ሻታ አል-ሳባግህ
የምስሉ መግለጫ,ሻታ አል-ሳባግህ

12 ጥር 2025

የ21 ዓመቷ ሻታ አል-ሳባግህ ጀኒን በዌስት ባንክ በሚገኘው ጀኒን ለልጆቿ ቸኮሌት ለመግዛት ነበር ከቤት የወጣችው።

ጋዜጠኛ ለመሆን ትማር ነበር። በፍልስጤማውያን ላይ ስለሚደርሰውን በደል መጻፍ ነበር ምኞቷ።

ከእናቷ፣ ከሁለት የአክስቷ ልጆችና ከዘመዶቿ ጋር አብራ ነው የምትኖረው።

ገበያ ወጥታ ሳለ ተተኮሰባት።

“ዛሬ አብረን እናመሻለን እያለች ነበር” ስትል እናቷ ታስታውሳለች።

እናቷ ኡም አል-ሞታሲም አሁንም ሐዘን ሰብሯታል።

“ዓይኗን እንደከፈተች ነበረች። እያየችኝ ነበር የመሰለኝ። በጀርባዋ ተንጋላ ደም እየፈሰሳት ነበር” ትላለች።

“መጮህ ጀመርኩ። ተው! መተኮሱን አቁሙ። ልጄኮ ሞታለች አልኳቸው። ግን ለአስር ደቂቃ ያህል ተኩሱ ቀጠለ” ትላለች እናት።

ሻታ በደም ተለውሳ ሕይወቷ አለፈ።

የሻታ ቤተሰብ የፍልስጤም አስተዳደር የፀጥታ ኃይሎችን ነው ተጠያቂ የሚያደርገው።

በአካባቢው የሚንቀሳቀሱት የፍልስጤም አስተዳደር የፀጥታ ኃይሎች ናቸው።

“የፍልስጤም አስተዳደር የፀጥታ ኃይሎች ናቸው። ሌላ ማንም አይሆንም። በእኛ አካባቢ ያሉት እነሱ ናቸው” ይላሉ የሻታ ቤተሰቦች።

የፍልስጤም አስተዳደር የፀጥታ ኃይሎች ግን ተጠያቂዎቹ “ሕገ ወጦች ናቸው” ይላል።

ሕገ ወጦች የሚሏቸው የጀኒን ባታሊዮን አባላትን ነው። እነዚህ ታጣቂዎች ከፓለስቲንያን ኢስላሚክ ጂሃድ እና ከሐማስ የተውጣጡ ናቸው።

የፍልስጤም የፀጥታ ኃይሎች በእስራኤል ቁጥጥር ሥር ባለው ዌስት ባንክ በተወሰነ ደረጃ ይንቀሳቀሳል።

በጀኒን ባለፈው ወር እንቅስቃሴ ማድረግ ጀምረው ነበር። በጀኒን ካምፕ ውስጥ ያለውን ታጣቂ ኃይል ዒላማ አድርገውም ነበር።

በካምፑ ውስጥ ያለው ኃይል ለፍልስጤም አስተዳደር መሰናክል እንደሚሆን ያምናሉ።

ጀኒን ባታሊዮን አንድ መኪና በካምፑ ውስጥ አቃጥሏል ተብሏል። ሌሎችም “ሕገ ወጥ ድርጊቶች” በመፈጸም ተከሷል።

የፍልስጤም አስተዳደር ብርጋድየር ጀነራል አንዋር ራጃብ “ከፍተኛ ቁጥር ያለው መሣሪያ እና ፈንጂ በቁጥጥር ሥር አውለናል” ብለዋል።

“ዓለማችን ካምፑን ከፈንጂዎች ነጻ ማድረግ ነው። በተለያዩ መንገዶች ላይ ተቀብሯል። እነዚህ ሕገ ወጦች ቀይ መስመር አልፈው ቀውስ ፈጥረዋል” ሲሉም አክለዋል።

ኢራንን እነዚህን ኃይሎች በማስታጠቅና በመደገፍም ከሰዋል።

ጀኒን ባታሊዮን ከኢራን ጋር ትስስር አለው የሚለውን ክስ ያስተባብላል።

በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ቃል አቀባዩ ኑር አል-ቢተር “የፍልስጤም አስተዳደር ገጽታችንን ለማጠልሸት እየሞከረ ነው” ሲል ጽፏል።

