
ከ 8 ሰአት በፊት
አንዲት የጣልያን መንደር ነዋሪዎቿ በጠና እንዳይታመሙ ከለከለች።
ቤልካስትሮ የተሰኘችው መንደር ነዋሪዎች “አስቸኳይ የህክምና እርዳታ ከሚያስፈልገው ማንኛውም በሽታ እንዳይያዙ” መመሪያ እንደተላለፈላቸው የአካባቢው ከንቲባ አንቶኒዮ ቶርቺያ ተናግረዋል።
ቤልካስትሮ በደቡባዊ ካላብሪያ የምትገኝ እና አነስተኛ እና ድሃ ከሆኑ መንደሮች አንዷ ናት።
ከንቲባው መመሪያው “ግልጽ በሆነ መልኩ ቀልድን የተላበሰ እርምጃ” መሆኑን ገልጸው ነገር ግን የአካባቢው የጤና አጠባበቅ ስርዓት ጉድለቶች ለመሸፈን ለክልሉ ባለስልጣናት ከላኩት አስቸኳይ ድንጋጌዎች የበለጠ ውጤት እያመጣ መሆኑን አልካዱም።
ከቤልካስትሮ 1 ሺህ 200 ነዋሪዎች መካከል ግማሽ ያህሉ ዕድሜያቸው ከ65 ዓመት በላይ ሲሆን በአቅራቢያቸው ያለው የአደጋ እና የድንገተኛ የጤና ማዕከል 45 ኪሎሜትር ይርቃል ብለዋል ከንቲባው።
ይህ የጤና ማዕከልን መድረስ የሚቻለው በመኪና ብቻ ሲሆን መንገዱም በሰዓት ከ30 ኪሎሜትር ፍጥነት በላይ አይነዳበትም።
- በትግራይ ወርቅ ለማውጣት የሚውሉ አደገኛ ኬሚካሎች የደቀኑት ከባድ አደጋከ 9 ሰአት በፊት
- ሥልጣን የለቀቁት የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶን ማን ሊተካ ይችላል?ከ 9 ሰአት በፊት
- አርቴታ ለክለቡ ሽንፈት ‘አስቸጋሪ እና በጣም ይበራል’ ሲል ኳሱን ተጠያቂ አደረገከ 8 ሰአት በፊት
የመንደሯ የቀዶ ህክምና ባለሙያ አልፎ አልፎ የሚመጡ ሲሆን ቅዳሜና እሁድ፣ በበዓላት እና ከስራ ውጭ ባሉ ሰዓታት አገልግሎት አይሰጡም።
ከንቲባው ለጣሊያኑ ቴሌቪዥን እንደተናገሩት ነዋሪዎች አስቸኳይ የህክምና እርዳታ ከፈለጉ ብቸኛው አማራጭ በሰዓቱ ወደ ማዕከሉ መድረስ ሲሆን ነገር ግን መንገዱ “ከህመሙ በበለጠ አደጋ ውስጥ የሚከት ነው” ብለዋል።
መመሪያው በተጨማሪ ነዋሪዎች “በቤት ውስጥ አደጋ ሊያጋልጣቸው ከሚችሉ ባህርያት እንዲቆጠቡ እና ብዙውን ጊዜ ከቤት እንዳይወጡ፣ ጉዞዎችንም ሆነ አካላዊ እንቅስቃሴዎችን እንዳያደርጉ እና አብዛኛውን ጊዜ ጊዜያዎችን በእረፍት እንዲያሳልፉ” ይላል።
እነዚህ መመሪያዎች የሚተገበሩ ከሆነ በምን መልኩ እንደሆነ ግልጽ አይደለም።
በርካታ ህዝብ የማይኖርበት የካላብሪያ ግዛት በጣልያን ድሆች ከሆኑት ስፍራ አንዱ ነው።
የአካባቢው ብልሹ አስተዳደር፣ የፖለቲካ ችግር እና የማፍያ ስርዓት መንሰራፋት የአካባቢውን የጤና አጠባበቅ ስርዓት አፈራርሶታል። ከዚህም ጋር ተያይዞ ማዕከላዊ መንግሥቱ ከ15 ዓመታት በፊት በልዩ አስተዳደር ስር አድርጎት ነበር።
በሮም የተሾሙት ኮሚሽነሮች ሆስፒታሎች የገቡበትን ከፍተኛ የዕዳ አዘቅት ለመፍታት ችግር ሆኖባቸው ቆይቷል። ግዛቲቱ የህክምና መሳሪያዎች እና በህክምና ባለሙያዎች እጥረት ለዓመታት ስትቸገር የቆየች ሲሆን በርካቶች ለረጅም ጊዜ ወረፋ ለመጠበቅ ተገደዋል።
ከአውሮፓውያኑ 2009 ጀምሮ 18ቱ የክልሉ ሆስፒታሎች ተዘግተዋል። በዚህም ምክንያት ከካላብሪያ ግማሽ ያህሉ፣ ወደ 2 ሚሊዮን የሚሆኑ ነዋሪዎች ከክልሉ ውጭ ነው የህክምና እርዳታ የሚያገኙት።
ከሶስት ዓመታት በፊት ኩባ 497 ዶክተሮችን ወደዚህችው የጣልያን ክልል ለሶስት ዓመታት ያህል አገልግሎት እንዲሰጡ ልካ ነበር። የክልሉ ገዥ ሮቤርቶ ኦቺውቶ እነዚህ ዶክተሮች የካላብሪያን ሆስፒታሎች “ታድገዋቸዋል” ሲሉ ተናግረው ነበር።