
ከ 4 ሰአት በፊት
አሜሪካ በቀድሞ የናይጄሪያ የነዳጅ ሚኒስትር ዲኤዛኒ አሊሰን ማዱኬ እና በሌሎች አጋሮቻቸው ተመዝብሮ ወደ አገሬ ገብቷል ያለችውን 50 ሚሊዮን ዶላር መመለሷ ተገለጸ።
ሚኒስትሮቹ በሕገወጥ መንገድ ከናይጄሪያ አስወጥተውታል የተባለው ወደ 53 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ለሕዝባዊ አገልግሎቶች እንደሚውል የናይጄሪያ የፍትህ ሚኒስቴር አስታውቋል።
ሚኒስትሯ የናይጄሪያን የነዳጅ ኩባንያ በሚመሩበት ወቅት የተለያዩ ውሎችን ለመስጠት ጉቦ እንደተቀበሉ እና ይህንንም ራሳቸውን እና ሌሎችን ለማበልጸግ እንደተጠቀሙበት ባለሥልጣናቱ ገልጸዋል።
አሜሪካ ገንዘቡ ጋላክቲካ ስታር የተሰኘ 65 ሜትር ርዝማኔ ያለው መርከብ እንዲሁም በካሊፎርኒያ እና በኒው ዮርክ ቅንጡ ቤቶችን ለመግዛት ውሏል ብላለች።
የ64 ዓመቷ የቀድሞ ሚኒስትር አሊሰን ማዱኬ እነዚህን የምንዝበራ ውንጀላዎችን ውድቅ አድርገዋል።
ሚኒስትሯ በሕገወጥ መንገድ አካብተውታል የተባለው ሃብት መኖሪያቸውን ባደረጉባት ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ እየተጣራ ይገኛል።
ከሁለት ዓመት በፊት በዩናይትድ ኪንግደም ሉዊ ቩተን ከተሰኘው ምርት የቅንጦት እቃዎች ስጦታ፣ የግል ትምህርት ቤት ክፍያዎች እንዲሁም 127 ሺህ ዶላር ጥሬ ገንዘብ ጋር በተያያዘ በጉቦ ወንጀል ተከሰዋል።
በቀድሞው ፕሬዚዳንት ጉድላክ ጆናታን አስተዳደር ውስጥ ቁልፍ ሰው የነበሩት ፖለቲከኛዋ የነዳጅ ላኪዎች ቡድን፣ ኦፔክ የመጀመሪያ ሴት ፕሬዚዳንትም ሆነው አገልግለዋል።
በናይጄሪያ የነዳጅ ሚኒስትርነትም ከአውሮፓውያኑ 2010 እስከ 2015 አገልግለዋል። ቀደም ሲል የትራንስፖርት ሚኒስትር፣ የማዕድን እና ብረታ ብረት ልማት ሚኒስትር ነበሩ።
- በሰሜን ወሎ በከፍተኛ የምግብ እጥረት ህፃናትን ጨምሮ ሰዎች መሞታቸውን የዳሰሳ ጥናት አመለከተ10 ጥር 2025
- እየፈረሰች ያለችውን አዲስ አበባ በመሰንቆ ‘እየገነባት’ ያለው ሀዲስ ዓለማየሁከ 6 ሰአት በፊት
- ሎስ አንጀለስ ሰደድ እሳቱን ለማጥፋት በመቶዎች የሚቆጠሩ እስረኞችን አሰማራችከ 5 ሰአት በፊት
የአሜሪካ የፍትህ መሥሪያ ቤት በቀድሞ ሚኒስትሯ እና በአጋሮቻቸው በሕገወጥ መንገድ ወደ አሜሪካ ገብቶ በንብረት ላይ ውሏል ያለውን ገንዘብ በተመለከተ ሁለት የፍትሐ ብሔር ክሶች የመጨረሻ ውሳኔ ከሁለት ዓመታት በፊት አስታውቆ ነበር።
አርብ፣ ጥር 2/ 2017 ዓ.ም. አሜሪካ እና ናይጄሪያ 52.88 ሚሊዮን ዶላር ወደ ምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር እንደሚመለስ አረጋግጠዋል።
ይህ ከቀድሞዋ ሚኒስትር ጋር በተገናኘ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ናይጄሪያ የሚመለስ ገንዘብ ይሆናል ሲል ሮይተርስ ዘግቧል።
በናይጄሪያ መዲና በተካሄደው የፊርማ ሥነ ሥርዓት ላይ የሀገሪቱ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ እና የፍትህ ሚኒስትር ላጢፍ ፋግቤሚ የገንዘቡ መመለስ ሙስናን ለመዋጋት በሚደረገው ትግል ውስጥ ትልቅ እርምጃ ነው ብለዋል።
ከገንዘቡ 50 ሚሊዮን ዶላር በዓለም ባንክ በኩር የገጠር የኤሌክትሪክ አገልግሎት ፕሮጀክቶችን ለማስፋፋት የሚውል እንደሆነ ፋግቤሚ ተናግረዋል።
ቀሪው 2.88 ሚሊዮን ዶላር ደግሞ የፍትህ ሥርዓቱን ለማጠናከር እንዲሁም የፀረ-ሙስና ጥረቶችን ለማበረታታት ለዓለም አቀፉ የፍትህ ተቋም እንደሚላክ ተገልጿል።
