
12 ጥር 2025
ሁለት የቆሰሉ የሰሜን ኮሪያ ወታደሮችን በሩሲያ ኩርስክ ግዛት መያዟን ዩክሬን አስታወቀች።
የጦር ምርኮኞቹ መያዛቸውን ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ ገልጸዋል።
ኪየቭ ውስጥ “አስፈላጊው ሕክምና” እየተደረገላቸው መሆኑንም ተናግረዋል።
የዩክሬን ወታደሮች ሰሜን ኮሪያውያኑን በመያዛቸው አመስግነዋል።
“ቀላል ሥራ አልነበረም” ሲሉም ወታደሮቹን አሞግሰዋል።
ሩሲያ እና ሰሜን ኮሪያ መረጃ ለመደበቅ በሚል የቆሰሉ የሰሜን ኮሪያ ወታደሮችን በስውር እንደሚገድሏቸውና ሁለቱን ወታደሮች መያዝ ቀላል እንዳልነበረ ገልጸዋል።
የዩክሬን ደኅንነት ክፍል እንዳለው ወታደሮቹ የተያዙት ከሦስት ቀናት በፊት ነው።
ወታደሮቹ በጄኔቫ ስምምነት መሠረት ሕክምና እንደተደረገላቸውና በተገቢው ሁኔታ እንደተያዙ የደኅንነት ክፍሉ ገልጿል።
የጦር ምርኮኞቹ ዩክሬንኛ፣ እንግሊዘኛ ወይም ሩሲያኛ ስለማይችሉ ከደቡብ ኮሪያ የደኅንነት ተቋም ጋር በመተባበር በኮርያኛ አስተርጓሚ በኩል እየተነጋገሩ መሆኑንም አክለዋል።
ጋዜጠኞች ወታደሮቹን እንዲያነጋግሯቸው እንደሚፈቀድ ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።
“ዓለም እውነታውን ማየት አለበት” ብለዋል።
- “መተኮስ አቁሙ! ልጄ ሞታለች!” – የዌስት ባንክ እናቶች ሰቆቃ12 ጥር 2025
- የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ ይፋዊ ጉብኝት በአዲስ አበባ12 ጥር 2025
- “ከጥቃቱ በፊት የሞተ ሰው አይቼ አላውቅም ነበር” ኢማኑኤል አደባዮር ስለ ቶጎው የአውቶብስ ጥቃት12 ጥር 2025
ዘለንስኪ በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሯቸው ምሥሎች በጦር ምርኮኛነት የተያዙት ወታደሮች ቆስለው ያሳያል።
የተወለዱት ሞንጎሊያ አቅራቢያ በሚገኘው ቱቫ ሪፐብሊክ እንደሆነ ተገልጿል።
አንደኛው ወታደር ሲያዝ የሩሲያ ወታደራዊ መታወቂያ ይዞ ነበር። የተሰጠው ስምም የተለየ ነበር።
በምርመራ ሲጠየቁ የሩሲያ ወታደሮች ካርድ የተሰጠው ሩሲያ መሆኑን ተናግሯል።
ሁለተኛው ወታደር ምንም ሰነድ አልያዘም።
የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች የሳምንት ሥልጠና ብቻ እንደወሰዱ ተናግረዋል።
የዩክሬን ደኅንነት ተቋም “የጦር ምርኮው እንዳለው ከዩክሬን ጋር ለመዋጋት ሳይሆን ለወታደራዊ ሥልጠና ነው የመጡት” ብሏል።
እአአ በ2005 የተወለደው አንደኛው ወታደር ከ2021 ጀምሮ በሰሜን ኮሪያ ጦር ውስጥ ቆይቷል።
ሁለተኛው ወታደር አገጩ ስለተጎዳ በጽሑፍ በሰጠው መልስ መሠረት የተወለደው እአአ በ1999 ሲሆን ከ2016 ጀምሮ በሰሜን ኮሪያ ጦር ውስጥ ዒላማ ተኳሽ ሆኖ ቆይቷል።

ሩሲያ ወታደሮቹ የመጡት ከቱቫ ወይም ከሌሎች የሩሲያ ግዛቶች እንደሆነ በማስመሰል ከሰሜን ኮሪያ መሄዳቸውን ለመደበቅ ትሞክራለች ሲሉ ዘለንስኪ ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ሩሲያ የሰሜን ኮሪያን ወታደሮች ስለማሰማራቷ ተጠይቀው አላስተባበሉም።
የሩሲያ “ሉዓላዊ ውሳኔ ነው” ሲሉ መልሰዋል።
የደቡብ ኮሪያ የደኅንነት ተቋም የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች በዩክሬን መሰማራታቸውን የሚጠቁም መረጃ አውጥቷል።
ዋይት ሀውስ ባወጣው መግለጫ የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች እየተገደሉ መሆኑን አስታውቋል።
የዩክሬን ደኅንነት ተቋም የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች በዩክሬን ጦርነት ውስጥ ያላቸውን ተሳትፎ ምርመራ ያደርጋል።