ባክቴሪያ ቤተ ሙከራ ውስጥ ሲታይ
የምስሉ መግለጫ,ባክቴሪያ ቤተ ሙከራ ውስጥ ሲታይ

7 ጥር 2025

በቅርቡ ርዕሰ ዜናዎችን ከተቆጣጠሩ ጉዳዮች ሁለቱ ምግብ መመረዝ ወረርሽኞች ናቸው። ከሁለቱም ጀርባ ያለው ደግሞ የባክቴሪያ ኢንፌክሽን የሆነው ኢ.ኮላይ ነው።

እንደ አሜሪካ በሽታ መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከል (ሲዲሲ) ገለጻ ከሆነ በመላው ዩናይትድ ስቴትስ የሚገኙ ቸርቻሪዎች በሚሸጡት ተፈጥሯዊ ካሮት ምክንያት በኢ.ኮላይ ኢንፌክሽን አንድ ሰው ሲሞት ቢያንስ 39 ሰዎች ታመዋል።

በጥቅምት ወር ማክዶናልድ ለበርገር ከተጠቀመበት ሽንኩርት ጋር በተያያዘ በአሜሪካ በተከሰተ ተመሳሳይ ወረርሽኝ አንድ ሰው ሲሞት 34 ሰዎች ሆስፒታል እንዲገቡ ምክንያት ሆኗል።

ስለነዚህ ወረርሽኞች ምን እናውቃለን? እንዴትስ ጤንነታችንን መጠበቅ እንችላለን?

ከኢ.ኮላይ ጋር በተያያዘ ካሮት ከገበያ እንዲሰበሰብ ተደርጓል
የምስሉ መግለጫ,ከኢ.ኮላይ ጋር በተያያዘ ካሮት ከገበያ እንዲሰበሰብ ተደርጓል

ኢ. ኮላይ ምንድን ነው?

“ኢ. ኮላይ ሁላችንም አንጀት ውስጥ ይገኛል” ሲሉ የዩናይትድ ኪንግደም የኢ.ኮላይ ዋና ተማራማሪ ፕሮፌሰር ሂዩ ፔኒንግተን ለቢቢሲ ፉድ ፕሮግራም ተናግረዋል።

“አብዛኞቹ እና በመቶዎች የሚቆጠሩት የኢ.ኮላይ ዓይነቶች ወደ የተሳሳተ ቦታ ካልገቡ በስተቀር ምንም ጉዳት የላቸውም።”

መርዝ የሚያመነጩ ዝርያዎች ግን አላቸው። ከእነዚህም መካከል ኢሼሪሺያ ኮላይ O157 አንዳንዴ ኤስቲኢሲ ተጠቃሽ ነው።

በበርካታ እንስሳት በተለይም በከብቶች አንጀት እና ሰገራ ውስጥ ይገኛል። እነዚህ እና ሌሎች ዝርያዎቹ ወደ ሰዎች ሲተላለፉ ከባድ የጤና ችግሮች ያስከትላል።

የኢ.ኮላይ ኢንፌክሽኖች በአንፃራዊነት የተለመዱ ናቸው። እአአ በ2023 በአሜሪካ ናሽናል ላይብረሪ ኦፍ ሜዲሲን በተደረገ ግምት መሠረት በዓለም አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ 2.8 ሚሊዮን ክስተቶች ይመዘገባሉ።

ኢ.ኮላይ ሊገድል ይችላል?

