
12 ጥር 2025
ወቅቱ ከ15 ዓመታት በፊት ነበር።
ታዋቂው የቶጓው እግር ኳስ ተጫዋች ኢማኑኤል አደባዮር ሞትን ያመለጠባት ቅጽበት።
በአምበልነት እየመራው የነበረው የቶጎ ብሔራዊ ቡድን ወደ ሰሜን አንጎላ እየተጓዙ እያለ ነበር ጥቃት የተፈጸመባቸው።
ከአውሮፓውያኑ 2010 የአፍሪካ ዋንጫ ጥቂት ቀናት በፊት።
ሁለት ሰዎች በተገደሉበት ኢማኑኤል እና ሌሎች ተጫዋቾች በነበሩበት አውቶብስ ላይ ጥይት እንደ ዝናብ ሲዘንብ አደባዮር አንድ የመጨረሻ ምኞት ነበረችው።
አደባዮር ቀጣዩ እኔ ልሆን እችላለሁ በሚል ስጋት በወቅቱ ነፍሰጡር የነበረችው ባለቤቱን ለማናገር የመጨረሻ የመሰለውን ስልክ ደወለ።
ለባለቤቱም “ስሚኝ የሚወለደው ህጻን ወንድ ከሆነ ጁኒየር ኢማኑኤል በይው። ሴት ከሆነች ፕሪንሰሰስ ኢማኑኤላ በያት” አላት።
ግራ የተጋባችው ባለቤቱ “ለምን? ምንድነው? ለምንድነው ይህንን የምትለኝ?” ስትል ጠየቀችው።
“የጥይት እሩምታው ሲቀጥል ስልኩን ዝም ብዬ የሆነ ቦታ ወረወርኩት” ይላል።
ከአስራ አምስት ዓመታት በፊት የተፈጸመው ይህ ጥቃት ሕይወቱን የቀየረ ክስተት ነበር።
“ከዚያችን ዕለት ጀምሮ ውስጤ የሆነ ነገር ተቀየረ” ሲል የ40 ዓመቱ አደባዮር ለቢቢሲ አፍሪካ ተናግሯል።
“ለራሴም መንገር ጀመርኩ። እያንዳንዷን ሰዓት፣ ደቂቃ እና ቅጽበት የመጨረሻህ እንደሆነች በማሰብ መደሰት አለብህ። የመጨረሻህ የምትሆነውን ቅጽበት አታውቃትም” ይላል።
“ካቢንዳ (ጥቃቱ የተፈጸመበት ስፍራ) በሕይወቴ ላይ ትልቅ ለውጥ አምጥቷል።”
ለፍጻሜው ጨዋታ በኮንጎ ብራዛቪል ዝግጅታቸውን ከጨረሱ በኋላ የቶጎ ብሄራዊ ቡድን ካቢንዳ ወደተሰኘችው የአንጎላ ግዛት እያመሩ ነበር።
የውድድሩ አዘጋጆች ቡድኑ ወደ አንጎላ መዲና ሉዋንዳ በአውሮፕላን ከተጓዘ በኋላ ከዚያ ወደ ካቢንዳ እንዲበር ተናግረው ነበር። ቡድኑ ግን በመኪና መጓዝን መረጠ። ተጫዋቾቹ በመንገድ ላይ ሊጠብቋቸው የሚችሉ የደኅንነት ሰዎች ቢመደቡላቸውም እነሱ ግን ስጋቱን ከመረዳት ይልቅ በነገሩ ቀለዱ።
ግን ያላሰቡት ጉዳይ ገጠማቸው። ጥቃት አድራሾቹ “አለባበሳቸው በፊልም ላይ ያሉ ይመስል ነበር።”
“ዓይናቸውን እንኳን ማየት አይቻልም። ስለት፣ ቦምቦች፣ ኤኬ47 ጠመንጃዎች፣ ሽጉጦች” ታጥቀው ነበር ይላል።
“በጦርነት ቀጠና ውስጥ መሆናችንን አላወቅንም ነበር” ሲል የነበረውን ግራ መጋባት ያስታውሳል።
ጥቃቱ የተፈጸመው የቀድሞ የአንጎላ ቅዢ ገዢ ፖርቹጋል ካቢንዳ ወደ አንጎላ እንድትቀላቀል የወሰነችውን ውሳኔ ፍጹም የማይቀበሉ መገንጠል በሚፈልጉ ታጣቂዎች ናቸው።
