ሔለን ተስፋዬ

January 12, 2025

በጫካ ፕሮጀክት ያስገነባውን የሽያጭ ቢሮ ምርቃት

የጫካ ፕሮጀክት አንድ አካል እንደሆነ የተነገረለት የመኖሪያ መንደር በ21 ቢሊዮን ብር መነሻ ካፒታል ሊገነባ መሆኑን ኦቪድ ሪል ስቴት አስታወቀ፡፡

ኦቪድ ሪል ስቴት ይህንን ያስታወቀው ጥር 1 ቀን 2017 ዓ.ም. በጫካ ፕሮጀክት ያስገነባውን የሽያጭ ቢሮ ምርቃትና የመንደሩን ግንባታ በኮንክሪት ሙሌት ሲያስጀምር ነው፡፡

የሪል ስቴቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሙሉቀን ምትኩ (ኢንጂነር) አጠቃላይ ፕሮጀክቱ የውስጥ ለውስጥ መንገድና አፓርታማ ግንባታዎችን ጨምሮ 21 ቢሊዮን ብር ድረስ ሊወስድ እንደሚችል ገልጸው፣ ነገር ግን ይህ ተመን በየጊዜው ባለው የገበያ ሁኔታ ሊቀያየር እንደሚችል ተናግረዋል፡፡   

በዚህ ፕሮጀክት ባለ18 ወለል ከስምንት እስከ አሥር ሕንፃዎች፣ ባለአንድ ወለል 12 ሕንፃዎች፣ እንዲሁም ባለ16 ወለል ተጨማሪ ሕንፃዎች፣ በአጠቃላይ 26 ሕንፃዎችን ለመገንባት መሠረት ማውጣቱን የገለጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ለሕንፃዎቹ ግንባታ የሚሆን 9.46 ሔክታር መሬት መዘጋጀቱን አስረድተዋል፡፡  

የመኖሪያ መንደሩ ከተለያዩ ክፍላተ ከተሞች ጋር የሚገናኙ የተለያዩ የመንገድ መሠረተ ልማቶች እንደሚዘረጋ፣ ከየካ ተራራ እስከ መሀል ከተማዋ የሚያገናኝና ከእንጦጦ እስከ የካ አባዶ የሚደርስ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

ይህ ፕሮጀክት በሁለት ዙሮች የሚነባ መሆኑንና የመጀመሪያውን በሁለት ዓመታት፣ ሁለተኛውን በአምስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ እንደታቀደ ነው ዋና ሥራ አስፈጻሚው የተናገሩት፡፡

የኦቪድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዮናስ ታደሰ በበኩላቸው የመንደር ግንባታው የሚከናወነው 70/30 በሚባለው በመንግሥትና በግል አጋርነት እንደሆነ፣ መንግሥት መሬት ስለሚያቀርብ በምትኩ ከፕሮጀክቱ 30 በመቶ እንደሚያገኝ ተናግረዋል፡፡

የጫካ ፕሮጀክት በዋናነት የቅንጦት አፓርትመንቶችን እንደሚገነቡበት፣ በውስጡም የገበያ ማዕከል፣ የሕፃናት ማቆያና ሌሎች መገልገያዎችን ያካተተ እንደሆነ አቶ ዮናስ አስረድተዋል፡፡

ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ ሌላ ኃላፊ እንደተናገሩት፣ የጫካ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ከባለአንድ እስከ ባለሦስት መኝታ አፓርትመንቶችን የያዘ ነው፡፡ ባለአንድ መኝታው በዝቅተኛ ዋጋ ስምንት ሚሊዮን ብርና ከዚያ በላይ የሚያወጣ ሲሆን፣ ባለሦስት መኝታው ደግሞ 22 ሚሊዮን ብር እንደሚደርስ ጠቁመዋል፡፡

ፕሮጀክቱ ትምህርት ቤቶች፣ የመዋኛ ገንዳዎች፣ የሕፃናት መጫወቻዎች፣ የንግድ ማዕከላት፣ ሆስፒታሎች፣ የመኪና ማቆሚያዎችና የስፖርት ማዘውተሪያዎችን በውስጡ የያዘ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በተጀመረው የጫካ ፕሮጀክት የመኖሪያ መንደር ግንባታ አንዱ መሆኑን የገለጹት ሙሉቀን (ኢንጂነር)፣ በአካባቢው በፍጥነት ወደ ልማት ከገቡ ፕሮጀክቱ የመጀመሪያው ነው ብለዋል፡፡   

ከ60 እስከ 100 ካሬ ሜትር ባለአንድ መኝታ ቤቶች አፓርትመንቶች እንደሚገነቡ ገልጸው፣ በተለያዩ አማራጮችና ዲዛይኖች የቀረቡ ቤቶችን ለደንበኞች ለማቅረብ ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል፡፡

ሕንፃዎቹ 2,132 አባወራዎችን እንደሚያስተናግዱ፣ በአጠቃላይ ከ8,000 እስከ 9,000 የሚሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎችን የሚይዝ መንደር መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከ80 በመቶ በላይ ግንባታቸው ያልተጠናቀቁ የሪል ስቴት ቤቶችን ለሽያጭ ማቅረብ አይቻልም የሚል አዋጅ በቅርቡ ማፅደቁ ይታወሳል።

ያልተጠናቀቁ የሪል ስቴት ቤቶች ለሽያጭ ማቅረብ በአዋጅ ስለተከለከለ፣ ኦቪድ ሪል ስቴት ግንባታውን ሳያጠናቅቅ መሸጡ ከአዋጁ ጋር አይፃረርም ወይ የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ አዋጁ 80 በመቶ ግንባታ ላይ ያልደረሰ መሸጥ እንደማይቻል ነው የሚደነግገው ካሉ በኋላ፣ ‹‹ነገር ግን እኛ ያልነው 80 በመቶ ሲደርስ ያልቃል ብለን ነው ለሽያጭ ያቀረብነው፤›› ብለዋል፡፡ እነዚህ ቤቶች በከፊል ከተጠናቀቁ በኋላ የሚሸጡ በመሆናቸው አዋጁ እንደሚፈቅድ ገልጸዋል፡፡ ‹‹በዚህ መሠረት አዋጁ እኛን የሚነካ አይደለም፤›› ሲሉ ገለጸዋል፡፡

‹‹ረቂቁ ተልኮልን አስተያየት የሰጠንበትና የምናውቀው ነው፣ አዋጁን እናከብራለንም፤›› ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ‹‹ሻጭና ገዥ ከተስማሙ አዋጁ የሚፈጥርብን ሥጋት የለም፤›› ብለዋል።

‹‹ገዥዎቻችን እንዲያምኑን የሚያስችሉ የማኅበራዊ ልማት ሥራዎችን እንሠራለን፤›› ብለው፣ አዋጁ  ከመፅደቁ በፊት በረቂቁ ላይ ያላቸውን  ምልከታ አቅርበው   እንደነበር አስታውሰዋል፡፡