ባለፈው ጥቅምት ከበርገር ሽንኩርት ጋር በተያያዘ አንድ ሰው ሞቷል
የምስሉ መግለጫ,ባለፈው ጥቅምት ከበርገር ሽንኩርት ጋር በተያያዘ አንድ ሰው ሞቷል

አዎ ለሞት ሊያበቃ ይችላል። በየዓመቱ በበሽታው ከሚያዙት ሰዎች ቁጥር ጋር ሲወዳደር ግን አነስተኛ ነው።

እንደ ሲዲሲ ጥናት ከሆነ በአውሮፓውያኑ ከ1982 እስከ 2002 በአሜሪካ ከ8 ሺህ በላይ ሰዎች ሲያዙ 40 ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል። በዚህ መሠረት ከ200 ክስተቶች አንድ ሞት ይመዘገባል ማለት ነው።

ታዳጊዎች እና በዕድሜ የገፉ ሰዎች ከባድ ከሆነው የኢ.ኮላይ ኢንፌክሽን ጋር ተያይዘው ለሚመጡ ችግሮች በጣም የተጋለጡ ናቸው።

ኢ. ኮላይ እንዴት ይተላለፋል?

የኢ.ኮላይ ባክቴሪያ በከብቶች፣ በበግ፣ በፍየሎች እና በአጋዘን አንጀት ውስጥ ይኖራል።

“ባክቴሪያው ካለባቸው ከብቶችን ጋር ተነካካ ነገር ስንበላ” በሽታው ይይዘናል ሲሉ ፕሮፌሰር ፔኒንግተን ተናግረዋል።

ይህ የሆነበት ምክንያት ኢ.ኮላይ በምንመገበው ምግበ በኩል በቀላሉ ወደ ሰውነታችን ስለሚገባ እና በጣም ተላላፊ በመሆኑ ነው።

የO157 ዝርያ አሜሪካ ውስጥ “የበርገር” በመባል ይታወቅ ነበር። ምክንያቱም ደግሞ አልፎ አልፎ የሚከሰቱት በርገር ከመብላት ጋር ተያይዞ ስለነበር ነው።

ፕሮፌሰር ፔኒንግተን ግን አነስተኛም ቢሆን ከብቶች ጋር የሚገናኝ ማንኛውም ምግብ አደጋ አለው ብለዋል ። “አትክልቶች ምንጭ ሊሆኑ ይችላሉ ምክንያቱም ማሳው ፍግ አግኝቶ ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ አሜሪካ ውስጥ በአፕል ጭማቂ ምክንያት ትልልቅ ወረርሽኞች አጋጥሟቸዋል ምክንያቱም አፕሉ እንስሳቱ በሚሠማሩበት ስፍራ ይወድቃሉ” ብለዋል።

ፓስቸራይዝድ ያልሆነ ወተት፣ ቅቤ እና አይብ ባክቴሪያውን የማስተላለፍ ዕድላቸው ከፍተኛ ነው። ምክንያቱም የወተት ተዋጽኦዎቹ ለንክኪ ሊጋለጡ ይችላሉ።

ባክቴሪያው ውሃ ወለድም ሊሆን ይችላል። ኢ. ኮላይ ከእንስሳት ወይም በሽታው ካለባቸው ሰዎች ጋር በመገናኘትም ሊተላለፍ ይችላል።

ኢ. ኮላይን እንዴት መከላከል ይቻላል?

እጅን በደንብ መታጠብ እና ደህንነቱ የተጠበቀ የምግብ አያያዝ ልምዶች በኢ.ኮላይ የመያዝ ዕድልን ለመቀነስ በከፍተኛ ደረጃ ሊቀንሱ ይችላሉ። አንዳንድ ምግቦችንም ማስወገድ ተገቢ ነው።

ቢል ማርለር ባለፉት ሰላሳ ዓመታት በኤ. ኮሊ፣ ሳልሞኔላ፣ ሊስቴሪያ እና ሌሎች የምግብ ወለድ በሽታዎች ለተጠቁ ተጎጂዎች ሲታገል የቆየ የምግብ ደህንነት ጠበቃ ነው።

