
7 ጥር 2023
ተሻሽሏል 7 ጥር 2025
አውሮፓ እና አሜሪካንን ጨምሮ በርካታ የዓለም አገራት ክርስቲያኖች የገና ወይም የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓልን የሚያከብሩት ከዘመን መለወጫቸው አንድ ሳምንት ቀደም ብሎ ታኅሣሥ አጋማሽ ላይ ነው።
ከአፍሪካ ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ እና ግብፅ እንዲሁም የተወሰኑ ሌሎች የአውሮፓ አገራት ግን የገና በዓልን ዛሬ (ታኅሣሥ 29) እያከበሩ ይገኛሉ።
እነዚህን አገራት የሚያመሳስላቸው አንድ ጉዳይ በርካታ የኦርቶዶክስ ሃይማኖት እምነት ተከታይ ስላላቸው ሲሆን፣ ሌላኛው ደግሞ የሚከተሉት የዘመን አቆጣጠር ነው።
ከአፍሪካ፤ በኢትዮጵያ፣ በኤርትራ እና በግብፅ (በተለይ የኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን እምነት ተከታዮች) ያሉ ክርስትያኖች ገናን በየዓመቱ ታኅሣሥ 29 (በአራት ዓመት አንድ ጊዜ ደግሞ ታኅሣሥ 28) ያከብሩታል።
የገናን በዓል ቀደም ብለው የሚያከብሩት አብዛኞቹ ምዕራባውያን አገራት እና ሌሎችም የግሪጎሪን የቀን አቆጣጠር ቀመርን የሚከተሉ ናቸው። የቀን አቆጣጠሩ የተፈጠረው በ1582 በሊቀ-ጳጳስ ግሪጎሪ ነበር።
እንዲሁም አብዛኞቹ የቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት አካል የነበሩ አገራት፣ የምሥራቅ አውሮፓ እንዲሁም የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ደግሞ በጁሊየስ ቄሳር የተፈጠረውን የጁሊያን የዘመን አቆጣጠር የሚከተሉ ናቸው።
በተጨማሪም በርካታ አገራት በይፋ የሚገለገሉበትን የዘመን አቆጣጠር የግሪጎሪያውያኑን አድርገው፣ ለአገር አቀፍ በዓላት ግን የጁሊያንን የዘመን ቀመርን የሚጠቀሙም አሉ።

ታኅሣሥ 29 ገናን የሚያከብሩት እነማን ናቸው?
አብዛኛው ዓለም የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓልን ካከበረ ከሁለት ሳምንት በኋላ ጥቂት የማይባሉ አገራት በዓሉን ዛሬ ታኅሣሥ 29/2017 ዓ.ም. እያከበሩ ይገኛሉ።
ናሽናል ጂኦግራፊክ እንደሚለው በዓለም ላይ ካሉ የክርስትና እምነት ተከታዮች መካከል ከ12 በመቶው የሚልቁት ክርስቲያኖች የልደት በዓልን ከቀሪው ዓለም በተለየ ቀን ያከብራሉ።
ከሌሎች የእምነቱ አጋሮቻቸው በተለየ የገና በዓልን ታኅሣሥ 29 በየአራት ዓመቱ ደግሞ ታኅሣሥ 28 የሚያከብሩት እነዚህ አገራት እነማን ናቸው?
- ኢትዮጵያ
- ኤርትራ
- ግብፅ
- ሩሲያ
- ዩክሬን
- ቤላሩስ
- ካዛኪስታን
- ሰርቢያ
- ሞንቴኔግሮ
- እስራኤል
- ቡልጋሪያ
- መቄዶኒያ
- ጆርጂያ
- ሞልዶቫ
ዛሬ የኢየሱስ ክርስቶስን ልደት በዓልን እያከበሩ የሚገኙ አገራት ናቸው።
በግሪክ፣ በቆጵሮስ እና በሩሜኒያ የሚገኙ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ግን የኢየሱስ ክርስቶስን የልደት በዓል ያከበሩት በግሪጎሪያን የዘመን አቆጣጠር ከሁለት ሳምንት በፊት ነው።
በተጨማሪም ከሌሎቹ በተለየ ሁኔታ አርሜኒያ ገናን በራሷ የቀን አቆጣጠር በተለየ ቀን ነው የምታከብረው። አርሜኒያ ገናን ታኅሣሥ 28 (በአራት ዓመት አንዴ ደግሞ ታኅሣሥ 27) ታከብራለች።

የኢትዮጵያ ገና ለምን ታኅሣሥ 29 ይከበራል?
