቱ በአዲስ አበባ እና በሌሎች ከተማዎች እየተሰማ ይገኛል።

ባለፈው አርብ ለሊት በሬክተር ስኬል 5.8 የሆነ ከመካከለኛ ከፍ ያለ ርዕደ መሬት ተከስቷል።

የኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ኢንስቲትዩት ተመራማሪዎች በንዝረቱ ምክንያት የተደናገጡ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች “እንዲረጋጉ” ጠይቀዋል።

በአፋር እና ኦሮሚያ ክልል የመሬት መሰንጠቅ እና መፈንዳት ባጋጠመባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ከሥፍራው አንስቶ ወደ ጊዜያዊ መጠለያ የመውሰድ ሥራ እንደተሰራ መንግሥት አስታውቋል።

ለመሆኑ የመሬት መንቀጥቀጥ አሊያም ንዝረት ሲከሰት ምን ልናደርግ ይገባል?

ምን ሊከሰት ይችላል?

የመሬት መንቀጥቀጥ ለመገመት እጅግ ከባድ ከሆኑ ተፈጥሯዊ ክስተቶች አንዱ ነው።

በመሬት መንቀጥቀጥ ወቅት ሕንፃዎች ሊጎዱ አሊያም ሊፈርሱ ይችላሉ። በተለይ በመስታወት የተገነቡ መስኮቶች ተሰባብረው የመውደቅ እና ሰዎች ላይ ጉዳት የማድረስ ዕድላቸው ከፍ ያለ ነው።

ሌላው በመሬት መንቀጥቀጥ ወቅት ሊከሰት የሚችል የጋዝ እና ቆሻሻ ማስተላለፊያ ቱቦዎች መፈንዳት ነው። በተጨማሪም አስፈላጊው መከላከያ ያልተደረገላቸው የኤሌክትሪክ ገመዶችና እንጨቶች ሊጎዱ ይችላሉ።

ከፋብሪዎች የሚወጡ ለጤና ጎጂ የሆኑ ኬሚካሎች በመሬት መንቀጥቀጥ ወቅት ሊጋለጡ ይችላሉ። ይህ ደግሞ በአካባቢው በሚኖሩ ሰዎቸ ላይ ጉዳይ የማስከተል አቅም አለው።

በዚህ ተፈጥሯዊ ክስተት ምክንያት የግንኙነት መስመር፣ የትራንስፖርት አገልግሎት እና የውሀ አቅርቦትም ሊቋረጥ ይችላል።

ምን ማድረግ አለብን?

የዘርፉ ባለሙያዎች የመሬት መንቀጥቀጥ አሊያም ከፍተኛ ንዝረት ሲከሰት “ቤት ውስጥ ከሆናችሁ በፍጥነት ከለላ ፈልጉ” ይላሉ። በቀላሉ የማይሰበር ጠረጴዛ ካለ መንቀጥቀጡ እስኪያባራ እዚያ ሥር መከለል ይመከራል። ካልሆነ ደግሞ ጭንቅላታችሁን በክርናችሁ ሸፍናችሁ ያላችሁበት ቤት ጥግ ላይ መሸሸግ ይመከራል።

ጋዝ ካለበት፣ ከመስታወት፣ ከበር እና ከግድግዳ ውጭኛው ክፍል በአጠቃላይ ሊወድቁ ከሚችሉ ቁሶች አካባቢ መራቅ ይመረጣል። ለምሳሌ ጣራ ላይ ከተሰቀለ አምፖል ራቅ ማለት ይመከራል።

አልጋ ካሉ ደግሞ እዚያው እንዲሆኑ ይመከራል። ጭንቅላትዎን በትራስ ይከላከሉ። ነገር ግን ከአልጋው በላይ ከበድ ያለ መብራት ካለና ወደቅ አደጋ ሊፈጥር የሚችል ከሆነ ቀረብ ወዳለና ከለላ ወዳለው ቦታ በፍጥነት ይሻገሩ።

አሳንሰር የተገጠመለት ሕንፃ ውስጥ የሚኖሩ ከሆነ በፍፁም እንዳይጠቀሙት።

በመሬት መንቀጥቀጥ ወቅት ውጭ ካሉ ከሕንፃዎች፣ የኤሌክትሪክና ስልክ ገመዶች እንዲሁም ከመንገድ መብራቶች ይራቁ።

ገላጣ ሥፍራ ላይ ካሉ መንቀጥቀጡ እስኪያባራ እዚያው ይሁኑ። ትልቅ አደጋ ሊኖር የሚችለው ሕንፃዎች አካባቢ ነው። በተለይ በሕንፃ መውጫና እና መግቢያ አካባቢ መሆን አይመከርም።

እየተንቀሳቀሰ ያለ ተሽከርካሪ ውስጥ ከሆኑ በተቻለ ፍጥነት አቁመው እዚያው ተሽከርካሪ ውስጥ ይሁኑ። ቢቻል ሕንፃዎች አካባቢ፣ ዛፎች አጠገብ እና የኤሌትሪክና ሌሎች ገመዶች ባለቡት ሥፍራ ባያቆሙ ይመረጣል።

የመሬት መንቀጥቀጡ ካባራ በኋላ ክብሪት መለኮስ አይመከርም። ምክንያቱም መንቀጠቀጡ ጋዝ ላይ አደጋ አድርሶ ከሆነ እሳት ሊፈጥር ይችላል። መንቀጥቀጡ ከፍተኛ ከሆነ እና ፍርስራሽ ካለ አፍና አፍንጫን በመሀረብ መሸፈን ይመከራል።

ብዙውን ጊዜ የመሬት መንቀጥቀጡ ከፍ ያለ ከሆነ ከዋናው መንቀጥቀጥ ቀጥሎ አነስተኛ የሚባሉ ንዝረቶች ይከተላሉ። እኒህ ክስተቶች “አፍተርሾክ” ይባላሉ።

የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ባለባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎች ለአደጋ ጊዜ የሚሆን ምግብና መጠጥ ቢያዘጋጁ ይመረጣል።

አዋሽና አካባቢዎቹን የሚያሳይ ካርታ

የመሬት መንቀጥቀጥ እንዴት ይከሰታል?

