በአንድ በተረጋጋጠ ቪዲዮ ፖሊስ ተቃዋሚን ሲመታ ይታያል

ከ 5 ሰአት በፊት

በቻይና ሰሜን ምዕራብ በምትገኝ ከተማ የአንድ ታዳጊ ልጅ በሚማርበት ትምህርት ቤት ህይወቱ ማለፉን ተከትሎ ከፍተኛ ተቃውሞ መቀስቀሱን ቢቢሲ ከቪዲዮዎች ማረጋገጥ ችሏል።

በማህበራዊ ሚዲያዎች በተለቀቁት ቪዲዮዎች ላይ እንደሚታየው በሻንሺ ግዛት በምትገኘው በፑቼንግ አንዳንድ ተቃዋሚዎች ወደ ፖሊሶች ቁሳቁሶችን፤ ፖሊሶች ደግሞ ተቃዋሚዎችን ሲደበድቡ ታይተዋል።

ታዳጊው ታህሳስ 24/ 2017 ዓ.ም በትምህርት ቤቱ ማደሪያ ውስጥ በደረሰ አደጋ ህይወቱ አልፏል በማለት ባለስልጣናት ተናግረዋል። ህይወቱ ማለፉን ተከትሎ ግን በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ የተሰጠው ምክንያት ሽፋን ነው የሚል ውንጀላ መሰራጨት ጀመረ።

ይህንን ተከትሎ የተቀስቅሰው ተቃውሞ ለቀናት ከቀጠለ በኋላ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ በኃይል እንዲረግብ ሆኗል። ቢቢሲ ባለፉት ጥቂት ቀናት በፑቼንግ ተቃውሞ ስለመኖሩ ምንም ተጨማሪ መረጃ አላገኘም።

በቻይና ውስጥ ህዝባዊ ሰልፎች የተለመዱ ናቸው። እአአ በ2022 የነጭ ወረቀት በሚል የኮቪድ ፖሊሲዎችን በመቃወም ህዝቡ ድምጹን ባሰማበት ወቅት ግን ባልተለመደ መልኩ በቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ እና በፕሬዚዳንት ዢ ጂንፒንግ ላይ ትችት ከተሰነዘረ ወዲህ ባለስልጣናት ለተቃውሞች ትዕግስት አልባ እየሆኑ ነው።

በቻይና ፑቼንግ ተቃዋሚ በደም የተጨማለቀውን ጭንቅላቱን ወረቀት እየጠረገ ይታያል

በፑቼንግ የተካሄደውን ተቃውሞ የመንግሥት መገናኛ ብዙሃን በዝምታ አልፈውታል። ማንኛውም ቪዲዮ ወይም ሰልፎቹን የሚመለከት ጉዳይ ከቻይና ማህበራዊ ሚዲያ በአብዛኛው ሳንሱር ተደርጎባቸዋል።

በርካታ ቪዲዮዎች ከቻይና ሾልከው በኤክስ ላይ ተለጥፈዋል።

እነዚህ ቪዲዮዎች የተቀረጹት በፑቼንግ የሙያ ትምህርት ማዕከል መሆኑን ቢቢሲ አረጋግጧል። ሰልፎቹ ከመከሰታቸው በፊት ምንም አይነት ተቃውሞ የሚያሳዩ ተመሳሳይ ተንቀሳቃሽ ምስሎች በበይነ መረብ ላይ እንዳልነበሩ አረጋግጧል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው የፑቼንግ መንግስት ቃል አቀባይ ተወካይ ተቃውሞ አልነበረም ሲሉ አስተባብለዋል። ምላሽ ለማግኘት በተደጋጋሚ የስልክ ጥሪ ቢደረግም ምንም መልስ አልተገኘም።

በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ የአካባቢው ባለስልጣናት በሰጡት መግለጫ ዳንግ የተባለው ታዳጊ በፑቼንግ በሚገኘው የትምህርት ማዕከል የሦስተኛ ዓመት ተማሪ እንደነበረ ገልጸዋል።

ዳንግ ከመሞቱ በፊት ሌሎች ተማሪዎች ማደሪያ ክፍላቸው ውስጥ ሲጨዋወቱ ተረብሾ በሌሊት ከእንቅልፉ እንደነቃ ተገልጿል። ከአንድ ልጅ ጋር ወደ ጭቅጭቅ የገባ ቢሆንም ጉዳዩ በትምህርት ቤቱ ኃላፊ ተፈትቷል ብለዋል።