ታጣቂዎቹ መሣሪያቸውን እንደማያስረክቡም ገልጿል።

“ነገሮች ለምን እንደዚህ ሆኑ? ስል የፍልስጤም አስተዳደርና ፕሬዝዳንት ሞሐመድ አባስን መጠየቅ እፈልጋለሁ ” ብሏል።

ይህን የተናገረው ሮኬት ፈንድቶበታል በተባው ቦታ ላይ የተገኘ ቁርጥራጭ መሣሪያን ይዞ ነው።

ፕሬዝዳንት አባስ በፍልስጤማውያን ዘንድ ያላቸው ተቀባይነት ቀንሷል። የትጥቅ ትግልን አምርረው የሚቃወሙም አሉ።

እስራኤል ይህ ቡድን አሸባሪ ነው ብላ ፈርጃለች።

የሕዝቡን ቁጣ ተከትሎ የፍልስጤም አመራሮች ታጣቂዎች ላይ ካምፕ ውስጥ እርምጃ መውሰድ ጀምረዋል።

እርምጃው ያልተጠበቀ ሲሆን በኃይል የተሞላና ረዥም ጊዜ የወሰደም ነው።

እስራኤል እነዚህ ኃይሎች አሸባሪዎች ናቸው ትላለች። የጀኒን ነዋሪዎች ግን እነሱን ለመከላከል እንደቆመ ቡድን ነው የሚወስዷቸው።

ኡም አል-ሞታሲም “እነዚህ ሕገ ወጦች የሚሏቸው የእስራኤል ኃይል ካምፓችን ላይ ጥቃት ሲያደርስ የሚከላከሉልን ናቸው” ይላሉ።

በካምፑ በደረሰው ጥቃት የ14 ዓመት ታዳጊን ጨምሮ 14 ሰዎች ተገድለዋል ሲል የፍልስጤም የጤና ሚኒስቴር ገልጿል።

የጀኒን ነዋሪዎች የእስራኤል ኃይልን የሚፈሩትን ያህል የፍልስጤም ኃይልንም እንደሚፈሩ ይናገራሉ።

የሻታ ሞት ደግሞ ፍርሃታቸውን ቀስቅሶታል።

ሻታ ከመገደሏ በፊት የፍልስጤም የፀጥታ ኃይሎችና የእስራኤል ኃይል በጀኒን ካምፕ ያደረሱትን ጉዳት በተመለከተ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ብዙ መረጃ እያጋራች ነበር።

ወንድሟን ጨምሮ በውጊያ የሞቱ ወንዶችን ምሥልም አጋርታለች።

ጋዜጠኞች

ሻታ መገደሏን ሐማስ አውግዟል። የተገደለው ወንድሟ የሐማስ ወታደራዊ ክንፍ አል-ቃሲም ብርጌድ አባል እንደነበር ተገልጿል።

“በጭካኔ ነው የተገደለችው። የጀኒን ካምፕን ዒላማ ያደረገውን ጨቋኝ ፖሊሲ ለመከላከል በሚል እዛ ያለ ኃይል አለ” ብለዋል።

የፍልስጤም ብሔራዊ ንቅናቄ የፖለቲካ ፓርቲ መሪ ሙስጠፋ ባርጎቲ በጀኒን ካምፕ ያለው ውጊያ በዋነኛው የፍልስጤማውያን ኃይል ፋታሕ ውስጥ ያለው ክፍፍል ውጤት ነው ይላሉ።

የፍልስጤም ኃይል እና ሐማስ የወጣው ከዚህ ቡድን ነው። ጋዛን ከ2007 ጀምሮ የመራው ይህ ቡድን ነው።

“እስራኤል ሁላችንም ላይ እየተኮሰችብን በዚያ ላይ ፍልስጤማውያን በፍልስጤማውያን ላይ መተኮስ የለባቸውም” ይላል።

በካምፑ ውስጥ ያለው የእለት ከእለት ሕይወት የከፋ ሆኗል።

“እዚህ ያለው ሕይወት ፈታኝ ነው። በነጻነት መንቀሳቀስ አንችልም። ዳቦ ቤቶችና ሱቆች ተዘግተዋል። የምሠራበት ሬስቶራንት አንድ ቀን ተከፍቶ 10 ቀን ይዘጋል። ቢከፈትም ማንም አይመጣም” ይላል አንድ የአካባቢው ነዋሪ።

አባስ

“ለልጆቻችን ወተት እንፈልጋለን። ተኩሱ ስለቀጠለ ሰዎች በራቸውን መክፈት እንኳን አይችሉም” ሲልም ያክላል።

የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት (ኦቻ) በፍልስጤም ኃይሎች ተፈጸመ ያለው የሰብአዊ መብት ጥሰት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ጠይቋል።

