የ9/11 ጥቃት ዋነኛ አቀናባሪ የተባለው ካሊድ ሼክ መሃመድ
የምስሉ መግለጫ,የ9/11 ጥቃት ዋነኛ አቀናባሪ የተባለው ካሊድ ሼክ መሃመድ

ከ 5 ሰአት በፊት

በአሜሪካ የተፈጸመውን የ9/11 የሽብር ጥቃት አቀናብረዋል የተባሉ ግለሰቦች ለችሎቱ ጥፋተኛ ነን ብለው እንዳይመሰክሩ መንግሥት ያቀረበው እግድ ተሳካለት።

ካሊድ ሼክ መሃመድ እና ሌሎች ሁለት ተከሳሾች የሞት ፍርድ እንዳይፈረድባቸው በምትኩ የተከሰሱባቸውን ወንጀሎች በሙሉ አምነው ለመቀበል ስምምነት ላይ ደርሰው ነበር።

የአሜሪካ መንግሥት በበኩሉ የጥፋተኝነት ምስክርነታቸው ተቀባይነት ካገኘ መንግሥትም ሆነ የአሜሪካ ህዝብ ሊጠገን የማይችል ጉዳት እንደሚደርስባቸው በመከራከር ለፌደራል ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት አቤቱታውን አስገብቷል።

ይሄንንም ተከትሎ ችሎቱን እየዳኙ ያሉት ሶስት ዳኞች ጉዳዩን ለማጤን ተጨማሪ ጊዜ እንደሚያስፈልጋቸው አስታውቀዋል። ሆኖም የችሎቱ መዘግየት “በምንም መልኩ በጉዳዩ ላይ የመጨረሻ ውሳኔ ተደርጎ መወሰድ የለበትም” ሲሉ አሳስበዋል።

ከዚህ ቀደም የአገሪቱ መከላከያ ሚኒስትር ሎይድ ኦስቲን ስምምነቶቹ እንዲሻሩ ለወታደራዊ ዳኛ እና የይግባኝ ሰሚ ጉባኤ ያቀረቡት ይግባኝ ውድቅ ተደርጎ ነበር።

በአውሮፓውያኑ መስከረም 11፣ 2001 ጥቃት አድራሾች የመንገደኞች አውሮፕላንን በመጥለፋቸው በኒውዮርክ የዓለም ንግድ ማዕከል እና ከዋሽንግተን ወጣ ብሎ በሚገኘው ፔንታጎን ላይ ተከስክሰው 3 ሺህ ያህል ሰዎች ሞተዋል። ሌላኛው አውሮፕላን ውስጥ አንድ መንገደኛ በመታገላቸው በፔንስልቫንያ በሚገኝ ሜዳ ላይ ተከስክሷል።

ጓንታናሞ ቤይ

ይህንን ጥቃት በማቀናበር ክስ የተመሰረተባቸው ሶስቱ ግለሰቦች ከ20 ዓመት በላይ በአሜሪካ በእስር ላይ ቆይተዋል። የቅድመ ችሎት ሰሚም ከአስር ዓመት በላይ ቆይቷል።

በዚህ ወቅትም ሶስቱ ግለሰቦች ጥፋተኛ ነን ብለው ያመኑት በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ በሲአይኤ ለረጅም ጊዜ በደረሰባቸው የከፋ ማሰቃየት በኋላ ነው የሚሉ ክርክሮች ተሰምተዋል።

በአውሮፓውያኑ 2003 በቁጥጥር ስር የዋለው መሃመድ በሚስጥራዊ የሲአይቤት ከታሰረ በኋላ 183 ጊዜ ያህል በውሃ እንዲሰጥም እና እንዲታፈን የማድረግ ስቃይ ተፈጽሞበታል። እሱን ጨምሮ ሌሎች ደግሞ እርቃናቸውን ማጋለጥ ጨምሮ፣ እንቅልፍ ማሳጣት እና ሌሎች “የረቀቁ የምርመራ ዘዴዎች” ተግባራዊ ሆኖባቸዋል ተብሏል።

በ9/11 ጥቃት ቤተሰቦቻቸውን ያጡ አንዳንድ ግለሰቦች ስምምነቱን ግልጽነት የጎደለው ያሉ እንዳሉ ሁሉ ሌሎች ደግሞ ውስብስብና ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረውን የፍርድ ሂደት መቋጫ አድርገው የቆጠሩት አልታጡም።

የመሃመድን የጥፋተኝነት ምስክርነት ለመስማት በኩባ ወደሚገኘው የአሜሪካ የባህር ኃይል ጦር ሰፈር ጓንታኖሞ ቤይ የተጓዙ አንዳንድ ግለሰቦች ፍርዱ በመዘግየቱ የተሰማቸውን ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

“የአሜሪካ መንግሥት በዚህ ውሳኔው በ9/11 ቤተሰቦቻቸውን ያጡ ሰዎችን አሳዝኗል። ትክክለኛው ነገር ለማድረግ እድሉ ቢኖራቸውም ያደረጉት ተቃራኒውን ነው” ሲል በጥቃቱ የቤተሰብ አባላትን ያጣው ቶም ሬስታ ተናግሯል።