ኢትዮጵያ የራሷ የዘመን አቆጣጠር ያላት አገር ናት። ይህ የጊዜ ቀመር ከኮፕቲክ ኦርቶዶክስ እምነት ቀን አቆጣጠር ጋር ተመሳሳይነት አለው።
ልክ እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ የኮፕቲክ ኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ገናን ከምዕራቡ ዓለም በሁለት ሳምንታት ያህል ዘግይተው ያከብራሉ። የጥምቀት እና የፋሲካ በዓልን የሚያከብሩበት ቀንም ከምዕራቡ ዓለም ጋር በተመሳሳይ ልዩነት ያለው ነው።
ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የኦርቶዶክስ፣ የካቶሊክ፣ የኢቫንጀሊካል፣ እንዲሁም የጴንጤኮስታል እምነት ተከታዮች እና ሌሎች የክርስትና እምነት ተከታዮች የልደት በዓልን የሚያከብሩት በአንድ ቀን ነው።
ኤርትራ በበኩሏ ብሔራዊው የዘመን አቆጣጠሯ የግሪጎሪያውያኑን ብታደርግም የክርስትና እምነት ተከታዮች ግን የኦርቶዶክስ የዘመን አቆጣጠርን ይከተላሉ።
በዓለማችን ያሉ የኦርቶዶክስ እምነትም ሆነ የሌሎች ክርስትና ሃይማኖቶች ተከታዮች ገና ከመድረሱ በፊት ያሉትን ቀናት በፆም እንዲሁም በፀሎት ያስቧቸዋል።
የገና አከባበር ከአገር አገር የተለያየ ቅርፅ አለው። ለምሳሌ ሩሲያ ውስጥ ያሉ ክርስትያኖች ከአዲስ ዓመት መባቻ እስከ ገና ዕለት ያሉትን 7 ቀናት፣ በቀን 12 የተለያዩ ዓይነት ምግቦችን በመመገብ ያሳልፋሉ። ዓላማው ደግሞ 12ቱን ሐዋሪያት ማሰብ ነው።
ዩክሬን ውስጥ ደግሞ የበዓሉ አክባሪዎች ከቤት ቤት በመዘዋወር ዝማሬ በማሰማት ነው ቀኑን የሚያሳልፉት።
ቤላሩሲያውያን ደግሞ ለዕለቱ ቂጣ እና ዓሣ ያዘጋጃሉ። በሞንቴንግሮ ውስጡ ሳንቲም ያለበት ድፎ ዳቦ ይደፋል፤ ዳቦው ሲቆረስም የሚገኘው ሳንቲም መልካም ዕድል ይዞ እንደሚመጣ ያስባሉ።
በሰርቢያ ውስጥ ገና የሚዘከረው ልክ እንደ ቡሄ ከጫካ ዛፍ ተቆርጦ ከተሰበሰበ በኋላ እሱን በማቃጠል በዙሪያው ተሰብስቦ እራት በመብላት ነው። ጆርጂያውያን ደግሞ ወደ አውራ ጎዳናዎች በመውጣት የኢየሱስ ክርስቶስን ልደት ይዘክራሉ።
በኢትዮጵያም ቢሆን የበዓሉ መሠረት አንድ ቢሆንም አከባበሩ ከቦታ ቦታ ይለያያል። የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ተከታዮች ከገና በፊት የጾም የሳምንታትን የሚያሳልፉ ሲሆን በበዓሉ ዕለት ጾሙ ይፈታል።
ነገር ግን አብዛኛው የክርስትና እምነት ተከታይ ምዕመን በዓሉን ወደ ቤተ እምነቶች በመሄድ፤ የጸሎት ሥነ ሥርዓቶችን በመታደምና በቤት ውስጥ በጋራ ማዕድ በመቁረስ ያከብረዋል።
በዓሉን ለምታከብሩ መልካም የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በዓል ይሁንላችሁ!