
ከ 8 ሰአት በፊት
በቻይና ተራራማ አካባቢ ማክሰኞ ማለዳ በደረሰ ከባድ የመሬት መንቀጥቀጥ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 95 ደርሷል። በተጨማሪም 130 ጉዳት እንደደረሰባቸው የቻይና መንግሥት የመገናኛ ብዙኃን ዘገቡ።
በቲቤት ቅዱስ በምትባለው ሺጋቴሴ ከተማ በአገሩ ሰዓት አቆጣጠር ጠዋት ሦስት ሰዓት አካባቢ የደረሰው ርዕደ መሬት በሬክተር ስኬል 7.1 መጠን ያለው ሲሆን፣ 10 ኪሎ ሜትር ጥልቀት እንደነበረው የአሜሪካ የጂኦሎጂካል ሰርቬይ መረጃ ያሳያል።
ጉዳትን ካደረሰው የመሬት መንቀጥቀጥ በኋላ በአካባቢው ከ40 በላይ ተከታታይ ንዝረቶች መሰማታቸው ተዘግቧል።
የመሬት ነውጡ የፈጠረው ንዝረት የቻይና አጎራባች በሆኑት በኔፓል እና በተወሰኑ የሕንድ ግዛቶች ውስጥ ተስምቷል።
አደጋው የደረሰበት የቻይና ክፍል በተደጋጋሚ የመሬት ነውጥ የሚከሰትበት ሲሆን፣ አካባቢውም ከፍተኛ ሥነ ምድራዊ እንቅስቃሴዎች የሚታዩበት መሆኑ ተነግሯል።
በመሬት መንቀጥቀጡ የተመታችው ሺጋትሴ በቲቤት ከሚገኙ የቡድሃ ዕምነት ቅዱሳን ከተሞች አንዷ ነች። ከዳላይ ላማ ቀጥሎ ቡድሂዝም ሃይማኖት ከፍተኛው መሪ የሆነው የፓንቸን ላማ መቀመጫ የሆነችው ከተማዋ በአደጋው ጉዳት ደርሶባታል።
- በኦባማ የዓመቱ ምርጥ መጻሕፍት ዝርዝር ውስጥ የተካተተው ዲናው መንግሥቱ ማነው?7 ጥር 2025
- በተለያዩ ሀገራት የሚገኙ ኦሮቶዶክስ ክርስትያኖች የገና በዓልን እንዴት እንደሚያከብሩ የሚያሳዩ ፎቶዎችከ 9 ሰአት በፊት
- ራሳችንን ከአደገኛ የምግብ መመረዝ እንዴት መጠበቅ እንችላለን?7 ጥር 2025
የቻይና መንግሥት መገናኛ ብዙኃን የመሬት መንቀጥቀጡ 6.8 መጠን እንዳለው የዘገቡ ሲሆን፣ ነውጡም ከ1,000 በላይ ቤቶች ላይ ጉዳት መድረሱን አመልክተዋል።
ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የተሰራጩ ምሥሎች ህንጻዎች ሲፈራርሱ ያሳያሉ። እንዲሁም በርካታ ጠንካራ ንዝረቶች በተከታታይ መከሰታቸውን ገልጸዋል።
በቻይና የመሬት መንቀጥቀጥ ማዕከል ተመራማሪ የሆኑት ጂያንግ ሃይኩን “ከፍተኛ የመሬት ነውጥ ከተከሰተ በኋላ ሁልጊዜም ቀስ በቀስ የመዳከም ሂደት አለ” ሲሉ ለሲሲቲቪ ተናግረዋል።
ጉዳት ካደረሰው አደጋ በኋላ በሬክተር ስኬል መጠኑ 5 የሆነ ሌላ የመሬት መንቀጥቀጥ ሊከሰት ቢችልም “ትልቅ የመሬት መንቀጥቀጥ የመከሰቱ አጋጣሚ ዝቅተኛ ነው” ብለዋል ተመራማሪው።
የቻይና አየር ኃይል በኤቨረስት ተራራ ግርጌ በሚገኘው እና ቅዝቃዜው ከዜሮ በታች በሆነው የአደጋው ስፍራ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን (ድሮን) በማሰማራት የነፍስ አድን ሥራዎችን እያከናወነ ነው።
የመሬት መንቀጥቀጡ በመታት አካባቢ የነበረው የኤሌክትሪክ ኃይል እና ውሃ አቅርቦት በአደጋው ምክንያት ተቋርጧል።
የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ እና የተፈናቀሉ ነዋሪዎችን መልሶ ለማቋቋም ሁሉን አቀፍ ፍለጋ እና የማዳን ጥረት እንዲደረግ አዘዋል።
በጎረቤት አገር ኔፓል የመሬት መንቀጥቀጥ ንዝረት የተሰማ በሆንም ምንም ዓይነት ጉዳት ወይም ውድመት አልደረሰም ሲሉ በኔፓል በኤቨረስት አቅራቢያ የሚገኙ አንድ የአካባቢው ባለሥልጣን ለኤኤፍፒ ዜና ወኪል ተናግረዋል።
የቲቤት የመሬት መንቀጥቀጥ መከታተያ ጽህፈት ቤት ስለደረሰው ጉዳት ማጣራትን እያደረገ በመሆኑ በአደጋው በሰው ላይ የደረሰውን ጉዳት እና የንብረት ውድመት በተመለከተ ግምታዊ አሃዝ ለመስጠት እንደማይችል ለቢቢሲ ገልጿል።
የመሬት መንቀጥቀጡ የደረሰበት የቻይና ክፍል ተደጋጋሚ ነውጥ የሚከሰትብት ሥነ ምድራዊ ተፈጥሮ ያለው ሲሆን፣ ከ10 ዓመት በፊት በኔፓል ዋና ከተማ አቅራቢያ በሬክተር ስኬል 7̇.8 ጥንካሬ ባለው ርዕደ መሬት ምክንያት 9,000 የሚጠጉ ሰዎችን ሲሞቱ ከ20,000 በላይ ሰዎች ቆስለዋል።