በበርሚንግሃም ቦርኒቪል የሚገኘው የቅዱስ ላዛር የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን

ከ 2 ሰአት በፊት

አገሮቻቸው በጦርነት እየተፋለሙ የሚገኙት ሩሲያውያን እና ዩክሬናውያን ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደበትን የገና በዓል በድምቀት አክብረዋል።

በአንዳንድ ስፍራዎች ደግሞ ክርስቲያናዊ ቤተሰብነት ይቀድማል በሚል በአንድነት ነው ያከበሩት ነው።

በዩናይትድ ኪንግደም፣ በርሚንግሃም በሚገኝ በአንድ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የልደት በዓልን በአንድ ላይ ያከበሩት ሩሲያውያን እና ዩክሬናውያን ሰላም፣ ፍቅር እና አንድነትን በተላበሰ መልኩ ዕለቱን አስበውታል።

በበርሚንግሃም ቦርኒቪል የሚገኘው የቅዱስ ላዛር የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የተገነባው በሰርቢያን ስደተኞች ነው። ስደተኞቹ ቤተ ክርስቲያኗን የገነቡበትን መሬት በአውሮፓውያኑ 1960ዎቹ ከአንድ ቤተሰብ የገዙበት ዋጋ አንድ ፓውንድ ነበር። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ቤተ ክርስቲያኗ ለየትኛውም ማኅበረሰብ በሯ ክፍት ነው።

ሆኖም ሩሲያ በዩክሬን ላይ የፈጸመችውን ወረራ ተከትሎ ባለፉት ዓመታት ውጥረት መከሰቱ አልቀረም። ነገር ግን የቤተ ክርስቲያኗ አገልጋዮች እና ምዕመናን ለእምነታቸው ቅድሚያ በመስጠታቸው ሁኔታዎች ሳይጋጋሉ ቀርተዋል።

የቤተ ክርስቲያኗ ካህን የሆኑት አባ ኔናድ ፐፖቪድ እንደ ዕድል ሆኖ ምዕመናኑ ፖለቲካውን ወደ ቤተ ክርስቲያኗ አያመጡትም ይላሉ።

“በዚህ ስፍራ ያለን አንድ መሪ ነው እርሱም እየሱስ ክርስቶስ ነው። ሌላ ማንም የለም” ይላሉ ካህኑ።

በቤተ ክርስቲያኗ የነበሩት ራይሳ የተባሉ ምዕመንም በዚህ የሚስማሙ ሲሆን፣ ዋናው የምዕመኑ ትኩረት አምልኮ ነው ይላሉ።

“እዚህ የመጣነው ለአምላካችን ነው ስለዚህ በሌሎች ነገሮች ላይ ላለመጠመድ እንሞክራለን” ሲሉ ያስረዳሉ።

“በመዘምራን ማኅበራችን ውስጥ ዩክሬናውያን፣ ሩሲያውያን፣ ከሞልዶቫውያን እንዲሁም ከዩናይትድ ኪንግደም አሉ። ሁላችንም እዚህ የተገኘነው ለአምልኮ ነው” ይላሉ።

የቤተ ክርስቲያኗ ካህን የሆኑት አባ ኔናድ ፐፖቪድ
የምስሉ መግለጫ,የቤተ ክርስቲያኗ ካህን የሆኑት አባ ኔናድ ፐፖቪድ

‘የማይቀየረው አምላክ ብቻ ነው’

በዩናይትድ ኪንግደም ነዋሪ የሆነችው የሩሲያ ተወላጇ ኦልጋ ዌክፍልድ እምነቷ ለጦርነቱ ጥርት ያለ ዕይታ እንደሚሰጣት ትናገራለች።

“ሕይወታችን በብዙ ፈተናዎች የተሞላ ነው። መጀመሪያ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ፤ እሱም አለፈ። አሁንም በርካታ ችግሮች አሉ። ብቸኛው ቋሚው አምላክ ብቻ ነው” ትላለች።

“ይሄም ለሕይወታችን ትምህርት የሚሆን ጉዳይ ነው” ትላለች።

የቤተ ክርስቲያኗ አገልጋዮችም ሆነ ምዕመናኑ ትኩረታቸውን በፖለቲካው እና ግጭቱ ላይ ላለማድረግ ቢጥሩም ለሦስት ዓመታት ያህል ገደማ የዘለቀውን ጦርነት ሙሉ በሙሉ ችላ ሊሉት አይችሉም።

