ዳዊት ታዬ

January 8, 2025

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ከመተዳደሪያ ደንቡ ውጪ ለማካሄድ ያቀደው ጠቅላላ ጉባዔና ምርጫ አነጋጋሪነቱ ቀጥሏል፡፡ 

ጥር 3 ቀን 2017 ዓ.ም. ይካሄዳል ተብሎ የሚጠበቀው ጠቅላላ ጉባዔና ምርጫ ነባር የምክር ቤቱ አባላትን ባገለለና የንግድ ምክር ቤቱን ሕገ ደንብ በጣሰ መንገድ የሚካሄድ ነው ሲሉ ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ የንግድ ምክር ቤቱ አባላት ለሪፖርተር ገልጸዋል።

አጠቃላይ የምርጫ ሒደቱ ከንግድ ምክር ቤቱ ጽሕፈት ቤት እጅ ወጥቶ በሌላ አካል አስመራጭነት ለማካሄድ ታቅዶ ዝግጅት መጠናቀቁን የጠቀሱት እኚሁ የምክር ቤቱ አባላት፣ በመጪው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ከንግድ ምክር ቤቱ አሠራርና ዕውቅና ውጪ ከሁሉም የአዲስ አበባ ክፍለ ከተሞች የሚወከሉ ነጋዴዎችን ተሳታፊ ለማድረግ መታቀዱን አስረድተዋል።

ከንግድ ምክር ቤቱ ዕውቅና ውጪ በአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ አስተባባሪነት ከአሥራ አንዱም ክፍላተ ከተሞች ጥሪ የተደረገላቸው ነጋዴዎች ከሰሞኑ ስብሰባ አድርገው በመጪው የንግድ ምክር ቤቱ ጉባዔ ላይ በቀጥታ የሚሳተፉ የጉባዔ አባላትን ከነጋዴዎች መካከል መርጠው መወከላቸው ታውቋል።

በጠቅላላ ጉባዔው እስከ 1,500 የሚሆኑ ተሳታፊዎች ይገኛሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 55ቱ ለንግድ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንትነትና የቦርድ አባልነት እንደሚወዳደሩ ምንጮቹ ጠቁመዋል። የንግድ ምክር ቤቱን ሕገ ደንብና አሠራር በመጣስ የንግድ ምክር ቤቱን ጠቅላላ ጉባዔና ምርጫ ለማካሄድ እየተደረገ ያለውን ዝግጅት ይበልጥ አነጋጋሪ ያደረገው የምክር ቤቱ ነባር አባላት በጠቅላላው ጉባዔው ይወከሉ፣ አይወከሉ የሚለው ጉዳይ የማይታወቅ መሆኑ ነው፡፡ 

በንግድ ምክር ቤቱ መተዳደሪያ ደንብ መሠረት በጠቅላላ ጉባዔ ላይ የመሳተፍና የመምረጥ መብት ያላቸው የምክር ቤቱ አባላት ብቻ ሆነው ሳለ፣ አሁን ባለው አሠራር ግን የምክር ቤቱ አባላት ምንም ዓይነት ተሳትፎ እንዳይኖራቸው መደረጉን ምንጮቹ ተናግረዋል።

ከአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ጽሕፈት ቤት ምንጮች ማረጋገጥ እንደተቻለውም የምክር ቤቱ አባላት ጥር 3 ቀን በሚካሄደው ጠቅላላ ጉባዔና ምርጫው ላይ እንዲገኙ ሲተላለፍ የነበረው የጥሪ ማስታወቂያ እንዲቋረጥ ተደርጓል፡፡ ከዚህ በተቃራኒ ደግሞ ከየክፍለ ከተሞቹ የሚወከሉ 1,500 ነጋዴዎች በጠቅላላ ጉባዔው ላይ ተሳታፊ እንደሚሆኑና ከእነዚህ ውስጥም 500 የሚሆኑት በምርጫው ላይ በድምፅ እንደሚሳተፉ እየተነገረ ነው።

