
ከ 6 ሰአት በፊት
ተመራጩ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ዋይት ሐውስ ከመመለሳቸው ጥቂት ሳምንታት ቀደም ብለው የፓናማ ቦይን እና የዴንማርክ አካል የሆነችውን ራስ ገዟን ግሪንላንድን ‘ለመጠቅለል’ ወታደራዊ እርምጃ አማራጭ አለመሆኑን በይፋ አለመግለጻቸው ብዙዎችን አስደንግጧል።
ሁለቱም ቦታዎች ለአሜሪካ ምጣኔ ሀብታዊ ደኅንነት ወሳኝ መሆናቸውን ትራምፕ ገልጸዋል።
ትራምፕ በዚህ ጉዳይ ውስጥ የአሜሪካ ሠራዊትን በይፋ ሲጠቅሱ የመጀመሪያቸው ነው። በተጨማሪም ካናዳን ወደ አሜሪካ ለማካተት ምጣኔ ሀብታዊ ጫናን እንደሚጠቀሙ ተናግረዋል።
ፓናማ፣ ግሪንላንድ፣ ዴንማርክ እና ካናዳ ለዚህ የትራምፕ አስተያየት ቁጣ የተቀላቀለበት ምላሽ ሰጥተዋል።

የፓናማ ቦይ
በ20 ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ የቦዩን ግንባታ ኃላፊነት ከወሰደች እና ከአስርት ዓመታት ድርድር በኋላ ዩናይትድ ስቴትስ በ1999 ቦዩን ሙሉ ለሙሉ ለፓናማ አስረክባለች።
ትራምፕ አሁን ላይ የብሔራዊ ደኅንነት ስጋቶችን በመጥቀስ ቦዩ እንዲመለስ ይፈልጋሉ።
“የፓናማ ቦይ ለአገራችን ወሳኝ ነው። በቻይና ጥቅም ላይ እየዋለ ነው። የፓናማ ካናልን ለፓናማ ሰጠን እንጂ ለቻይና አልሰጠናትም። ስጦታውን አላግባብ ተጠቅመውበታል” ብለዋል ትራምፕ።
ይፋዊ ቁጥሮች ግን የሚያመለክቱት ከዚህ በተቃራኒ ነው። ቦዩ ከሚያስተናግደው 72 በመቶውን የአሜሪካ ጭነት እያስተናገደ ነው። የቻይና ጭነት 22 በመቶ ገደማ በመሆን ሁለተኛ ደረጃ ላይ መቀመጡን የፓናማ ቦይ ባለሥልጣን አስታውቋል። ቻይና በፓናማ ውስጥ ትልልቅ ኢንቨስትመንቶች አሏት።
ተንታኞች እንደሚሉት ከሆነ የፓናማ ቦይ ለአሜሪካ የፓስፊክ ውቅያኖስ ንግድ ብቻ ሳይሆን ወደፊት ከቻይና ጋር ወታደራዊ ግጭት ከተፈጠረም ወሳኝ ቦታ ይሆናል።

የአሜሪካን የጭነት መርከቦች ቦዩን ሲጠቀሙ ከፍተኛ ክፍያ ትጥልባቸዋለች ሲሉ ትራምፕ ከዚህ ቀደም ፓናማን ወቅሰዋል።
ትሩዝ ሶሻል በተሰኘው ትራምፕ በባለቤትነት በሚያስተዳድሩት የራሳቸው ማኅበራዊ ሚዲያ መድረክ ገጻቸው ላይ ደግሞ በፓናማ ቦይ መሃል የአሜሪካ ባንዲራ ተተክሎ የሚያሳይ ምሥል ለጥፈዋል።
የፓናማ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሃቪየር ማርቲኔዝ-አቻ በፓናማ ሲቲ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የፓናማ ቦይ ሉዓላዊነት ለድርድር የማይቀርብ ነው ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
“ቦዩን የሚቆጣጠሩት ብቸኛ እጆች የፓናማውያን ነው። በዚሁ መልኩም ይቀጥላል” ብለዋል ማርቲኔዝ-አቻ።
- ከቢቢሲ አማርኛ ዜና እና ታሪኮች በቀጥታ እንዲላክልዎ የዋትስአፕ ቻናላችን አባል ይሁኑ5 ታህሳስ 2024
- በሊቢያ “ለባርነት ጨረታ” የቀረበችው ኢትዮጵያዊቷ ነሒማ9 ጥር 2025
- የመሬት መንቀጥቀጦች አስከፊ የሚሆኑባቸው 7 ምክንያቶች9 ጥር 2025