በጫካ ውስጥ እየነዱ ባለበት ወቅት በተፈጸመው በዚህ ጥቃት የአውቶብሱ አሽከርካሪ ቆሰለ።
ጥቃቱ በከፍተኛ ሁኔታ ተፋፍሞ ቢያንስ ለግማሽ ሰዓት ቀጠለ። ግብ ጠባቂው ኮድጆቪ ኦቢላሌ በጥይት አከርካሪው ላይ ተመታ።
ልብሱ ሁሉ በደም ተለወሰ።
“ከዚህ ቀደም አንድም ሰው ሲሞት አይቼ አላውቅም ነበር።”
- ነዳጅ ከመሸጫ ዋጋ በላይ የሚሸጡ ነጋዴዎችን እስከ 500 ሺህ ብር የሚያስቀጣ አዋጅ ጸደቀ9 ጥር 2025
- በሎስ አንጀለስ እየተዛመተ ያለው ሰደድ እሳት ወደ ዝነኛው የሆሊውድ ምልክት እየተቃረበ ነው9 ጥር 2025
- የመሬት መንቀጥቀጦች አስከፊ የሚሆኑባቸው 7 ምክንያቶች9 ጥር 2025

የአውቶብስ መስታወት ቢረጋግፍም በመጨረሻ ተጫዋቾቹን መታደግ ተቻለ። ከዚያም ካቢንዳ ከተማ ዳርቻ ወደሚገኝ ሆስፒታል ተወሰዱ።
ከአደባዮር ጋርም አብሮ የነበረው የግል ረዳቱ እና በቶጎ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን የሚዲያ ኃላፊ የነበረው ስታንሲላስ ኦክሎ ነበር።
“ሆዴን፣ ሆዴን እያለ ከፍተኛ ህመም እየተሰማው እንደሆነ መናገር ጀመረ። ሆዱን ስናየው መርፌ የወጋው ይመስል ትንሽ ቀዳዳ አየን” ሲል የቀድሞው የማንቸስተር ሲቲ ተጫዋች አደባዮር ይናገራል።
“ሆስፒታል ደርሰን በቃሬዛ ተሸክመነው ገባን። ጓደኛዬ ጠንካራ መሆን አለብህ፤ ለመጠንከር እንደምትሞክር ቃል ግባልኝ? አልኩት” ሲል ያስረዳል።
“ዶክተሩ መረመረውና ሁለት ወይም ሦስት ጥይቶች እንደገቡበት ተናገረ። ስታን ይሄንን ሲሰማ ተስፋ ቆረጠ።”
“ተስፋ መቁረጥ የለብህም። መጽናት አለብህ። ቤተሰብህ በቶጎ እየጠበቀህ ነው። ሁላችንም ከአንተ ጋር ነን” አልኩት።
“ከዚያም ጭንቅላቱ እየተንቀሳቀሰ እንዳልሆነ ተረዳሁ።”
“ከዚህ ቀደም ማንም ሰው ፊቴ ላይ ሲሞት አይቼ ስለማላውቅ፤ የሞተ ሰው እንዴት እንደሆነ አልገባኝም” ይላል።
“ለሰዓታትም ያህል ስታን እያልኩ እየጠራሁት ነበር። ምላሽ ሳይሰጠኝ ቀረ። እና ፊት ለፊቴ አንድ ሰው ሲሞት አየሁ” ብሏል።
“አንድ ሰው ለመጨረሻ ጊዜ ዓይኑን ሲዘጋ አየሁ። ለማመን በጣም ከባድ ነው።”
ስታን በዕለቱ ከሞቱት የቡድኑ አባላት አንዱ ነበር። በዚህ ጥቃት ሌላኛው የተገደለው ደግሞ የቡድኑ ረዳት አሠልጣኝ አምሌቴ አባሎ ነው።
ግብ ጠባቂው አቢላሌ በጥቃቱ ከወገቡ በታች ሽባ ሆነ።
የተሳሳተው አውቶብስ