‹‹በዚህ ቀመር መሠረት ነባር የምክር ቤቱ አባል የሆነ ነጋዴዎች በጠቅላላ ጉባዔው መገኘት አይችሉም፤›› ያሉት ምንጮቹ፣ አጠቃላይ ሒደቱ ከንግድ ምክር ቤቱ እጅ ወጥቷል በማለት የሒደቱን ውስብስብነት ያስረዳሉ፡፡ በጠቅላላ ጉባዔው ዕለት ምናልባት ተሰናባቿ ፕሬዚዳንት ሪፖርት ሊያቀርቡ ይችላሉ ከሚል ግምት ውጪ የዕለቱን መርሐ ግብር ጽሕፈት ቤቱም ሆነ አባላት እንደማያውቁት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡ 

አዲስ የተቀረፀውና እየተተገበረ ያለው የምርጫ ማስፈጸሚያ ሥርዓት የፀና የንግድ ፈቃድ ያላቸው በጠቅላላ ጉባዔው መምረጥና መመረጥ እንደሚችሉ የተቀመጠ በመሆኑ፣ እስካሁን አባል ሆነው የአባልነት ግዴታቸውን እየተወጡ ያሉ ነጋዴዎች ተሳትፎን አናሳ እንደሚያደርገው ምንጮቹ ተናግረዋል። በአዲስ አበባ ንግድ ቢሮው አስተባባሪነት በየክፍለ ከተሞቹ በተደረጉ ምርጫዎች በጣት የሚቆጠሩ ነባር አባላት ብቻ በጉባዔው እንዲሳተፉ መወከላቸውን፣ የተቀሩት አብዛኛዎቹ ግን የምክር ቤቱ አባል ያልነበሩ ነጋዴዎች መሆናቸውን ምንጮቹ ገልጸዋል። 

አጠቃላይ የምርጫውን ሒደት በተመለከተ ጽሕፈት ቤቱ ምንም ዓይነት መረጃ የሌለው በመሆኑ፣ የዘንድሮው ምርጫና ጠቅላላ ጉባዔ ሒደት ከንግድ ምክር ቤቱ ጽሕፈት ቤት ውጪ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት የንግድ ምክር ቤቱን ነባር አሠራሮች በሙሉ በመሰረዝ ከአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ጋር በመሆን እንዲዘረጋ ያደረገው አሠራር ንግድ ምክር ቤቱን አሳልፎ እንደመስጠት የሚቆጠር መሆኑን የሚገልጹት ያነጋገርናቸው የንግድ ምክር ቤቱ አባላት፣ አካሄዱ ሕገወጥ ስለሆነ በሕጋዊ መንገድ ጥያቄ የሚያቀርብበት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ይህንን ምርጫ ሒደት በመቃወም ጉዳዩን ወደ ሕግ የወሰዱም አሉ፡፡

የንግድ ምክር ቤቱ ሕልውና አደጋ ላይ ስለመሆኑ በቁጭት የሚናገሩት እነዚህ የምክር ቤቱ ምንጮቻችን፣ በሁሉም የአዲስ አበባ ክፍለ ከተሞች የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች በአዲስ መልክ እየተቋቋመ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ይህንን በተመለከተ የጉለሌ ክፍለ ከተማ ንግድ ጽሕፈት ቤት በክፍለ ከተማው ያሉ ነጋዴዎችን በማሰባሰብ የንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በአዲስ መልክ ማደራጀቱን በይፋ እንዳስታወቀ ገልጸዋል። 

በጉለሌ ክፍለ ከተማ ተቋቋመ በተባለው የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የማቋቋሚያ መድረክ ላይ በመጪው የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ የሚሳተፉ ነጋዴዎች ምርጫ መከናወኑንም ጨምረው ገልጸዋል።

በምርጫው ላይም የንግድ ፈቃድና የድርጅት ባለቤት የሆኑ፣ እንዲሁም በትምህርት ደረጃቸው ዲፕሎማ ያላቸው በጠቅላላ ጉባዔው ለመሳተፍ እንደተመረጡ ለማወቅ ተችሏል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ የልደታ ክፍለ ከተማ ንግድ ጽሕፈት ቤት ባዘጋጀው መድረክም በንግድ ምክር ቤቱን ሊመሩ የሚችሉ ዕጩዎች የተጠቆሙበት መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡

በንግድ ምክር ቤቱ የ78 ዓመታት ታሪክ ባልታየ ሁኔታ ሲከተላቸው የነበሩ የምርጫ አሠራሮችን በመጣስ፣ ከጽሕፈት ቤቱ ውጪ ያለ አካል ጠቅላላ ጉባዔውን እንደጠለፈው የሚገልጹ የንግድ ምክር ቤቱ ሠራተኞች በበኩላቸው፣ ተሰናባቹ የንግድ ምክር ቤቱ ቦርድ እየወሰዳቸው ያሉ ዕርምጃዎች ፈጽሞ አግባብነት የሌላቸው እንደሆኑ ይናገራሉ።

በተለመደው አሠራርና በመተዳደሪያ ደንቡ መሠረት የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫዎች በጽሕፈት ቤቱ በኩል ይከናወኑ የነበረ መሆኑን፣ በዚሁ አግባብም ጽሕፈት ቤቱ የዕጩዎች ጥቆማ መቀበል ጀምሮ የነበረ መሆኑን፣ ነገር ግን ግልጽ ባልሆነ ምክንያት ጽሕፈት ቤቱ የጀመረውን ሒደት በማስቆም በአዲስ አሠራር ምርጫውን ለማካሄድ መወሰኑን ገልጸዋል፡፡ 

በነባሩ አሠራርና በምክር ቤቱ ደንብ መሠረት ተጀምሮ የነበረውን የምርጫ ሒደት የንግድ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት በደብዳቤ ያስቆሙት ሲሆን፣ ይህንንም ያደረጉት የምክር ቤቱን አባላት ብዛት ለማስፋት አዲስ አሠራር በማስፈለጉ ነው የሚል ምክንያት ማቅረባቸው ይታወሳል፡፡

የንግድ ምክር ቤቱ ነባር ሠራተኛ ስለሁኔታው ለሪፖርተር እንደለገጹት፣ ‹‹የጠቅላላ ጉባዔና የምርጫ ሒደቱ በሙሉ ከጽሕፈት ቤቱ አውጥተው በሌላ በኩል እንዲካሄድ ቦርዱ ተስማምቷል፤›› ብለዋል፡፡ 

ይህንንም ስምምነት ያደረገው ከአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ጋር መሆኑን የገለጹት እኚሁ ሠራተኛ፣ ይህ ከንግድ ምክር ቤቱ አሠራር ውጪ በመሆኑ ቀጣዩ ጠቅላላ ጉባዔና የምርጫ ሒደትን አወዛጋቢ ሊያደርገው ይችላል በማለት ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡ 

የንግድ ምክር ቤቱን የመተዳደሪያ ደንብ በማሻሻል ከተለደመው አሠራር ውጪ እንዲሆን ውሳኔ ያሳለፉት የተሰናባቹ ቦርድ አባላት፣ ከዚህ ቀደም በምርጫ ሒደት የተቀመጡ መሥፈርቶች ሳይካተቱ ምርጫው በዘልማድ እንደሚካሄድ እንዲካሄድ መፈለጉ የማይስማሙ መሆኑም እየተገለጸ ነው፡፡ 

ከዚህ ቀደም የሚካሄዱ ምርጫዎች አባልነትን ከማረጋገጥ ጀምሮ ለመመረጥና ለመምረጥ አባሉ ዓመታዊ የአባልነት ክፍያ መክፈል አለመክፈሉ የሚረጋገጥበት አሠራር እንደነበር፣ አሁን ግን አባል ያልሆኑ ከየክፍለ ከተሞቹ የሚወከሉ የፀና የንግድ ፈቃድ ያላቸው ነጋዴዎች በጉባዔው እንዲሳተፉ መወሰኑን ምንጮቹ አስረድተዋል። ምርጫን ለማካሄድ እየተሄደበት ያለው መንገድ እንዲህ ያሉ ወሳኝ መመዘኛዎችን ከግምት ያላስገባ መሆኑ እንዳስገረማቸውም ገልጸዋል።

‹‹ባለፉት 78 ዓመታት ያልነበረ አሠራር አሁን ሊመጣ ነው፤›› ያሉት እኚሁ የምክር ቤቱ ሠራተኛ፣ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት እንዳለበት የሚናፈሰው ወሬ ትክክል መሆኑን አሁን ለማመን እንደተገደዱ ተናግረዋል።