ግሪንላንድ
ግሪንላንድ በዴንማርክ ስር ያለ ራሱን የቻለ ግዛት ሲሆን፣ በዓለም ላይ በጣም አነስተኛ ሕዝብ ከሚኖርባቸው አካባቢዎች አንዱ ነው።
ትራምፕ በመጀመሪያው የፕሬዝዳንትነት ዘመናቸው በአውሮፓውያኑ 2019 ነበር ግሪንላንድን የመግዛት ሀሳብን ያቀረቡት።
የዴንማርክ ጠቅላይ ሚንስትር ሜቴ ፍሬድሪክሰን ከመጪው የትራምፕ አስተዳደር ጋር ለመሥራት ፍቃደኛ መሆናቸውን ገልጸው፤ ግሪንላንድ ግን የሕዝቦቿ ነች ሲሉ ተናግረዋል።
“ግሪንላንድ የግሪንላንድ ሕዝቦች ናት። ኩሩ ሕዝብ ነው፤ የራሱ የሆነ ቋንቋ እና ባህልም አለው። ቀደም ሲል እንደተገለጸው ግሪንላንድ አይሸጥም” ሲሉ ፍሬድሪክሰን ተናግረዋል።
የትራምፕ ፍላጎት የማያስገርም ይሆናል። ግዛቱ በተፈጥሮ ሃብት የበለፀገ ነው። የዴንማርክ የጂኦሎጂካል ሰርቬይ እና የግሪንላንድ ድረ-ገጽ በምድር ላይ ትልቁ በሆነው ደሴት ውድ የሆኑ ማዕድናት እና የኢነርጂ ሃብቶች ተዘርዝረዋል።
እንደ ወርቅ እና ፕላቲኒየም ያሉ ውድ ብረቶች፤ ሊቲየም፣ ቲታኒየም እና ሌሎች ተፈላጊ የምድር ንጥረ ነገሮችን ጨምሮ እንደ ድንጋይ ከሰል እና ዩራኒየም ያሉ የኃይል ማዕድናት እና እንደ አልማዝ እና ሩቢ ያሉ የከበሩ ድንጋዮችም በደሴቲቱ ይገኛሉ።

በተጨማሪም ከፍተኛ የነዳጅ እና የጋዝ ክምችቶች እንዳለ ተጠቁሟል። በአብዛኛው ገና ያልተመረመሩ እና ጥቅም ላይ ሊውሉ የማይችሉ ቢሆንም ግን በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የበረዶ ግግር መቅለጥ ምርቱን ለማውጣት በር ሊከፍት ይችላል።
ለጊዜው በባትሪ ምርት ውስጥ በብዛት ጥቅም ላይ የሚውሉት ውድ ብረቶች መኖራቸው ግሪንላንድን ተፈላጊ ያደርጋታል። እንደ ዓለም ባንክ መረጃ ከሆነ የአሜሪካን ብቻ ሳይሆን የቻይናን እና የተቀረውን ዓለም ፍላጎት ለማሟላት ማዕድናቱን የማውጣት ሥራ በ2050 በአምስት እጥፍ እንደሚጨመር ተንብዮ ነበር።
ደሴቷ በሩሲያ እና በዩናይትድ ስቴትስ መካከል ባለው ቦታ በመገኘቷ ምክንያትም ሞስኮም ክልሉ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ትረዳለች። ዋሺንግተን በደሴቱ ላይ የቅድሚያ ማስጠንቀቂያ የባለስቲክ ሚሳኤል ሥርዓትን ያዘ የጦር ሰፈር አላት።
ግሪንላንድ ራሷን እንድትችል በሚወተውቱት ጠቅላይ ሚኒስትር ሙቴ ቡሩፕ ኤጌዴ ትመራለች። ደሴቲቱ ለሽያጭ እንደማትውል በግልጽ ተናግረው የነፃነት ሕዝበ ውሳኔ በሚያዝያ ወር ከሚካሄደው የፓርላማ ምርጫ ጎን ለጎን ሊካሄድ እንደሚችል ጠቁመዋል።
ካናዳ

