የነዳጅ ዋጋ ባለፉት ስድስት ወራት

ከ 3 ሰአት በፊት

የቤንዚን እና የአውሮፕላን ነዳጅ የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ለመጀመሪያ ጊዜ ከመቶ ብር ተሻገረ።

የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ማክሰኞ ምሽት፣ ታኅሳስ 29/ 2017 ዓ.ም የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ላይ ማሻሻያ መደረጉን አስታውቋል።

ማሻሻያውን ተከትሎ 91 ብር ሲሸጥ የነበረው ቤንዚን ብር 101.47 ገብቷል። በዚህም መሰረት የቤንዚን ዋጋ ለመጀመሪያ ጊዜ ከመቶ ብር ተሻግሯል።

ከታኅሳስ 29/ 2017 ዓ.ም ምሽት በተደረገው የዋጋ ማሻሻያ የአውሮፕላን ነዳጅ የችርቻሮ ዋጋም በተመሳሳይ ሶስት አሃዝ ገብቷል። የአውሮፕላን ነዳጅ አዲሱ ዋጋ ብር 109.56 ሆኗል።

ኬሮሲን እና ነጭ ናፍጣ ደግሞ የስምንት ብር ጭማሪ አሳይተው በሊትር ብር 98.29 መሸጫ ዋጋ ወጥቶላቸዋል።

ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር መጨረሻ ተግባራዊ መደረግ ከጀመረው የማክሮ ኢኮኖሚ የፖሊሲ ለውጥ ወዲህ የነዳጅ ምርቶች ላይ ማሻሻያ ሲደረግ ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።

የመጀመሪያው ማሻሻያ የተደረገው ባለፈው ጥቅምት ወር ላይ ነበር።

በጥቅምት ማሻሻያ በተደረገበት ወቅት የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር፤ “የዓለም የነዳጅ ዋጋ መነሻ በማድረግ የነዳጅ የችርቻሮ ዋጋ ማስተካከያ በየሦስት ወሩ የሚደረግ ሲሆን ለአንድ ዓመት የሚቆይ ጥቅል ድጎማ ይደረጋል” ብሎ ነበር።

ከማክሮ ኢኮኖሚ የፖሊሲ ለውጥ በኋላ በቤንዚን፣ ኬሮሲን እና ነጭ ናፍጣ ላይ የ20 ብር ገደማ ጭማሪ ተደርጓል። የአውሮፕላን ነዳጅ ደግሞ የ39 ብር ጭማሪ አድርጓል።

ባለፈው ሐምሌ ተግባራዊ በተደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም የውጭ ምንዛሬ ግብይት በገበያው አማካኝነት እንዲበየን ማድረጉ ይታወሳል። ከዚህ በተጨማሪም የገንዘብ እና የፊስካል ፖሊሲዎች ላይ ማሻሻያዎችንም አድርጓል።

መንግሥት ፕሮግራሙን ይፋ ባደረገበት ወቅት፤ “ተጋላጭ የኅበረተሰብ ክፍሎችን ለመደገፍ የሚያስችሉ ተግባራት ይከናወናሉ” ብሎ ነበር። ከእነዚህ ተግባራት መካከል የነዳጅ ዋጋ ጭማሪውን በከፊል መደጎም አንዱ ነው።

በገና በዓል ምሽት የተደረገው የነዳጅ ውጤቶች የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ሁለተኛው ዙር ሲሆን ቀጣዩ ከሶስት ወር በኋላ ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል።

ከዋጋ ማሻሻያው ሶስት ሳምንት ቀደም ብሎ በህዳር መጨረሻ የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት፤ ለአዲስ ማደያዎች ነዳጅ ላለማቅረብ መወሰኑን አስታውቆ ነበር። ድርጅቱ ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው መንግሥት ወደ ሀገር ውስጥ የሚያስገባውን ነዳጅ “ለመቀነስ እየተሰራ” በመሆኑ ነው።

ድርጅቱ ይህን ውሳኔ ያስታወቀው ለነዳጅ እና ኢነርጂ ባለስልጣን በጻፈው ደብዳቤ ነበር።

የነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ለአዲስ ማደያዎች ነዳጅ ላለማቅረብ የወሰነው “የድርጅቱ የሥራ አመራር ቦርድ ባደረገው” ስብሰባ ጉዳዩ ከመንግሥት ፖሊሲ ጋር የሚቃረን ሆኖ ስላገኘው እንደሆነ በደብዳቤው ላይ ጠቅሷል።

ከዚህ በተጨማሪም የድርጅቱ የስራ አመራር ቦርድ “መንግሥት ወደ ሀገር የሚገባውን የነዳጅ መጠን ለመቀነስ እየሰራ ባለበት ሁኔታ ለእነዚህ ማደያዎች ነዳጅ ማቅረብ ከመንግሥት ፖሊሲ አንጻር ተገቢ አለመሆኑን አቅጣጫ አስቀምጧል” ሲል ከአንድ ወር በፊት በጻፈው ደብዳቤ ውሳኔውን አስረድቷል።