ሌላው የምክር ቤቱ አባል ደግሞ እየተካሄደ ባለው ሁኔታ እጅግ ማዘናቸውንና ‹‹ድርጊቱ ንግድ ምክር ቤቱን አሳልፎ እንደመስጠት የሚቆጠር ነው፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡ 

ከንግድ ምክር ቤቱ ደንብና መተዳደሪያ ደንብ ውጪ ጠቅላላ ጉባዔውን ለማካሄድ የተፈለገበት ምክንያትም ግልጽ ያለመሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡ በሥራ ላይ የሚገኘው የምክር ቤቱ ከፍተኛ አመራር ጠቅላላ ጉባዔውንና ምርጫውን ከአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ጋር በመነጋገር ለማካሄድ ተወስኗል ብሎ የሰጠው መግለጫ መንግሥት በንግድ ምክር ቤቱ ጉዳይ ጣልቃ ገብቷል የሚለውን አመለካከት እንድናጠናክራቸው ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት የንግድ ምክር ቤቱ የመተዳደሪያ ደንብ ለማሻሻል የተረቀቁ አንቀጾችም ከነባር አባላት ውጪ በአባልነት ያልተመዘገቡ፣ እንዲሁም የሚጠበቅባቸውን ዓመታዊ የአባልነት ክፍያ ያልከፈሉ ግለሰቦች በጠቅላላ ጉባዔው እንዲሳተፉና በምርጫው ላይም የመምረጥና የመመረጥ መብት እንዲያገኙ ያለመ መሆኑንም እኚሁ የንግድ ምክር ቤቱ አባል አስረድተዋል፡፡ 

በአጠቃላይ የምርጫው ሒደት እንደ አባል ግልጽ መረጃ ለማግኘት እንኳን እስከመቸገር ደርሰናል ያሉት እኚሁ አባል፣ በራሳቸው መንገድ ባደረጉት ማጣራትም ምርጫው በዕለቱ የሚገኙ ተሳታፊዎች በእጅ በሚሰጥ ድምፅ እንዲካሄድ ስለመወሰኑ ታውቋል፡፡ 

ንግድ ምክር ቤቱ ከኮሮጆ ምርጫ ወደ እጅ በመስጠት ምርጫ መግባቱ ለምን የሚል ጥያቄ ያቀረብንላቸውና በዚህ ምርጫ ሒደትና የንግድ ምክር ቤቱ መተዳደሪያ ደንብ እንዲሻሻል በኮሚቴ አባልነትና የተሰናባቹ የቦርድ አባል ዓለማየሁ ንጋቱ (ኢንጂነር)፣ የንግድ ምክር ቤቱ መተዳደሪያ ደንብ ምርጫን የተመለከቱና ተያያዥ አንቀጾች እንዲሻሻሉ የተደረጉት የአባላትን ተሳትፎ ለማጠናከርና ይረዳል ተብሎ ስለታመነበት ነው ይላሉ፡፡ 

ይህ ኮሚቴ መተዳደሪያ ደንቡን ለማሻሻል ያስፈለገበትን ምክንያት ምርጫው ሁሉንም የከተማ ነጋዴ የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የአባልነት ዕድል የሚሰጥና ምክር ቤቱን የሚያጠናክር የተወሰኑ የደንብ አንቀጾችን ማሻሻልና አዲስ መጨመር ኮሚቴው አስፈላጊ ሆኖ አግኝቷል በሚል ገልጾታል፡፡ 

በዚህ መሠረት በተሻሻለው ደንብ ውስጥ በአዲስ እንዲካተቱ ካደረጋቸው አንቀጾች መካከል የአባልነት ምዝገባው በተጨማሪም፣ ምክር ቤቱ ለዚህ አገልግሎት ብሎ በሚያዘጋጀው የኦንላይን የምዝገባ ሥርዓት የሚካሄድ ይሆናል የሚል ተካቷል፡፡ በተጨማሪም በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ባሉ በሁሉም ክፍለ ከተሞች ውስጥ የፀና የንግድ ፈቃድ ያላቸውና የአባልነት ክፍያ ያጠናቀቁ የነጋዴ ማኅበረሰቦችና ተወካዮች በጉባዔው ላይ በሙሉ ድመፅ የሚሳተፉ ይሆናልም ይላል፡፡ 