በዚያው ምሽት አስከሬኑ በሌላ ተማሪ በማደሪያ ክፍሉ ወለል ላይ ተገኝቷል።

“ተማሪው ከትምህርት ቤት ከፍታ ቦታ ላይ በወደቀበት አደጋ” ህይወቱ ማለፉን መግለጫው ገልጿል። የፖሊስ እና የአስከሬን ምርመራ ማካሄዱን እና “በአሟሟቱ ዙሪያ ምንም ወንጀል አልተፈጸመም” ሲል አክሏል።

ሆኖም ከአሟሟቱ ጀርባ ሌላ ታሪክ እንዳለ እና ትምህርት ቤቱ እና ባለስልጣናት እውነቱን እየደበቁ ነው የሚሉ ውንጀላዎች ለቀናት በይነ መረብ ላይ ሲሽከረከሩ ቆይተዋል።

አንድ ገጽ ላይ ዳንግ ራሱን የገደለው ቀደም ሲል ከተጣላው ልጅ በተሰነዘረበት ጥቃት እና ማስፈራሪ ነው እንደሆነ ማስረጃ ሳያቀርብ ገልጿል።

በዳንግ አስከሬን ላይ የደረሰው ጉዳት ከባለሥልጣናቱ መግለጫ ጋር የማይጣጣም እና አስከሬኑን ለረጅም ጊዜ እንዳይመረምሩ መከለከላቸውን ቤተሰቦቹ መግለጻቸውንም ያልተረጋገጡ አስተያየቶች እየተናፈሱ ነው።

ጉዳዩ በፑቼንግ ብዙዎችን ያስቆጣ ሲሆን ይህንን ተከትሎም በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ለተቃውሞ አነሳስቷል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በቻይና ውስጥ የታዳጊዎች ጥቃት በጣም አሳሳቢ ርዕሰ ጉዳይ ከመሆን ባለፈ በዚህ ምክንያት ቀደም ሲልም ተማሪዎች መሞታቸው ተቃውሞዎችን ቀስቅሰዋል። ባለፈው ወር አንድ የቻይና ፍርድ ቤት የክፍል ጓደኛቸውን በገደሉ ሁለት ታዳጊዎች ላይ ረዥም የእስር ቅጣት አስተላልፏል።

በፑቼንግ ሰልፍ ላይ አንድ ተቃዋሚ ወደ ፖሊስ አባል ድንጋይ ሲወረውር

ሰኞ ዕለት ኤክስ ላይ የተለጠፉ እና በፑቼንግ የሙያ ትምህርት ማዕከል መሆናቸውን ቢቢሲ ያረጋገጣቸው ተንቀሳቃሽ ምስሎች ላይ በርካቶች በታዳጊው ሞት ሃዘናቸውን ሲገልጹ አሳይተዋል።

በትምህርት ቤቱ ደጃፍ ላይ አበባዎችን ካስቀመጡ እና የገንዘብ ድጋፍ ካደረጉ በኋላ ከትምህርት ቤቱ ህንጻ ጣሪያ ላይ ወረቀቶችን በመወርወር ባህላዊውን የሀዘን ስነ ስርዓት አከናውነዋል።

በሌሎች በበይነ መረብ በተሰራጩ ተንቀሳቃሽ ምስሎች ደገሞ አብዛኛዎቹ ወጣት የሚመስሉ ሰልፈኞች “እውነታው ይነገረን”በማለት ህንጻውን በመክበብ ከፖሊስ ጋር ተጋጭተዋል።

በአንድ በተረጋገጠ ቪዲዮ ላይ የትምህርት ቤቱ ኃላፊ ላይ ተቃዋሚዎች እየጮሁ ሲጎነትሉት ያሳያል። ሌሎች ቪዲዮዎች ደግሞ በግቢው ውስጥ የወደሙ ቢሮዎችን እና በትምህርት ቤቱ መግቢያ በተቃዋሚዎች መዘጋቱን ያሳያሉ።

ቀጥሎ ስለተፈጠረው ነገር ያለው መረጃ አነስተኛ ሲሆን፤ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የሚወጡት ሪፖርቶች እንደሚጠቁሙት ግን ከቅርብ ቀናት ወዲህ በርካታ ፖሊሶች በፑቼንግ በመሰማራታቸው ተጨማሪ ሰላማዊ ሰልፎች ሪፖርት አልተደረጉም።

ህብረተሰቡ “አሉባልታ እንዳይፈጥር፣ እንዳያምን እና እንዳያሰራጭ” ባለስልጣናት አሳስበዋል።