ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሶማሊያው ፕሬዝደንት ሐሰን ሼክ ማሕሙድ

11 ጥር 2025

ተሻሽሏል 12 ጥር 2025

በአዲስ አበባ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ያደረጉት የሶማሊያው ፕሬዝደንት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር ተገናኝተው ባደረጉት ውይይት በሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመሥራት ተስማምተዋል።

የሶማሊያው ፕሬዝደንት ቅዳሜ ጥር 3/2017 ዓ.ም. ከሰዓት አዲስ አበባ በሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በስፍራው ተገኝተው አቀባበል አድርገውላቸዋል።

ፕሬዝደንት ሐሰን ወደ አዲስ አበባ ያቀኑት “በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ግብዣ” መሆኑን የሶማሊያ መንግሥት አስታውቋል።

መሪዎቹ የሁለትዮሽ ውይይት ካደረጉ በኋላ በተለያዩ ዘርፎች በጋራ ለመሥራተ መስማማታቸውን የሁለቱ ሀገራት ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሮች ያወጡት መግለጫ ያትታል።

ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ነጻ አገርነቷን ካወጀችው ሶማሊላንድ ጋር የመግባቢያ ሰነድ መፈረሟን ተከትሎ ከአንድ ዓመት በላይ በሁለቱ አገራት ብሎም በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ከፍተኛ ውጥረት ተፈጥሮ ቆይቷል።

መሪዎች ባለፈው አንድ ዓመት ተቀዛቅዞ የነበረውን “ግንኙነታቸውን ለማደስ በሁለቱ ሀገራ መዲናዎች በሚገኙ ዲፕሎማሲያዊ ተወካዮች በኩል ለማጠናከር እንደተስማሙ” የጋራ መግለጫው ያለመክታል።

ሁለቱ ሀገራት የሚያደርጉት “የጋራ መተማመን እና መከባበር ላይ የተመሠረተ” መተባበር ለቀጣናው መረጋጋት ወሳኝ እንደሆነም በመግለጫው ተገልጿል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ፕሬዝደንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የፀጥታ ግንኙነትም ለማጠናከር ተስማምተዋል።

ነገር ግን ኢትዮጵያ ‘አውሶም’ በተሰኘው አዲሱ የሶማሊያ ሰላም ማስከበር ሚሽን ውስጥ ትከታተለች ወይ የሚለው ጉዳይ በመግለጫው አልተካተተም።

የሶማሊያው ፕሬዝደንት ሐሰን ሼክ ማሕሙድ በኢትዮጵያ የነበራቸውን ጉብኝት አጠናቀው እሑድ ከሰዓት መመለሳቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በኤክስ ገፃቸው አስታውቀዋል።

ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ እና ጠቅላይ ሚኒስት ዐቢይ አሕመድ በአዲስ አበባ
የምስሉ መግለጫ,ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ አዲስ አበባ ሲገቡ ጠቅላይ ሚኒስት ዐቢይ አሕመድ ተቀብለዋቸዋል

መሪዎቹ በፀጥታ በኩል ያላቸውን ግንኙነት ለማጠናከር የመከሩት “በቀጣናው የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች” የሚሰነዝሩትን ጥቃት ለመመከት መሆኑ ተገልጿል።

የጋራ መግለጫው ሁለቱ መሪዎች ለአንካራ ስምምነት ያላቸውን ቁርጠኝነት ገልፀዋል በማለት በስምምነቱ ላይ የተጠቀሱት ቴክኒካዊ ድርድሮች ለማካሄድ መስማማታቸውን አስታውቋል።

ኢትዮጵያ፤ ሶማሊያ የሉዓላዊ ግዛቴ አካል ናት ከምትላት ሶማሊላንድ ጋር ባለፈው ዓመት ታኅሣሥ ወር መጨረሻ ላይ የባሕር በር አጠቃቀም እና ዕውቅና መስጠትን በተለመከተ የመግባቢያ ስምምነት ከተፈራረመች በኋላ ከሶማሊያ ጋር ከባድ ውዝግብ ውስጥ መግባቷ ይታወሳል።

ሶማሊያ ስምምነቱ ሉዓላዊነቷን የሚጥስ መሆኑን በመግለጽ ለአፍሪካ ኅብረት እና ለተባበሩት መንግሥታት አቤቱታ አቅርባ፣ የኢትዮጵያን አምሳደር ከሞቃዲሾ በማስወጣት የራሷን አምባሳደር ከአዲስ አበባ መጥራቷ አይዘነጋም።

በተጨማሪም ከ15 ዓመት በላይ በሶማሊያ ሰላም ሲያስከብር የነበረው የኢትዮጵያ ሠራዊት ከግዛቷ እንዲወጣ ጠይቃ ነበር።

በተጨማሪም ሶማሊያ ኢትዮጵያ ላይ የተለያዩ ክሶች በተደጋጋሚ መሰንዘሯ አለመግባባቱ በአፍሪካ ቀንድ ሌላ ግጭት ሊያስከትል ይችላል የሚል ስጋትን ፈጥሮ ቆይቷል።

ሶማሊያ ከኤርትራ እና ከግብፅ ጋር የሶስትዮሽ ግንኙነት መመስረቷ በቀጣናውን ያለውን ውጥረት ያባብሰዋል ቢባልም የኤርትራው ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ ከወራት በፊት በሀገሪቱ ቴሌቪዥን ጣቢያ በሰጡት ቃለ-ምልልስ የሶስቱ ሀገራት ግንኙነት “ከኢትዮጵያ ጋር ግንኙነት የለውም” ብለው ነበር።

የሁለቱም አገራት ወዳጅ በሆነችው በቱርክ በኩል ሲደረግ የነበረው ተከታታይ ጥረት ውጤት አፍርቶ በፕሬዝዳንት ረሲፕ ታይብ ኤርዶዋን አማካኝነት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እና ፕሬዝዳንት ሐሰን ባለፈው ታኅሣሥ መጀመሪያ ላይ ውጥረቱን የሚያረግብ እና ግንኙነታቸውን የሚያድስ ስምምነት ላይ ደርሰዋል።

ፕሬዝዳንት ኤርዶዋን “ታሪካዊ” በማለት የጠሩት ስምምነት በሁለቱ አገራት መካከል “ሰላም እና ትብብር ለማምጣት የመጀመሪያ እርምጃ” እንደሚሆን በመጥቀስ፣ መሪዎቹ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለማሥራት መስማማታቸውን የሚገልጽ ሰነድ ይፋ ተደርጎ ግንኙነታቸው ለመቀጠል ተስማምተዋል።