ለንግድ ምክር ቤቱ ሙሉ አባል የሆኑና ካለፉት ቦርድ አመራር የአገልግሎት ዘመናቸው ያልጨረሱ የቦርድ አባላት ክፍለ ከተማቸውን ወክለው በቀጥታ በምርጫ ይሳተፋሉ የሚል በማሻሻያነት መጨመሩንም ሰነዱ ያመለክታል፡፡ አሁን ባለው አካሄድ ግን ለነባር አባላት ጥሪ ባለመተላለፉ የተሻሻለውን አንቀጽ ራሱ ማስተግበር አለመቻሉ ታውቋል፡፡ 

የንግድ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ወ/ሮ መሰንበት ሸንቁጤ የምርጫ ሒደቱን በተመለከተ የተደረገውን ለውጥ አስመልክተው እንደገለጹት ደግሞ፣ አዲሱን አሠራር ለመተግበር ያነሳሳቸው በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ያለው የነጋዴ ቁጥርና ንግድ ምክር ቤቱ ያለው የአባላት ቁጥር የማይጣጣም በመሆኑ ነው፡፡ ይህንን ለማስተካከል አዲሱ አሠራር ያግዛል ይላሉ፡፡ 

ተሰናባቹ ቦርድ እስካሁን ከነበረው አሠራር ውጪ አዲስ አሠራር ለመዘርጋት የታሰበው በመንግሥት ጣልቃ ገብነት ነው የሚለውንም የማይቀበሉት መሆኑን የገለጹት ወ/ሮ መሰንበት፣ አሁን ያለንን የአባላት ቁጥር ይዘን መቀጠል አንችልም ብለን ለአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ አቅርበን እኛ ያቀረብነውን ሐሳብ ሊቀበለን ችሏል በማለት አዲሱ አሠራርና መመርያ የማሻሻሉ ተግባር የቦርድ ሐሳብ ስለመሆኑ አረጋግጠዋል፡፡ አያይዘውም፣ ‹‹መንግሥትን አዋጅ ተከትሎ መተዳደሪያ ደንብ ይወጣል፡፡ መተዳደሪያ ደንብ ደግሞ ዶግማ አይደለም መስተካከል አለብን በማለት ነው ያቀረብነው፤›› በማለትም ዕርምጃቸው ትክክል ስለመሆኑ ጠቅሰዋል፡፡ 

‹‹እንዲያውም አባላትን ለማበራከት የምናደርገው እንቅስቃሴ ሁላችንንም ሊያኮራ ይገባል፤›› በማለት የተወሰደውን ዕርምጃ ትክክል መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የንግድ ምክር ቤቱ ቦርድ፣ የንግድ ምክር ቤቱን ሕልውና የሚያናጋ ውሳኔ ስለማሳለፉ የሚጠቅሱ ያነጋገርናቸው አባላት፣ ተሻሻለ በተባለው መተዳደሪያ ደንብ ውስጥ ራሳቸውን ደግሞ ለመምረጥ የሚያስችላቸውን አንቀጽ ማካተታቸውንም ያስረዳሉ፡፡ 

በተለይ ከነባሩ አባላት ውጪ አዲስ አባል ሆነው የሚገቡ አባላት መምረጥና መመረጥ እንዲፈቀድላቸው ተደርጎ የተሻሻለው መመርያ ሕገወጥ በመሆኑ፣ አባላት በጠቅላላ ጉባዔው ላይ ይህንን ሕገወጥ ተግባር ሊያስቆሙ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡ 

እንዲህ ያለው ዕርምጃ ፈጽሞ የማይጠበቅና በንግድ ምክር ቤቱ ታሪክ ባልተለመደ ሁኔታ እንዲፈጸም የተደረገ መሆኑን የሚጠቅሱት ያነጋገርናቸው የምክር ቤቱ አባላት፣ ተሰናባቹ ቦርድ ባለፉት ዓመታት በምክር ቤቱ ውስጥ የተፈጸሙ የአሠራር ብልሽቶችን ለመሸፋፈንና አጀንዳ ለማስቀየር ያደረገው አሳዛኝ ውሳኔ ነው ያሉም አሉ፡፡ 

