በሎስ አንጀለስ የተዛመተው የእሳት ሰደድ

ከ 5 ሰአት በፊት

የእሳት ሰደድ በከፍተኛ ሁኔታ የተዛመተባት የአሜሪካዋ ግዛት ሎስአንጀለስ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አወጀች።

እሳት ሰደዱ ከ10 ሄክታር ተነስቶ በሰዓታት ውስጥ ወደ 2 ሺህ 900 ሄክታር መዛመቱን ተከትሎ ነው ይሄ እርምጃ የተወሰደው።

የሰደዱ አደጋ የተጋረጠባቸው 30 ሺህ የሚሆኑ ነዋሪዎች አካባቢያቸውን ለቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ እንደተላለፈላቸው እና 13 ሺህ ህንጻዎች አደጋ ላይ መሆናቸውን የግዛቲቱ የእሳት አደጋ ኃላፊ ክርስቲን ክራውሌይ አስታውቀዋል።

በፓስፊክ ፓሊሴድስ አካባቢ ያሉ መኖሪያ ቤቶች በእሳት ተያይዘው እንዲሁም ነዋሪዎች መኪኖቻቸውን ትተው ሲሸሹ የሚያሳዪ ቪዲዮዎች ወጥተዋል።

እሳቱ የተነሳው ማክሰኞ በአገሬው ሰዓት አቆጣጠር ከጥዋቱ 4፡30 አካካቢ ሲሆን 80 ኪሎሜትር በሰዓት በፍጥነት በመጓዝ በከፍተኛ ሁኔታ መዛመቱ ተገልጿል።

ሁለተኛው የእሳት ሰደድ በአልታዴና ግዛት አካባቢ በፍጥነት ተያይዞ በሰዓት 40 ኪሎሜትር እየተጓዘ ነበር ተብሏል።

በካሊፎርኒያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ነዋሪዎች በከፍተኛ የእሳት አደጋ ላይ እንደሆኑ ማስጠንቀቂያ ተላልፎላቸዋል።

የእሳት ሰደዱ ቤቶችን አውድሞ፣ መንገዶችን እና አውራ ጎዳናዎችን ከጥቅም ውጭ ያደረገ ሲሆን አንዳንድ ሰፈሮች እሳት ሲያጋያቸው የሚያሳዩ ቪዲዮዎች ወጥቷል። የሎስ አንጀለስ የእሳት አደጋ በስራ ላይ የሌሉ የእሳት አደጋ ተከላካዮች ተሰማርተው እርዳታ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል።

በሎስ አንጀለስ ግዛት ቢያንስ 200 ሺህ ነዋሪዎች የመብራት አገልግሎት ተቋርጦባቸዋል። አንዳንድ ትምህርት ቤቶች በከፍተኛ ንፋስ እና መብራት መቆራረጥ ምክንያት ለመዘጋት መገደዳቸውን አስታውቀዋል።

በአጎራባች ሳን በርናርዲኖ ግዛት 13 ሺህ 600 የሚሆኑ ነዋሪዎች መብራት ተቋርጦባቸዋል። በሌሊት የሚነፍሰው ኃይለኛ ንፋስ ዛፎችን በመገንደስ፣ የኤሌክትሪክ መስመሮችን የበጣጠ ሲሆን መንገዶችም እየተዘጉ መሆናቸውን ባለስልጣናቱ አስጠንቅቀዋል።

ከዚህም ጋር ተያይዞ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከመታወጅ በተጨማሪ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የተጎዱ አካበቢዎችን ለመደገፍ የፌደራል በጀትን አጽድቀዋል።

በግዛቲቷ በተለያዩ ማዕከላት የሚገኙ አረጋውያን በዊልቸር እና በሆስፒታል አልጋዎች እንዲወጡ መደረጋቸው ተዘግቧል።

በርካታ ዊልቸሮች እና የሆስፒታል አልጋዎች በጎዳናዎች ላይ ተዘርግተው እንዲሁም በርካታ የጸጥታ ኃይሎች መኖራቸውን የቢቢሲ አጋር የሆነው ሲቢኤስ የዜና ወኪል ዘግቧል።