ትራምፕ በቅርብ ሳምንታት ትልቋን ጎረቤታቸውን ካናዳን ደጋግመው ተንኮስ በማድረግ 51ኛዋ የአሜሪካ ግዛት እንደምትሆን እና ድንበራቸውንም “ሰው ሠራሽ” ብለው እስከመጥራት ደርሰዋል።
ተመራጩ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ለካናዳ ጥበቃ ሲባል የሚወጣውን በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር በመተቸት የካናዳ መኪኖች፣ እንጨት እና የወተት ተዋጽኦዎችን ላይ ፈተና ደቅነዋል። ትራምፕ ዋይት ሐውስ ሲገቡ ልክ እንደ ሜክሲኮ ሁሉ ካናዳ ወደ አሜሪካ በምትልካቸው ሸቀጦች ላይ 25 በመቶ ታሪፍ እንደሚጥሉ ዝተዋል።
ትራምፕ በቅንጡው ማር አ ላጎ የመኖሪያ ይዞታቸው ውስጥ በሰጡት ረዥም ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት የሜክሲኮ እና የካናዳ ድንበሮችን አቋርጠው ወደ አሜሪካ የሚገቡ ዕጾች ላይም ያላቸውን ስጋት አንስተዋል።
በአሜሪካ እና በካናዳ ድንበር የተያዘው የፌንታኒል መጠን በደቡብ አቅጣጫ ካለው ድንበር አንጻር በእጅጉ ያነሰ መሆኑን የአሜሪካ መረጃ ያሳያል።
ካናዳ ድንበር ተሻጋሪ የተደራጁ ወንጀሎችን ዒላማ ለማድረግ የተጠናከረ ክትትል እና የጋራ ኃይልን በማከል በድንበር አካባቢ አዳዲስ የቁጥጥር እርምጃዎችን ተግባራዊ ለማድረግ ቃል ገብታለች።
የካናዳ ጠቅላይ ሚንስትር ጀስቲን ትሩዶ በበኩላቸው ትራምፕ ሁለቱን አገራት ለመቀላቀል “ኢኮኖሚያዊ ኃይል” ይጠቀማሉ በማለት ተችተዋል።
ወሬ ብቻ ወይስ እውነታ?
የዩናይትድ ስቴትስ የቀድሞ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ጄምስ ጄፍሪ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ከሆነ ትራምፕ ለዓለም አቀፍ አጋሮቻቸው እና ለአገር ውስጥ ደጋፊዎቻቸው መልዕክት እያስተላለፉ ነው።
እስካሁን ባለው ሁኔታ በዩናይትድ ስቴትስ በኩል የአውሮፓ አጋሮቿ የዓለም አቀፍ ደኅንነትን ለመጠበቅ በቂ ጥረት ባለማድረጋቸው ብስጭት እንዳለ ተናግረዋል።
ጄፍሪ የወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ዕድል ጠባብ መሆኑን ጠቅሰዋል።
“ወደ ግሪንላንድ አንዘምትም፤ ወደ ካናዳ አንዘምትም፣ የፓናማ ካናልንም አንይዝም። ይህ ምን ያህል አለመረጋጋት ይፈጥራል የሚለው ሌላ ጥያቄ ነው” ሲሉም አክለዋል።
“የዓለም አቀፉ ሥርዓት ስጋት ዶናልድ ትራምፕ አይደለም፣ የዓለም አቀፍ ሥርዓት ስጋት ሩሲያ እና ቻይና ናቸው” ሲሉ ጄፍሪ ተናግረዋል።
የለንደኑ ዘ ኢንዲፔንደንት ጋዜጣ የፖለቲካ አርታኢ ዴቪድ ማዶክስ በበኩሉ ትራምፕ በቁም ነገር መታየት እንዳለበት ይሰማዋል።
“ይህ ግዛት የማስፋፋት ፍልጎት ያለው ትራምፕ ነው። የአሜሪካን አሻራ ማሳደግ ይፈልጋል። እነዚህ ትልቅ ስጋቶች ናቸው” ሲል ማዶክስ ለቢቢሲ ተናግሯል።
“ከመጀመሪያው የትራምፕ አስተዳደር በተለየ መልኩ ለቀሪው ዓለም ያለመረጋጋትን ይፈጥራል” ሲል አክሏል።