ታጣቂዎች አደረሱት በሚባል ጥቃት ከዘጠኝ ዓመታት በላይ የንጹሐን ግድያ ልጓም ባልተገኘለት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኮሬ ዞን አሁንም “ ንጹሐን ተገድለዋል ” ተብሏል።
ስማቸው እንዲነገር ያልፈለጉ የዞኑ አካል ለቲክቫህ ኢትዮጵያ በሰጡት ቃል፣ “ታጣቂዎች ባደረሱት ጥቃት ባለፉት 48 ሰዓታት ብቻ የሁለት ሰዎች ህይወት አልፏል ” ብለዋል።
በዞኑ ኬረዳና ጀሎ በተሰኙት ቀበሌዎች አንታዮ ዦላና አድማሱ አሰፋ የተባሉ ሰዎች ታጣቂዎቹ ሰነዘሩት በተባለ ጥቃት መገደላቸውን ከቤተሰቦቻቸው መረጋገጡን ነው የገለጹት።
አቶ አንታዮ ዦላ የተገደሉት ከትላንት በስቲያ ታኀሳስ 28 ቀን 2017 ዓ/ም ከቀኑ 11 ሰዓት ተኩል ኬረዳ ቀበሌ መሆኑን አስረድተው፣ “ ገዳዮቹ ከጋላና ወረዳ ሻሞሌ ሽዳ ታጥቀው ወደ ኮሬ ዞን ዘልቀው ገብተው ነው ” ብለዋል።
“ በዚሁ ቀበሌ ጥቃት ከመፈጸም ተጨማሪ የቤት እንስሳትን ዘርፈዋል ” ብለው፣ “ አድማሱ አሰፋ ደግሞ ታኀሳስ 29 ቀን 2017 ዓ/ም ከቀኑ 6:30 ገደማ ጄሎ ቀበሌ ተገድሏል ” ሲሉ ገልጸዋል።
“ ገዳዮቹ የጋላና ወረዳ የቡልቶ ጃልደሳ ታጣቂዎች ወደ ኮሬ ዞን ዘልቀው በመግባት ጥቃት ፈጽመው ነው ” ብለዋል።
“ ባለፉት ቀናት ጥቃት ለመሰንዘር ከፍተኛ እንቅስቃሴ እንደነበር ከህዝብ አስተያየት መረጃ መመልከት ተችሎ ነበር። መረጃዎቹ ከጃሎ፣ ኬረዳ፣ ዞቀሣ፣ ጋሙሌ፣ ሻሮ፣ ጎልቤ፣ ቆቦ፣ ዶርባዴ ቀበለያት ተሰባስበዋል” ነው ያሉት።
የንጹሀን ጥቃቱ እንዲቆም ለመንግስት አሳስበው እንደሆን በቅርቡ ቲክቫህ ኢትዮጵያ ጥያቄ ያቀረበላቸው በሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት የዞኑ ሕዝብ ተወካይ አምዛዬ አወቀ (ዶ/ር)፣ በፓርላማ ቢያሳውቁም ድርጊቱ እንዳልቆመ ገልጸው ነበር።
“ ነዋሪዎቹ በየቀኑ ይገደላሉ። የአንዱ ግድያ ይገለጻል፤ የአንዱ አይገለጽም ሰው ተሰላችቶ” ብለው፣ “መንግስት ትኩረት ቢሰጥ ኖሮ ያ አካባቢው የሚያስቸግር አይደለም ጠባብ ቦታ ነው ገላና ሸለቆና ነጭ ሳር ፓርክ እነዚህ ሽፍቶች የሚንቀሳቀሱበት ነው ” ብለው ነበር።
ከዚህ ቀደም ስለጉዳዩ የጠየቅናቸው በክልሉ ምክር ቤት የቀድሞ አማሮ ምርጫ ክልል ተወካይ አቶ ዜናነህ አዱላ በበኩላቸው፣ “ አካባቢው ከ2009 ዓ/ም ጀምሮ በጸጥታ ችግር የወደቀ ነው ” ማለታቸው ይታወሳል።
“ በአካባቢው ላይ ከመንግስት ተቃርኖ የሚንቀሳቀሰው የሸኔ ታጣቂ መኖሩ ሁኔታውን አባብሶታል” ብለው፣ “ ‘መንግስት ቸልተኛ ሆኗል’ የሚል ግምገማ አለን ” ሲሉ ተናግረው ነበር።
ከወራት በፊት ቃሉን የሰጠን ዞን ኮሚኒኬሽን “ ባለፉት ዓመታት ከ300 በላይ ንጹሐን በታጣቂዎች ተገድለዋል ” ማለቱ አይዘነጋም።