የፍልስጤም አስተዳደር ብርጋድየር ጀነራል አንዋር ራጃብ “የጀኒን ካምፕን የተቆጣጠሩት ሕገ ወጦች ታስረዋል። ለፍርድም ይቀርባሉ” ብለዋል።

ነዋሪው እንደሚለው ግን ንጹኃን ሰዎች ናቸው በመሀል እየተጎዱ ያሉት።

“የጋራ ቅጣት ነው የተፈጸመባቸው” ይላሉ ነዋሪዎች።

“ሕገ ወጦችን ለመቅጣት በሚል ሕዝቡ መቀጣት የለበትም። ከቤታችን ስንወጣ ፀልየን ነው። ወደ ቤት ልንመለስ አንችልም ብለን እናስባለን። በጣም ስለሚበርደን በራችንን ገንጥለን እሳት እንሞቃለን” ሲል አንድ የአካባቢው ነዋሪ ይናገራል።

ቢቢሲ ነዋሪዎቹን ባነጋገረበት ወቅት ተኩስ በቅርብ ርቀት ይሰማ ነበር።

በጀኒን ካምፕ የተገደሉ ሰዎች

አንደኛዋ ነዋሪ ሳዳፍ “መንገዱ በቆሻሻ የተሞላ ነው። ይሄን ሁሉ ተኩስ እየሰማን እንዴት እንተኛለን። በተራ በተራ መተኛት ጀምረናል። ቤታችን ውስጥ ይገባሉ ብለን እንፈራለን” ትላለች።

የጸጥታ ኃይሎች ሆነ ብለው የኤሌክትሪክ ግሪድ በመምታት መብራት ያጠፋሉ።

የፍልስጤም የጸጥታ ኃይሎች ለዚህ ተጠያቂ የሚያደርጉት “ሕገ ወጦች” የሚሏቸውን ቡድኖች ነው።

የፍልስጤም አስተዳደር ብርጋድየር ጀነራል አንዋር ራጃብ በኦፕሬሽናቸው እንደሚቀጥሉ ይገልጻሉ።

“ታጣቂዎቹ ሕዝቡን ተጠቅመው ኦፕሬሽኑን ማስቆም ነው የሚፈልጉት” ይላሉ።

በጀኒን ካምፕ የፍልስጤም ኃይል ቁጥጥር እንዲኖረው ይፈልጋል።

ታጣቂዎች በካምፑ ከሌሉ እስራኤል ጥቃት ለመሰንዘር ምክንያት አይኖራትም ብሎ ያስባል።

የፍልስጤም የጤና ሚኒስቴር እንደሚለው እስካሁን 36 ፍልስጤማውያን ተገድለዋል።

የፍልስጤም ኃይሎች በጋዛ አመራራቸውን አጠናክረው መቀጠል እንደሚፈልጉ ተንታኞች ይናገራሉ።

የፍልስጤም አስተዳደር ብርጋድየር ጀነራል አንዋር ራጃብ “ጋዛ የፍልስጤም አካል ስለሆነች ብናስተዳድር ምን ችግር አለው?” ይላሉ።

“ጋዛ እና ዌስት ባንክ የተለያዩ ግዛቶች አይደሉም” ሲሉም ያክላሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ከጋዛ ጦርነት በኋላ እስራኤል አካባቢውን መቆጣጠር ይፈልጋሉ።

“ፍልስጤማውያን እስራኤል ላይ ጥቃት ከሚሰነዝሩ ኃይሎች ጋር ትስስር አይኖራቸውም” ይላሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

የእስራኤል ደጋፊዋ አሜሪካ ጋዛ በእስራኤል አመራሮች ሥር እንዲሆን ነው የምትፈልገው።

የጀኒን ካምፕ ነዋሪዎች እየደረሰባቸው ባለው ጥቃት መማረራቸውን ይናገራሉ።

የሻታ አል-ሳባግህ እናት “የፍልስጤም ኃይሎች የእኛን ደኅንነት ማስጠበቅ እንደሚፈልጉ ነው የሚነግሩን። ታዲያ ለምን መተኮስ አያቆሙም? ከፈለጉ ሕገ ወጦችን ማሳደድ ይችላሉ። ልጄ ግን ለምን ሞተች? ልጄን ማን እንደገደላት ሳውቅ ነው ፍትሕ የሚሰፍነው” ትላለች።