Getu Temesgen – (ጌጡ ተመስገን)  · Follow

ጥቂት ስለ መሬት መንቀጥቀጥ እና የሕንጻ መዋቅር ዲዛይን

#Ethiopia | የመሬት መንቀጥቀጥ ከመሬት የውስጠኛው ክፍል በድንገት በሚለቀቅ ‘ኢነርጂ’ ምክንያት የላይኛው የመሬት ክፍል ላይ በሞገዶች (seismic waves) አማካኝነት የሚተላለፍ ንዝረት ወይም መንቀጥቀጥ ነው።

ለመሬት መንቀጥቀጥ በተጋለጡ አካባቢዎች ያሉ ሕንፃዎች የመሬት መንቀጥቀጥ በሚከሰትበት ጊዜ የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ እና ነዋሪዎችን ለመጠበቅ የመሬት መንቀጥቀጥ ኃይሎችን እንዲቋቋሙ ሆነው የተነደፉ መሆን አለባቸው። ይህ የመሬት መንቀጥቀጥን የሚቋቋም ንድፍ earthquake-resistant design (ERD). በመባል የሚታወቅ ሲሆን ይህንንም ለመስራት ልዩ የምህንድስና ትምህርት እና ልምዶችን ይፈልጋል።

በመሬት መንቀጥቀጥ ወቅት መሬቱ በምን ያህል ፍጥነት እንደሚንቀጠቀጥ የሚለካበት በ PGA(Peak Ground Acceleration) መንገድ ነው። ይህ ለዲዛይን ዋናው መሰረት ነው ፤ እርሱም ከፍተኛውን የመንቀጥቀጥ ፍጥነት ከመሬት የስበት ኃይል (9.81 m/s²) ጋር አዛምዶ ያሳየናል። ከፍ ያለ PGA ማለት ጠንካራ መንቀጥቀጥ እና የበለጠ ጉዳት ሊያስከስት የሚችል ማለት ነው።

PGA ከ0.1%g ያነሰ ከሆነ ላናስተውለው እንችላለን ፤ ከ 0.1-1% g ከሆነ ምንም ጉዳት ሳያስከትል በትንሽ እናስተውለዋለን ፤ ከ1-3% g ቀላልና አነስተኛ ፤ ከ3-10% መካከለኛና ትንሽ ጉዳት ፤ ከ10-30% በጣም ጠንካራ የመዋቅራዊ ስንጥቆች (Very strong, structural cracks )፤ከ30-50% ከባድና ከፍተኛ ጉዳት፤ ከ50-100% ኃይለኛና የሕንፃዎች መፈራረስ ፤ ከ100% g በላይ ከሆነ ደግሞ እጅግ በጣም ከባድና አጠቃላይ ጥፋትን ያስከትላል።

የኢትዮጵያ የሕንፃ ኮድ ኢትዮጵያ ለመሬት መንቀጥቀጥ ተጋላጭ የሆነ አካባቢ እንዳላት በግልጽ ያስቀምጣል።

ለመሬት መንቀጥቀጡ እንዳላቸው ተጋላጭነት ቦታዎቹን አዲሱ የ2015ቱ ኮድ( EBCS EN: 2015) Zone 0, Zone 1, Zone 2, Zone 3, Zone 4 እና Zone 5 በማለት በ6 ምድቦች አስቀምጧቸዋል። በነገራችን ላይ ይህ ኮድ በጣም የተሻለ ቢሆንም እንኳን በባለሙያዎች ዘንድ በቂ ግንዛቤና ይሁንታን ሳያገኝ እና በበቂ ሁኔታ ተግባራዊ ሳይሆን አዲሱ ኮድ እንደተባለ ይኸው አስር አመት ሞላው ፤ በኮዱ አጠቃቀም ዙርያ በሥራ ላይ ያጋጠሙ ችግሮችንና ያሁኑን ክስተት ከግምት ወስጥ በማስገባት በፍጥነት መከለስ (ክለሳው መጠናቀቅ) ይኖርበታል።

