ማኅበራዊ
ተስፋ መቁረጥ የተሸነፈበት መቄዶኒያ

የማነ ብርሃኑ

ቀን: January 8, 2025

በተለያዩ ምክንያቶች ጥቂት የማይባሉ ሰዎች ለከፋ ችግር ይጋለጣሉ፡፡ ኑሮን መቋቋም አቅቷቸው የሰው እጅ ማየትና ጎዳና እስከመውጣትም ይደርሳሉ፡፡ አረጋውያን በእርጅና ዘመናቸው ጧሪ ደጋፊ አጥተው ሜዳ ላይ ወድቀው የሚያነሳቸው እጅ ሲጠባበቁ መመልከትም የተለመደ ነው፡፡

ሕፃናትና እናቶች በከፋ ድኅነትና ችግር ውስጥ ወድቀው ይታደገኛል ለሚሉት ወገናቸው እጃቸውን ለምፅዋት ሲዘረጉ ማየትም አዲስ አይደለም፡፡ በተለይ በአሁኑ ወቅት ኑሮ ቡዙኃኑን እየፈተነ ባለበት ሁኔታ በኢኮኖሚ ችግር የሚማቅቁ የኅብረተሰብ ክፍሎች በርካታ ናቸው፡፡ እነኚህን አቅመ ደካሞችና ችግረኞችን በመንከባከብና በመደገፍ ካሉበት አስከፊ ሕይወት እንዲወጡ ለማስቻል በጎ አድራጊ ግለሰቦችና ተቋማት የድርሻቸውን እያበረከቱ ይገኛሉ፡፡

ከእነዚህ ተቋማት መካከል ጧሪና ደጋፊ የሌላቸውን አረጋውያንና የአዕምሮ ሕሙማን ከወደቁበት ጎዳና በማንሳት እንክብካቤ በመስጠት ላይ የሚገኘው መቄዶኒያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ሕሙማን መረጃ ማዕከል ይጠቀሳል፡፡

መቄዶኒያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ሕሙማን መረጃ ማዕከል ‹‹ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን በቂ ነው›› በሚል መርህ ጧሪና ደጋፊ በማጣት ጎዳና የወደቁ አረጋውያንና በአዕምሮና በተለያዩ ሕመሞች ምክንያት የሚንከባከባቸው አጥተው የሚባክኑ ወገኖችን በመቀበል የምግብ፣ የአልባሳትና የመጠለያ ድጋፍ እየሰጠ ይገኛል፡፡

የማዕከሉ መሥራችና ሥራ አስኪያጅ አቶ ቢንያም በለጠ በታኅሳስ 2002 ዓ.ም. የቤተሰቦቻቸውን ቤት በመጠቀም በአሥር ሰዎች የጀመሩት የበጎ አድራጎት ሥራ፣ ዛሬ ላይ በመላ አገሪቱ በሚገኙ 44 ከተሞች ከስምንት ሺሕ በላይ ሰዎች የሚረዱበት ሆኗል፡፡

ፕሬዚዳንት አቶ ታዬ አጽቀሥላሴ ታኅሳስ 18 ቀን 2017 ዓ.ም. መቄዶኒያ ማዕከሉን በጎበኙበት ወቅት እንደተናገሩት፣ የማዕከሉ መሥራችና ሥራ አስኪያጅ አቶ ቢንያም በለጠ በጎ ልብ ያለው ብቻ ሳይሆን ያለውንና የተሰጠውን ሁሉ ለሌሎች ለማድረግ የወደደና አርዓያ ለመሆን የቻለ ሰው ነው፡፡

‹‹ማዕከሉ ብዙዎችን ከመቃብር ጉድጓድ አፋፍ ጎትቶ አውጥቷል፡፡ ብዙዎች ተስፋ በቆረጡበትና በመኖርና ባለመኖር መካከል ያለው ልዩነት ባልታየቸው ጊዜ ሰው ድጋፍ ካገኘ እንደገና ተመልሶ ሕይወት መዝራት እንደሚችል ያሳየ ነው፤›› ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ በማዕከሉ በነበራቸው ቆይታ ፅናት፣ ጥንካሬና ብርታትን መመልከታቸውን ተናግረዋል፡፡