መሬት የተዋቀረችው በሦስት ንብርብሮች ነው። የመሬት ማዕከላዊው ክፍል ‘ኮር’ ይባላል። ቀጥሎ የሚገኘው ‘ማንትል’ ነው። በመቀጠል ‘ክረስት’ ይመጣል። ይህ በዓይናችን የምናየው የመሬት ክፍል ነው።

ክረስት እና የማንትል የላይኛው አካል ቴክቶኒክ ፕሌትስ ከተባለው ድንጋይ የተሠሩ ናቸው።

‘ቴክቶኒክ ፕሌትስ’ ዝግ ባለ መልኩ ሁሌም ይጓዛሉ። በዚህ መካከል ግጭት እና መተፋፈግ ይፈጠራል። ይህ ነው የመሬት መንቀጥቀጥ ሆኖ በመሬት ገጽ ላይ ያሉ አካላትን የሚነቀንቀው እና የሚያፈራርሰው።

በቀላል አገላለጽ በዓይናችን ከምናየው መሬት በታች ያሉት ንብርብር አለቶች በተቃራኒ አቅጣጫ እየተጓዙ እርስ በርስ ሲተፋፈጉ አሊያም ሲፋጩ መሬት ትንቀጠቀጣለች ማለት ነው።

‘ቴክቶኒክ ፕሌትስ’ በየዓመቱ በጥቂት ሴንቲ ሜትሮች እንቀስቃሴ ያደርጋሉ። እነዚህ መሬት የተዋቀረችባቸው አለቶች በተለያየ አቅጣጫ ነው የሚንቀሳቀሱት። ፍጥነታቸውም የተለያየ ሊሆን ይችላል።

አንዳንድ አለቶች እርስ በርስ ተፋፍገው ሊያልፉ ይችላሉ። ሌላ ጊዜ ደግሞ አንዱ ክፍል ከሌላኛው እየራቀ ሊሄድ ይችላል። እርስ በርስም የሚጋጩ አሉ።

በተለያየ አቅጣጫ የሚጓዙ ድንጋዮች ሲተፋፈጉ ርዕደ መሬት ያስከትላሉ። በመተፋፈጉ መካከል የሚከሰተው ኃይል ከፍተኛ ስለሆነ የመሬት ማዕበል ይፈጥራል።

የመሬት መንቀጥቀጥ የባሕር ጠለል ላይ ሲከሰት ደግሞ ከፍተኛ ማዕበል ይፈጠራል። ሱናሚ የሚባለውም ይህ ነው።

በዓለማችን በየቀኑ በሺዎች የሚቆጠሩ የመሬት ነውጦች ይመዘገባሉ። አብዛኛዎቹ ዝቅተኛ የሚባሉ እና በተለየ ቴክኖሎጂ የሚለዩ ናቸው። በጣም ከፍተኛ የሚባሉት ደግሞ ከተሞችን የማፈራረስ አቅም አላቸው።

ርዕደ መሬት የሚለካው እንዴት ነው?

ርዕደ መሬት የሚለካው የአፍታ መጠን መለኪያ በሚባል መስፈርት ነው።

2.5 ወይም ከዚያ ያነሰ መንቀጥቀጥ ሊሰማን አይችልም። ነገር ግን በመሳሪያዎች እገዛ ሊታወቅ ይችላል።

እስከ አምስት የሚደርሱ መንቀጥቀጦች የሚታወቁ ቢሆንም የሚያደርሱት አነስተኛ ጉዳት ነው። በቱርክ የደረሰው ርዕደ መሬት 7.8 ሲሆን፣ ትልቅ በሚባለው ደረጃ ውስጥ ተካቷል።

በዚህም ምክንያት በሺዎች የሚቆጠሩ ሕንጻዎችን ወደ ፍርስራሽነት በመቀየር፣ አስካሁን ከ10 ሺህ በላይ ነገር ግን ቁጥሩ በየደቂቃው የሚጨምር ሕይወትን በመቅጠፍ አሁን እንደተፈጠረው ዓይነት ከፍተኛ ጉዳትን ያስከትላል።

በርዕደ መሬት መለኪያ ከ8 በላይ የሚመዘገብ ነውጥ አስከፊ ጉዳት ያስከትላል። በዚህም የመሬት መንቀጥቀጡ የተከሰተበት ማዕከላዊው ስፍራ እና በአቅራቢያው የሚገኙ ግንባታዎችን እና ሰዎችን ሙሉ በሙሉ ሊያጠፋ ይችላል።

እአአ በ2011 በጃፓን የባሕር ዳርቻ የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ በሬክተር ስኬል 9 ሆኖ ተመዝግቧል። ምድር ላይ ሰፊ ውድመት ከማስከተሉም በላይ ተከታታይ ግዙፍ ሱናሚዎችንም ፈጥሯል።

አንደኛው ሱናሚም በባሕህር ዳርቻው የኒውክሌር ጣቢያ ላይ ትልቅ አደጋ አስከትሏል።

አስካሁን ከተመዘገቡት ሁሉ ከፍተኛው የመሬት መንቀጥቀጥ 9.5 ሲሆን በ1960 በደቡብ አሜሪካዊቷ አገር ቺሊ ውስጥ የተከሰተው ነበር