በአዲስ አበባ ያሉ ሕንጻዎች አሁን ባለው የሕንጻ ኮድ (EBCS EN-1998-1:2015)መስፈርት መሰረት ለ 0.1g (ማለትም 10% g) PGA የተሠሩ እና ሊሠሩ የሚገባቸው ናቸው። የቀድሞው ኮድ እንኳን (EBCS 8 1995) በአዲስ አበባ ለሚሰሩ ሕንጻዎች ከ 5% g እስከ 7% g PGA ታሳቢ ተደርገው እንዲሰሩ ያዛል ። በዚህም መሰረት እስካሁን ባለው ሁኔታ የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀት ጥንካሬ (ማለትም 1% g) በአዲስ አበባ ውስጥ ያሉት በበቂ ባለሙያ እና ኮዱን ተከትለው የተሠሩ ሕንጻዎች ላይ ጉዳት ለማድረስ የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀት በጣም ትንሽ ነው። ነገር ግን፣ ከመሬት መንቀጥቀጡ በተወሰኑ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ባለው አካባቢ፣ 10% g የመሬት መንቀጥቀጥ በሚገመትበት ቦታ ላይ ጉዳት ሊደርስ ይችላል።

ይህ ማለት ግን ስጋቱ የለም ማለት አይደለም ፤ የመሬት መንቀጥቀጡ እየጨመረበት ያለበት ሁኔታ እና ከዚህ ቀደም በ1961 ካራቆሬ ላይ በሬክተር ስኬል 6.5 ተከስቶ የሰዎች ሕይወት እንዳለፈ ሲታሰብ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያሰፈልግ እንረዳለን ።

ሊደረጉ የሚገባ ጥንቃቄዎች

ተደጋጋሚ እና ጥልቅ የባለሙያዎች እና የሚመለከታቸው አካላት የቀጥታ ውይይትና ገለጻ ችግሩ እስኪቀረፍ ድረስ በቋሚነት በሁሉም የመንግስት እና የግል መገናኛ ተቋማት ያስፈልጋል ። ጉዳዩ በመግለጫ ብቻ የሚታለፍ አይደለም ።

አደጋ ቢከሰት ስለሚደረጉ ጥንቃቄዎች ቀድሞ ማስተማር እና ማዘጋጀት

ያረጁ ሕንፃዎች – በዲዛይን ጊዜ የሚታሰበው የሕንጻዎቹ የአገልግሎት ዘመን ያበቃ (ከ50 ዓመት በላይ የሆናቸው)ያረጁ ሕንፃዎች በብዙ ምክንያት ለዚህ አደጋ የተጋለጡ ናቸው። በዘመን ብዛት በCreep effect እና fatigue ምክንያት የኮንክሪት ስትራክቸር ጥንካሬ ይቀንሳል። በንጉሡ ጊዜ ተሠርተው አሁንም አገልግሎት እየሰጡ ያሉ ሕዝብ መገልገያ ሕንጻዎች ማለትም ትምህርት ቤት ፤ የህክምን ተቋማትና ሌሎችም ። እነዚህ የማጠናከርያ ሥራ (Retrofitting) ይፈልጋሉ ።

በድንጋይ ግንብ (Masonry) ብቻ እና መሰል የአርማታ ብረት የሌላቸው ግንባታዎች።

ተገቢውን የአፈር ጥናት፣ ዲዛይን እና ክትትል ሳይደረግላቸው የተገነቡ ግንባታዎች ለአደጋ ተጋላጭ ናቸው።

በሚገባው ባለሙያ ዲዛይን ያልተደረጉ እና ያልተገነቡ ግንባታዎች ለዚህ ተጋላጭ ናቸው። ከተገነቡ በኋላ በተለይ ግርግዳቸውና ሌሎች የሕንጻ አካላት ፍርሰው ባዶ ሲሆኑ በወለሎቹ መካከል የጥንካሬ ልዩነት ሲከሰት (Soft stories) በሰላም ለዘመናት የኖሩትን ሕንጻ ለአደጋ እንዳርጋቸዋለን።

የሕንጻ ኮድ ክለሳውን ማፋጠን

መልካሙን ነገር ያሰማን !

(ኤልያስ ደፋልኝ)

May be an image of map and text