‹‹በመቄዶኒያ የአረጋውያንና የአዕምሮ መርጃ ማዕከል ውስጥ ተስፋ መቁረጥ ሲሸነፍ አይቻለሁ፡፡ የማዕከሉ መሥራች ይህን በጎ ተግባር ባያሳካው፣ የእነኚህ ወገኖች ችግር፣ ሰቆቃና ተስፋ መቁረጥ በዚህ መሰል በጎ ተግባር ሳይመለስ ቢቀር እንደ ሰው ቁስሌን እንዴት ማከም እችል እንደነበር አላውቅም፤›› ሲሉም ገልጸዋል፡፡

እንደ ፕሬዚዳንቱ፣ ከበጎነትና ከመልካምነት በላይ ዕውቀትም ሆነ መዳረሻ የለም፡፡ የዕውቀትና ጥበብ ትልቁ ግቡ ለሰው መድረስና ወገንን ማትረፍ ነው፡፡ የሚደግፋቸው፣ የሚረዳቸውና የሚያግዛቸው በማጣት በተለያዩ ምክንያቶች ጎዳና ላይ የወደቁ፣ የተቸገሩና በሕመም የሚሰቃዩትን ማየት እንደ ኢትዮጵያዊ ዜጋ የሁሉም ሕመምና ደዌ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ይህን መሰል ማዕከል መኖሩ ብርታትና ጥንካሬ ሰጥቶ እንደ አገር ያለብን ሕመምና ደዌ መታከም የሚችል ስለመሆኑ አሳይቷል፡፡

የሕይወትና የመኖር ሙሉነት የሚገለጸው ለሌሎች በጎ በማሰብና በመስጠት ነው ያሉት አቶ ታዬ፣ ስለሆነም የመቄዶኒያን መንገድና አርዓያነት የሚከተሉ ሌሎች በበጎ ተግባር ሥራ ላይ የተሰማሩ ተቋማት እንደ አገር ሊበዙና ሊስፋፉ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

‹‹ኢትዮጵያውያን ከተባበርንና ከተደጋገፍን በርካቶችን ከችግር ማጥ ውስጥ ማውጣት እንችላለን፡፡ ባለመስጠት ንፉግ መባልንም አንፈልግም፡፡ ሁላችንም የአቅማችንን መስጠት ከቻልን ተስፋ የሌላቸው የሚመስሉ ወገኖች ሕይወት ላይ ተስፋ መዝራት እንችላለን፡፡ በመሆኑም መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጎዳና ላይ የወደቁትን በማንሳትና በመንከባከብ አገራዊ ኃላፊነቱን መወጣት ይኖርበታል፤›› ሲሉም አሳስበዋል፡፡

እንደ አቶ ታዬ፣ መቄዶንያ የአረጋውያንና የአዕምሮ መርጃ ማዕከል በተለያዩ የአገሪቱ ከተሞች እያከናወናቸው ለሚገኙ የበጎ ተግባር ሥራዎች የሐሳብ፣ የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ ይፈልጋል፡፡ ስለሆነም የማዕከሉን በጎ ሥራ በመደገፍ እያንዳንዱ ዜጋ አቅሙ በሚፈቅደው ልክ የመልካም ሥራው ተባባሪ በመሆን የድርሻውን ማበርከት ይኖርበታል፡፡

የማዕከሉ መሥራችና ሥራ አስኪያጅ አቶ ቢንያም በለጠ እንደገለጹት፣ መቄዶኒያ በአገሪቱ በሚገኙ 44 ከተሞች ከስምንት ሺሕ በላይ ድጋፍና እንክብካቤ የሚሹ ወገኖችን በመርዳት ላይ ይገኛል፡፡

ማዕከሉ ጧሪና ደጋፊ የሌላቸውን አረጋውያን፣ ራሳቸውን ችለው መንቀሳቀስ፣ መመገብና መፀዳዳት የማይችሉ ሕሙማንና የተቸገሩ በርካታ ወገኖችን የሚያስተናግድ በመሆኑ በጎና ልብ ያላቸው ደጋግ የኢትዮጵያውያንን ድጋፍ ይፈልጋል፡፡ ስለሆነም ሁሉም ዜጋ ይህንን ቅዱስ ተግባር በመደገፍ ተቋሙን እንዲያግዝና እንዲረዳ ሲሉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