ዓለማየሁ (ኢንጂነር) በበኩላቸው፣ ተሰናባቹ ቦርድ እየወሰደ ያለው ዕርምጃ አባላት የማበራከት ሥራ በመሆኑ በዚህ ደረጃ ሊተች የማይገባ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ 

የንግድ ምክር ቤቱ ሠራተኛ ግን አሁን የተበለሻሸውን ነገር ማስተካከል ከባድ እንደሚሆን ጠቁመው፣ ነገሩን ለማስተካከል ዕድል ካለ በዕለቱ የሚገኙ የነባር አባላት ውሳኔ ምናልባት ለውጥ ሊያመጣ ይችላል የሚል ግምት አላቸው፡፡ 

ይህ በእንዲህ እንዳለ ምርጫው ለመካሄድ ጥቂት ቀናት የቀሩት ሲሆን፣ እስካሁን ባለው መረጃ በንግድ ቢሮ አስተባባሪነት ከየክፍለ ከተማው በዕጩነት የሚወከሉትን ለማሟላት ንግድ ቢሮው ምርጫ ያላካሄደባቸው ክፍለ ከተሞች ስላሉ ይህንን ለማካሄድ ያለው ጊዜ አጭር በመሆኑ ጠቅላላ ጉባዔውና ምርጫው ሊራዘም ይችላል በሚል እየተገለጸ ነው፡፡ 

በዚሁ ጉዳይ ላይ ከትናንት በስቲያ ጥር 28 ቀን 2017 ዓ.ም. የምርጫ አመቻች ኮሚቴው ተሰናባቹ የንግድ ምክር ቤቱ ቦርድና የንግድ ቢሮው ኃላፊዎች ስብሰባ መቀመጣቸውን ያገኘነው መረጃ ያስረዳል፡፡ 

ከሪፖርተር ምንጮች መረዳት እንደተቻለው በዕለቱ በሚደረገው ምርጫ ለፕሬዚዳንትነት የሚወዳደሩት ከየክፍለ ከተሞቹ ከተመረጡ 55 ሰዎች ውስጥ ከፍተኛ ድምፅ ያላቸው ይሆናሉ፡፡ 

በንግድ ምክር ቤቱ መተዳደሪያ ደንብ ምክትል ፕሬዚዳንት በመሆን የሚመረጡ ከዘርፍ ምክር ቤት የሚወከሉ ሲሆን፣ ይህም በቀጥታ ተፈጻሚ ይሆናል፡፡ እስካሁን በምክትል ፕሬዚዳንትነት ሲያገለግሉ የቆዩት አቶ አስፋው ሲሳይ የንግድ ምክር ቤቱ ምክትል ፕሬዚዳንት የአዲስ አበባ ዘርፍ ምክር ቤቱን በመወከል የተሰየሙ መሆኑ ይታወቃል፡፡ 

እንደ ምንጮች ገለጻ ምክትል ፕሬዚዳንቱ በዚህ ምርጫ ላለመሳተፍ ራሳቸውን ያገለሉ ሲሆን፣ አዲስ የሚመረጡ የዘርፍ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት በቀጥታ ምክትል ፕሬዚዳንት ይሆናሉ ተብሏል፡፡ ከነባር ቦርድ ውስጥ ፕሬዚዳንቷ ወ/ሮ መሰንበት ሸንቁጤ ከምርጫ ዘመን በላይ በማገልገላቸው ተሳታፊ እንደማይሆኑ የታወቀ ሲሆን፣ ሁለት የቦርድ አባላት ግን ለፕሬዚዳንትነት ሊወዳደሩ እንደሚችሉ ተጠቁሟል፡፡ የምርጫ አመቻች ኮሚቴው ለፕሬዚዳንትነት ለመወዳደር ዕጩ ሆነው ከሚቀርቡት ውስጥ የምርጫ ቀኑ ከመድረሱ በፊት በተለያዩ መመዘኛዎች ሦስት ብቻ ተለይተው በዕለቱ እንዲቀርቡ መመርያ የተሰጠ ለመሆኑ ታውቋል፡፡