

የኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስትር አይሻ መሐመድና የሶማሊያ አቻቸው አብዱልቃዲር መሐመድ ኑር ዓርብ ታኅሳስ 25 ቀን 2017 ዓ.ም. በሞቃዲሾ በተገናኙበት ወቅት
ዜና ሶማሊያ ኢትዮጵያን በአዲሱ የሰላም አስከባሪ ተልዕኮ የማካተትን ሒደት እያጤንኩት ነው አለች
ቀን: January 8, 2025
ሶማሊያ በአዲሱ የአፍሪካ ኅብረት ድጋፍና ማረጋጋት ተልዕኮ (አውሶም) ውስጥ የኢትዮጵያን ጦር እንዳይካተት ስትቃወም የነበረውን አቋሟን በማለዘብ፣ ጉዳዩን በድጋሚ እያጤነችው እንደምትገኝ አስታወቀች፡፡
ይህ የሞቃዲሾ የአቋም ለውጥ የታየው የኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሐመድ ከቀናት በፊት ሶማሊያን ከጎበኙ በኋላ ነው፡፡ ሚኒስትሩ ከሶማሊያ አቻቸው አብዱልቃድር መሐመድ ኑር ጋር ተወያይተዋል፡፡ ለአዲሱ ተልዕኮ ጦር የሚያዋጡ አገሮች ዝርዝር የመጨረሻ ውሳኔ ላይ ለመድረስ ሶማሊያ እየሠራች መሆኗን ገልጸው፣ ኢትዮጵያም እንደከዚህ ቀደሙ ጦሯን ለማዋጣት ያቀረበችውን ጥያቄ ሶማሊያ ተቀብላ እያጤነችው እንደምትገኝ የሶማሊያው መከላከያ ሚኒስትር ገልጸዋል፡፡ ይህንንም ጉብኝቱን በማስመልከት የሶማሊያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባወጣው መግለጫ ይፋ አድርጓል፡፡
ሁለቱ መከላከያ ሚኒስትሮች በሞቃዲሾ ያደረጉት ምክክር የአንካራውን ስምምነት አፈጻጸም ላይ ቀጣይነት ያለው ውይይት ለማድረግ ሲሆን ከሳምንት በፊት በሶማሊያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የተመራ ልዑክም አዲስ አበባ ተገኝቶ እንደነበር ይታወሳል፡፡
አዲሱ የአፍሪካ ኅብረት ሰላም አስከባሪ ተልዕኮ በሶማሊያ (AUSSOM) በረፈንጆቹ አዲስ ዓመት (January 1,2025) ሥራውን እንዲጀምር በተመድና በአፍሪካ ኅብረት ቀነ ገደብ ተቀምጦለት የነበረ ሲሆን፣ ከቀነ ገደቡ ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ ሶማሊያ የኢትዮጵያን ጦር እንደማታካትት ይፋ አድርጋ ነበር፡፡
ከሳምንት በፊት ተመድ በአዲሱ የሶማሊያ ተልዕኮ የገንዘብ ድጋፍ ዙሪያ ምክክር ባደረገበት ወቅት፣ በተመድ የሶማሊያ ተወካይ መሐመድ ራኪ ‹‹ለአዲሱ ተልዕኮ ጦር የሚያወጡትን አገሮች መርጠን ጨርሰናል፡፡ በግልጽ በሚታወቀው ምክንያት ከኢትዮጵያ ጋር ያለንን ሁኔታና የጦር አዋጭ አገሮችን እንደገና ከልሰናል፡፡ በመሆኑም በኢትዮጵያ ጦር አለመካተት ምክንያት የሚፈጠር የፀጥታ ክፍተት እንዳይኖር፣ ከሌሎች የጦር አዋጭ አገሮች ጋር የሁለትዮሽ ስምምነት ሞልተን ጨርሰናል፤›› ብለው ነበር፡፡ በወቅቱ ሶማሊያ አልሸባብን ለመዋጋት በአዲሱ ተልዕኮ ከሚያስፈልገው 11,000 ሺሕ ሰላም አስከባሪ ወታደሮች 7,000 ሺሕ ያህሉን ከዩጋንዳ እንዲሁም የተቀሩትን ከሩዋንዳ፣ ጂቡቲ፣ ኬንያ፣ ብሩንዲና ደቡብ ሱዳን እንዳሟላች ገልጾ ነበር፡፡
ብሩንዲ የተሰጣት የአንድ ሺሕ አካባቢ ወታደር ኮታን ተቃውማ እንደማትሳተፍ ገልጻለች፡፡
የኢትዮጵያ ጦር ከዚህ ቀደም በሶማሊያ በነበሩት ተልዕኮዎች (AMISOM እና ATMIS) በሁለት መልኩ ሲሳተፍ የነበረ ሲሆን፣ ይህም በሁለትዮሽና በአፍሪካ ኅብረት ተልዕኮዎች በኩል ነበር፡፡ ይሁንና ነባሩ ተልዕኮ (ATMIS) በባለፈው ሳምንት December 31, 2024 ሲያበቃና አዲሱ ተልዕኮ (AUSSOM) በሚቀጥሉት ቀናት ተልዕኮዎን ሲረከብ የሶማሊያው ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር ባለፈው ዓመት የገባችውን ስምምነት (MOU) ካላፈረሰች፣ የኢትዮጵያ ጦር ከሶማሊያ መውጣት እንዳለበት ሲገልጹ ቆይተው ነበር፡፡ ይሁንና በቱርኪዬ አደራዳሪነት በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) እና ሀሰን ሼክ መሐሙድ የደረሱበት የአንካራው ስምምነት፣ ይህንን የሶማሊያ አቋም በማስቀየር፣ ሶማሊያ ኢትዮጵያን በአዲሱ ተልዕኮ ለማሳተፍ እንድታጤነው አስገድዷታል፡፡ የሪፖርተር ምንጮች እንደሚጠቁሙት ግን ኢትዮጵያ በሶማሊያ የሚኖራት ተሳትፎ ጦሯን በራሷ በጀት እስከደገፈች ድረስ ሶማሊያ እንደምትፈቅድ ገልጸዋል፡፡ የኢንጂነር አይሻን ጉብኝት ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግሥት በደፈናው በፀጥታ ጉዳዮች፣ ከሶማሊያ መንግሥት ጋር አብሮ ለመሥራት ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ከመግለጽ ባለፈ ዝርዝር ጉዳዮችን አላመለከተም፡፡
ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር የገባችውን ስምምነት ተከትሎ የሀሰን ሼክ መንግሥት የግብፅን ጦር ወደ ሶማሊያ ለማስገባት ጫፍ ደርሶ የነበረ ሲሆን በመጨረሻ ግን ሳይገፋበት በእንጥልጥል ቀርቷል፡፡ ኢትዮጵያም ስምምነቱን የፈረሙት የሶማሌላንድ ፕሬዚዳንት ሙሴ ቢሂ በቅርብ በተደረገው ምርጫ ተሸንፈው አዲሱ ፕሬዚዳንት አብድር ሃማን ሞሐመድ (ኢሮ) አርጌሳን በመረከባቸው ስምምነቱ በእንጥልጥል ቀርቷል፡፡