አደባዮር በኮንጎ እና በአንጎላ ድንበር በተፈጠረው መሳሳት ባይሆን በርካቶች ይሞቱ እንደነበር ያምናል።
ቡድኑ ሁለት አውቶብስ ተሰጥቷቸው ነበር። አንደኛው የአየር ማቀዝቀዣ ያለው ሌላኛው ደግሞ የሌለው።
ሻንጣዎቻቸው እና ጓዞቻቸው በሙሉ በስህተት አየር ማቀዝቀዣ ባለው አውቶብስ ውስጥ ተጫነ። ተጫዋቾቹም እንደገና ከማውረድ ይልቅ ጊዜ ለመቆጠብ አየር ማቀዝቀዣ በሌለውወ አውቶብስ ውስጥ ተጭነው ወደ ፍተሻ ኬላው አቀኑ።
ይህም ውሳኔያቸው ሕይወታቸውን ታደገው።
“የመጀመሪያው አውቶብስ የአየር ማቀዝቀዣ (ኤሲ) ስለነበረው መስኮቶች እና መጋረጃዎች ተዘግተው ነበር” ይላል አደባዮር።
“ነገር ግን ያንን ከኋላ እኛ ተሳፍረንበት የነበረው አውቶብስ ሁሉም መስኮቶች ተከፍቶ ነበር። ሞቃት ስለነበር አብዛኛዎቹ ተጫዎቾች ከላይ ራቁታቸውን ነበሩ።”
“እኔ እንደማስበው ጥቃት ፈጻሚዎቹ እኛን ሲያዩን የምንከተላቸው ደጋፊዎች መስለናቸው ነበር። ስለዚህ የመጀመሪያው አውቶብስ ላይ ጥቃት ፈጸሙ።”
“አውቶብሱን አፈነዱት። በእርግጠኝነት ቦምብ ወይም ፈንጅ ነው” ይላል።
ከጥቃቱ በኋላ የቶጎ ባለሥልጣናት ቡድኑን ከአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታዎች ለማስወጣት ብዙ ጊዜ አልፈጀባቸውም።
ከሁለት ሳምንታት በኋላ አደባዮር ወደ ሰሜን እንግሊዝ ተመለሰ።
“ይህንን አጋጣሚ ተጠቅሜ ለማንችስተር ሲቲ ትልቅ ምስጋና አቀርባለሁ። ምክንያቱም ከጥቃቱ በኋላ ስመለስ በየቀኑ ቤቴ የሚመጣ የሥነ ልቦና ባለሙያ መደቡልኝ። እና የደረሰብኝን እንዴት መቋቋም እንዳለብኝ ረድቶኛል” ይላል።
“ስለ ሌሎች ጉዳዮች፣ ስለ ወደፊቱ፣ ስለ ተፈጥሮ እንዲሁም ስለ ሕይወት ጨምሮ የደረሰብኝን መርሳት እንድችል ሁልጊዜ ያወራልኛል። በእውነቱ ሌላ ሰው እንድሆን ረድቶኛል።”
ምንም እንኳን የሥነ ልቦና እርዳታ ቢያገኝም ጥቃቱ ያደረሰበት ጠባሳ ከህሊናው ሙሉ በሙሉ ሊጠፋ አልቻለም።
“አንድ ሰው የሆነ ነገር ሲጥል ወይም ከተኩስ ድምጽ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ነገር ስሰማ ጥቃቱ ይታወሰኛል” የሚለው አደባዮር ተኩስ ያለባቸው በድርጊት የተሞሉ ፊልሞችን ማየት እንደሚቸግረው ያስረዳል።
“ከዚህ ጋር መኖር አለብህ። ምንም እንኳን ያለፍኩበት ፈታኝ ሁኔታ ቢሆንም ዛሬ ግን የሕይወቴ አካል ነው” ይላል።
ጥቃቱ በተፈጸመበት ወቅት ነፍሰ ጡር የነበረችው ባለቤቱ ከጥቂት ወራት በኋላ ሴት ልጅ ተገላገለች። ከአደባዮር ጋር ሆነው ኬንድራ ብለው ጠሯት።