
ከ 5 ሰአት በፊት
ሰሜን ኮሪያ አዲስ መካከለኛ ርቀት የሚጓዝ እና ሀይፐርሶኒክ አረር የተሸከመ ባለስቲክ ሚሳኤል ሙከራ ማድረጓን አስታወቀች።
ይህ የረቀቀ ሚሳዔል በፓሲፊክ ውቅያኖስ አካባቢ ያሉ “ጠላቶችን ለመቆጣጠር ሁነኛ ነው” ብላለች።
ሰኞ ዕለት የተደረገው ሙከራ በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ የመጀመሪያው ሲሆን፣ የዩናይትድ ስቴትስ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን ለይፋ የሥራ ጉብኝት ደቡብ ኮሪያ ሳሉ የተሞከረ ነው።
ሀይፐርሶኒክ የተባሉትን ሚሳዔሎች ተከታትሎ መትቶ ለመጣል እጅግ ከባድ ሲሆን፣ እነዚህ ሚሳዔሎች ከድምፅ አምስት እጥፍ ይፈጥናል።
ሰሜን ኮሪያ አዲሱ ሚሳዔሏ ከድምፅ ፍጥነት 12 እጥፍ በላቀ ሁኔታ መጓዙን እና 1500 ኪሎ ሜትር መመዝጉን አስታውቃለች።
ደቡብ ኮሪያ በበኩሏ ባወጣችው ዘገባ ሚሳዔሉ 1100 ኪሎ ሜትር ተመዝግዝጎ ባሕር ላይ እንደወደቀ አስታውቃ፤ ይህ የፒዮንግያንግ ድርጊት “ጠብ አጫሪ እና ሊኮነን የሚገባው ነው” ብላለች።
ሰሜን ኮሪያ የሀይፐርሶኒክ ሚሳዔል ሙከራ ስታደርግ ይህ የመጀመሪያዋ አይደለም።
የኮሪያ የዜና ተቋም ኬሲኤንኤ የለቀቃቸው ምሥሎች እንደሚያሳዩት ሰኞ የተደረገው የሚሳዔል ሙከራ ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ካደረገችው ጋር ተመሳሳይነት አለው።
ነገር ግን ፒዮንግያንግ እንደምትለው አዲሱ ሀይፐርሶኒክ ሚሳዔል “አዲስ የበረራ እና የመመሪያ መቆጣጠሪያ ሥርዓት” የተዘረጋለት እንዲሁም ከካርበን ፋይበር የተሠራ ሞተር የተገጠመለት ነው።
- በተለያዩ ሀገራት የሚገኙ ኦሮቶዶክስ ክርስትያኖች የገና በዓልን እንዴት እንደሚያከብሩ የሚያሳዩ ፎቶዎችከ 9 ሰአት በፊት
- ኢየሱስ በተወለደባት ቤተልሔም እና በናዝሬት የሚገኙ ቅዱስ ስፍራዎችከ 7 ሰአት በፊት
- በቻይና 7.1 መጠን ባለው የመሬት መንቀጥቀጥ ከ50 በላይ ሰዎች ሞቱከ 8 ሰአት በፊት
የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ሰኞ ባደረጉት ንግግር “በግልፅ ተቀናቃኞቻችን ምን እያደረግን እንደሆነ ማየት ይችላሉ። ሕጋዊ የሆነ ፍላጎታችንን ለመከላከል አስፈላጊውን እርምጃ ለመውሰድ ተዘጋጅተናል” ብለዋል ሲል ኬሲኤንኤ ዘግቧል።
በካርንጌ ኢንዶውመንት ለዓለም አቀፍ ሰላም የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ባለሙያ የሆኑት አንኪት ፓንዳ አዲሱ የሚሳዔል ሙከራ “የሚያስደንቅ” አይደለም ብለዋል።
“ሰሜን ኮሪያ ላለፉት ዓመታት ከተለያዩ ቁሳቁሶች ሚሳኤል እንደምትሠራ እናውቃለን። እነዚህ ቁሳቁሶች በየጊዜው የሚሻሻሉ ከባድ ክብደት መሸከም የሚችሉ ናቸው” ሲሉ ለቢቢሲ ይናገራሉ።
ምንም እንኳ ሀይፐርሶኒክ ሚሳዔሎች ላለፉት አስርታት የነበሩ ቢሆንም፤ በቅርብ ዓመታት ግን በጣም ዘመናዊ የሆኑ ሚሳዔሎች እየተሠሩ ነው ይላል ሲኤሲኤን የተባለው የጦር መሣሪያ ጥናት ማዕከል።
ሀይፐርሶኒክ ሚሳዔሎችን መከታተል የሚቻለው ሕዋ ላይ ባሉ መሣሪያዎች ነው። ሚሳዔሎቹ በጣም ፈጣን እና ተጣጣፊ ቢሆኑም አሁን ጥቅም ላይ የሚውሉ ቴክኖሎጂዎች ሀይፐርሶኒክ ሚሳዔሎችን መከታተል ይችላሉ።
ብሊንከን በሴዑል በነበራቸው ጉብኝት ሩሲያ በጣም ዘመናዊ የሆኑ የሕዋ እና የሳተላይት ቴክኖጂዎችን ለሰሜን ኮሪያ ልታጋራ እንደሆነ አሜሪካ ታስባለች ብለዋል።
አክለውም ሞስኮው ለበርካታ ዓመታት አክብራው የነበረውን ቃል በማጠፍ ሰሜን ኮሪያ የኒውክሌር ኃያል ሀገር መሆኗን እውቅና ልትሰጥ ትችላል ሲሉ ተደምጠዋል።
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከደቡብ ኮሪያው ጊዜያዊ ፕሬዝደንት ቾይ ሳንግ-ሞክ ጋር መክረዋል። በዋሺንግተን እና በሴዑል መካከል ያለው ግንኙነት “በኮሪያ ልሳነ መድር ሰላም እና መረጋጋት ለማምጣት ያለመ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
የደቡብ ኮሪያ ጦር ሠራዊት በሰሜን ኮሪያ በኩል የሚደረጉ የሚሳዔል ሙከራዎችን “በቅርበት እየተከታተለ” መረጃዎችን ለአሜሪካ እንደሚያጋራ አስታውቋል።
ደቡብ ኮሪያ በሀገር ውስጥ ፖለቲካዊ ውጥንቅጥ ውስጥ ትገኛለች። ከሥልጣናቸው የተወገዱት ፕሬዝደንት ዩን ሱክ የዎል ወታደራዊ ሕግ መደንገጋቸውን ተከትሎ ነው ይህ የሆነው። ፕሬዝደንቱ የእስር ማዘዣ ወጥቶባቸዋል።
በዓለማችን እጅግ ጨቋኝ አገዛዝ ያላት ሰሜን ኮሪያ የታገዱትን ፕሬዝደንት ድርጊት “እብደት የታከለበት” ነው ስትል ኮንናለች።