በኔትፍሊክስ በተላለፈው ፖይዝንድ፡ ዘ ደርቲ ትሩዝ አባዎት ዩር ፉድ በተሰኘ ዘጋቢ ፊልም ላይም ተሳትፏል።

መታመም ካልፈለጉ እንዳይመገቧቸው የሚፈለጉ ምግቦችን ለቢቢሲ ተናግሯል።

ያልበሰሉ ጥሬ ቡቃያዎች ለባክቴሪያ ምቹ ናቸው
የምስሉ መግለጫ,ያልበሰሉ ጥሬ ቡቃያዎች ለባክቴሪያ ምቹ ናቸው

ጥሬ ቡቃያዎች

በደንብ በቅለው ዕድገታቸውን ያልጨረሱ እና ያልበሰሉ የተለያዩ ጥሬ ቡቃያዎች እንዳንመገብ ይመከራል።

እነዚህ በዓለም ላይ ካሉት አንዳንድ የምግብ ወለድ ወረርሽኞች ጋር ተያይዘዋል።

“ዘሮቹ ውጭ በሚበቅሉበት ጊዜ ይበከላሉ። ወደ ቤት በማስገባት በውሃ ለማጠቀብ ሲቀመጡ ለባክቴሪያ ዕድገት ጥሩ ዕድል ይፈጠርላቸዋል” ብሏል።

“በምግብ ደኅንነት ኢንዱስትሪ ውስጥ የሚሠራ እና ጥሬ ቡቃያ የሚበላ ሰው አላውቅም።”

በደንብ ያልተዘጋጀ ሥጋ

ሥጋ ሲፈጭ በላዩ ላይ ያለው ማንኛውም ባክቴሪያ ወደ ውስጠኛው ክፍል ይቀላቀላል። ለዚህም ነው ሃምበርገርን በደንብ ማብሰል የሚያስፈልገው።

አንድ ሰው በጠና እንዲታመም ለማድረግ ብዙ ባክቴሪያዎችን መውሰድ አያስፈልግም።

“አንድን ሰው ለመግደል ወደ 50 የሚጠጉ የኢ.ኮሊይ ባክቴሪያዎች በቂ ናቸው። የሚታየው የሚቀምሱት ወይም ማሽተት የሚችሉትን ነገር አይደለም። ባክቴሪያውን ለማስወገድ ሃምበርገርን በደንብ ማብሰል ብቸኛው አስተማማኝ መንገድ ነው” ይላል ማርለር።

ማንኛውንም በሽታ አምጪ ተህዋስን ለማስወገድ በርገርዎ በ69 ዲግሪ ሴልሺየስ (156 ፋህራናይት) የሙቀት መጠን እንዲበስል ማድረግ አጥብቆ ይመክራል።

ወደ ስቴክ በሚመጣበት ጊዜ በሚበስልበት ወቅት ባክቴሪያዎች ስለሚሞቱ አብዛኛውን ጊዜ የሚፈጥረው አደጋ አነስተኛ ነው።

ፍራፍሬዎች እና አትክልቶች

በአውሮፓውያኑ 2006 ከቆስጣ ጋር የተያያዘ ትልቅ የኢ.ኮላይ ወረርሽኝ ተከስቶ ነበር። በዚህም አሜሪካ ውስጥ ከ200 በላይ ሰዎች ሲታመሙ፣ አምስት የሚሆኑ ሰዎች ሞተዋል።

የባክቴሪያው ብክለት በካሊፎርኒያ ከሚገኝ የቆስጣ እርሻ ጋር የተያያዘ ነበር። የስፒናች እርሻው ባለቤት የተወሰኑ እንስሳት ነበሩት ሲሆን፣ እበታቸው በኢ.ኮላይ ተበክሎ ነበር።

ቆስጣው ተቆርጦ ወደ አንድ ተቋም ተልኮ ሦስት ጊዜ ታጠበ። በሚታጠብበት ወቅት ግን ባክቴሪያው በሌሎቹ ቆስጣዎች ላይ ተሠራጨ። በኋላም በመላው አገሪቱ ለገበያ ቀርቦ ብዙ ሰዎችን ለህመም ዳርጓል።