
January 8, 2025

እያንዳንዳቸው 163 ካሬ ሜትር ላይ ያረፉ የ54ቱንም የአፍሪካ አገሮች የሚወክል ገጽታ የተላበሱ ቪላዎችን የያዘው፣ የኩሪፍቱ ሪዞርትና ስፓ የአፍሪካ መንደር ቅዳሜ ታኅሳስ 26 ቀን 2017 ዓ.ም. ተመርቋል።
በልዩነት የአፍሪካን አገሮች ባህልና እሴት እንዲያጎላ ሆኖ በሸገር ከተማ በተለምዶ አሸዋ ሜዳ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ተገንብቶ ሥራውን የጀመረው ኩሪፍቱ ሪዞርትና ስፓ ምን ያህል የግንባታ ጊዜና በጀት እንደፈጀ መሥራችና ሥራ አስፈጻሚ የሆኑት አቶ ታዲዮስ ጌታቸው ከመግለጽ ተቆጥበዋል።
ቅዳሜ ታኅሳስ 26 ቀን 2017 ዓ.ም. የኩሪፍቱ ሪዞርትና ስፓ የአፍሪካ መንደር የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ በተገኙበት በይፋ ተመርቋል።
የተለያዩ ከፍተኛ ባለሥልጣናትና ታዋቂ ግለሰቦች በተገኙበት የምረቃ ሥነ ሥርዓትን በኢትዮጵያ የአሜርካ አምባሳደር የሆኑት ኸርቪን ማሲንጋ ተገኝተው ጉብኝት አድርገዋል።
ሪዞርትና ስፓው የአፍሪካ አገሮችን ታሪክ፣ ባህልና እሴት እንዲያጎሉ ተደርጎ በተገነባው የአፍሪካ መንደር እያንዳንዳቸውን የአፍሪካ ኅብረት መሥራቾች ስም የተሰየሙ የኮንፈረንስ ጉባዔ አዳራሾችንም አካትቷል።