
ማኅበራዊ ልሂቅ የምጣኔ ሀብት ባለሙያና ፖለቲከኛ በፍቃዱ ደግፌ (ዶ/ር) ሲታወሱ
ቀን: January 12, 2025
የምጣኔ ሀብት (ኢኮኖሚክስ) ዕውቀትን እስከ ሦስተኛ ዲግሪ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል በከፍተኛ ደረጃ ያስተማሩ፣ ያማከሩ ነበሩ፡፡ ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የነበራቸው የአገልግሎት ቁርጠኝነት ከግማሽ ምዕት ዓመት በላይ የተሻገረ መሆኑም የተመሰከረላቸው በፍቃዱ ደግፌ (ዶ/ር) ናቸው።

በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የኢኮኖሚ አማካሪና ተመራማሪ ሆነውም ለዓመታት ሠርተዋል።
በኢትዮጵያም ሆነ በውጭ በኢኮኖሚክስ ዘርፍ ያበረከቱት ወደር የማይገኝለት በርካታ ጥናቶችን በግልና በጋራ በመሥራት ያበረከቱት አስተዋፅኦ ከፍ ያለ እንደሆነ በገጸ ታሪካቸው ተቀምጧል፡፡
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ ማኅበር መሥራች አባል፣ በመቀጠልም ከ2000 እስከ 2004 አራተኛው ፕሬዚዳንት በመሆን ያገለገሉት በፍቃዱ ደግፌ (ዶ/ር) ማኅበሩ አሁን ካለበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ በማድረግ ረገድ ተጠቃሽ ናቸው።
በተመራማሪነት፣ በአስተማሪነትና በፖሊሲ አማካሪነት ያከናወኗቸው ተግባራትም ተተኪ ኢኮኖሚስቶች የላቀ ደረጃ ላይ እንዲደርሱና ለአገሪቱ ዕድገት ትርጉም ያለው አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ያደረገ መሆኑም ተጠቅሷል።
‹‹የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ›› (ኢሕዲሪ) መንግሥትን ያስወገደው ኢሕአዴግ መንበሩን እንደጨበጠ፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከተባረሩ 42 ምሁራን አንዱ የነበሩት በፍቃዱ (ዶ/ር)፣ በፖለቲካው ጎራ በምርጫ 1997 ከቅንጅት ጋር የተቀላቀለውንና ቀስተ ደመና የተባለውን የፖለቲካ ድርጅት ከመሠረቱት መካከልም አንዱ ነበሩ።
በወቅቱ በአዲስ አበባ ወረዳ 24 ‹‹ቅንጅት››ን በመወከል ለፓርላማ ተወዳድረው ያሸነፉ ቢሆንም፣ ምርጫውን ተከትሎ በተፈጠረው ነገር ለ21 ወራት በወኅኒ ቤት ከታሰሩት አመራሮች አንዱ ነበሩ፡፡
በምርጫ 2013 በአዲስ አበባ ወረዳ 24 መሥራች አባል የነበሩበት ኢዜማን በመወከል መወዳደራቸው ይታወሳል።
መንግሥታዊ ለውጡን ተከትሎ ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተመለሱት በፍቃዱ (ዶ/ር) በኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል በመምህርነትና በሦስተኛ ዲግሪ ተማሪዎች አማካሪነት አገልግለዋል፡፡
ልሂቅ የምጣኔ ሀብት ባለሙያው በፍቃዱ ደግፌ (ዶ/ር) ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ባደረባቸው ሕመም ምክንያት በሕክምና ሲረዱ ቆይተው ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ጥር 1 ቀን 2017 ዓ.ም. ነው፡፡ ሥርዓተ ቀብራቸውም በማግሥቱ በቀራኒዮ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ተፈጽሟል።
ከ11 ዓመታት በፊት በወርኃ ነሐሴ ‹‹ሰማያዊ›› ፓርቲ አዘጋጅቶት በነበረው የውይይት መድረክ ላይ ስለ ትውልድ ሐረጋቸው ከሃይማኖት ጋር አስተሳስረው መግለጻቸውን በዘ-ሐበሻ እንዲህ ተዘግቦ ነበር፡-
‹‹የእኔ ቅድመ አያት ሙስሊም ናቸው። እናቴ ጌጤ ትባላለች። አያቴ ደግሞ ብሩ ይባላሉ። ቅድመ አያቴ መንሱር የሚባሉ ሲሆን፣ የመንሱር አባት ደግሞ በፍቃዱ ይባላሉ። እኔ በቅድመ አያቴ ስም ነው የምጠራው። ስሜን ያወጡልኝ አያቴ ናቸው። ቀኝ አዝማች ብሩ ይባላሉ። በፍቃዱ ሙስሊም ነው ያገቡት፤ ሰባት ልጆች ወልደው ነበር። ሦስቱ ሙስሊም ሲሆኑ አራቱ ክርስቲያን ሆነዋል። ከነዚህ ውስጥ ሴቷ ሙስሊም አግብታ አብራ ኖራለች። አብረን ነው የምንበላው አብረን ነው የምንኖረው፤›› በማለት ለሃይማኖቶች መቀራረብ ከዚህ የተሻለ ማነፃፀሪያ የለም ማለታቸው ተጠቅሷል።