“ጦርነቱ ሲከሰት ውጥረቶች ነበሩ። በሩሲያውያን እና በዩክሬናውያን መካከል የነበሩ መጋጋሎች ግን ውጭ ነው እንጂ ቤተክርስቲያኗ ውስጥ አልነበሩም። በርካቶች ወደ ቤተ ክርስቲያኗ ሲመጡ ነገሮችን ትውት አድርገው ስለሆነ ነው” ይላሉ የቤተ ክርስቲያኗ የኮሚቴ አባል የሆኑት ድራጋን ኦብሬኖቪች ።

“በተጨማሪ እየሆነ ባለው ነገር ላይ ምንም ተጽእኖ እንደሌለን ስለምናውቅ ሁሉን ነገር ለአምላካችን ጥለን በጋራ ባለን ነገር ላይ እናተኩራለን” ይላሉ።

ከአንዳንድ የሰንበት ትምህርት ቤት የልጆች ግጭት በስተቀር ይህ ነው የሚባል ግጭት እንዳልነበር ቤተ ክርስቲያኗ አስታውቃለች።

ከአውሮፓውያኑ 2014 ጀምሮ ቤተ ክርስቲያኗን የመሩት አባ ኔናድ ለፕሬዚዳንቶቹ ትራምፕ፣ ዜሌንስኪ እና ፑቲን ምክር አላቸው።

በበርሚንግሃም ቦርኒቪል የሚገኘው የቅዱስ ላዛር የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን

“በጣም ከባድ ነው ነገር ግን ሁሉም ሰው በአምላክ አምሳያ እንደተፈጠረ ቢያስብ እና የአምላክን ገጽታ በሰዎች ውስጥ ለማየት እንዲሁም ለማክበር እና ለመውደድ ብንሞክር፣ ፍላጎት ካለ መፍትሄ ማግኘት ትችላላችሁ” ሲሉ ምክራቸውን ለግሰዋል።

ቤተ ክርስቲያኗ የገና በዓል በደመቀ ሁኔታ ከተከበረባቸው የዓለማችን በርካታ ስፍራዎች መካከል አንዷ ናት።

በዓለማችን ለሚገኙ 200 ሚሊዮን የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት ዕለት ታኅሣሥ 29 ናት። ይህም የጁሊያን የዘመን አቆጣጠር ጋር ተያይዞ ነው።

የዚህች ቤተ ክርስቲያን ግንባታ የተጀመረው በአውሮፓውያኑ 1965 ነበር። ይህንን ግንባታ ያከናወኑትም በአንደኛውና ሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ወደ ዩናይትድ ኪንግደም የመጡ ሰርቢያውያን ስደተኞች ነው።

በርካቶቹ በስፍራው በነበረው ካድበሪ የቸኮሌት ፋብሪካ ውስጥ ሥራ አግኝተው ነበር። በጎ አድራጊ የሆነው የካድበሪ ቤተሰብ ይህችን ቤተ ክርስቲያን ለመገንባት ለኮሚቴው ድጋፍ ሰጥተው ነበር።

ቤተ ክርስቲያኗን ለመገንባት “የካድበሪ ቤተሰብ ንብረት የሆነ መሬት አገኙ” በማለት ድራጋን ኦብሬኖቪች ያስረዳሉ።

መሬቱን መግዛት እንፈልጋለን ብለው የካድበሪ ቤተሰብን ሲጠይቁ 5 ሺህ ፓውንድ አምጡ ብለው መለሱላቸው።

“እነዚህ ሰዎች ድሃ ቢሆኑም እንደምንም አምስት ሺህ ፓውንድ ማሰባሰብ ቻሉ” ይላሉ ኦብሬኖቪች።

ስደተኞቹ መሬቱን ለመግዛት የነበራቸውን ቁርጠኝነት ያየው ቤተሰብ 4 ሺህ 999 ፓውንዱን መልሰው አንድ ፓውንድ ብቻ ወሰዱ።

“መሬቱን በአንድ ፓውንድ ብቻ ነው የሸጡት። የሆሊውድ ፊልም ሁሉ ይመስላል” ይላሉ።

ከዚያም ማኅበረሰቡ በቸኮሌት ፋብሪካው ፈረቃቸው መካከል ቤተ ክርስቲያኗን ገነቡ። በአውሮፓውያኑ 1968 ተጠናቆ ገቡ።