ወጣት የገና ጨዋታ በኤግዚቢሽን

በጋዜጣዉ ሪፓርተር

ቀን: January 12, 2025

በምሥራቅ ደረጄ

በኢትዮጵያ የገና በዓል የተለያዩ መንፈሳዊና ባህላዊ እሴቶችን በጠበቀ መልኩ የሚከበር ነው። ከባህላዊ እሴቶቹ አንዱ የሆነው ደግሞ የገና ጨዋታ ነው።  ጨዋታው በዓሉ ከመድረሱ በፊት በወጣቶች እንዲሁም በአዛውንቶች ይዘወተር የነበረ ቢሆንም፣ ዛሬ ላይ ደብዝዟል፡፡

የገና ጨዋታ በኤግዚቢሽን | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
ወጣት ናትናኤል ጴጥሮስ

ወጣት ናትናኤል ጴጥሮስ የገና ጨዋታን ይበልጥ ለአሁኑ ትውልድ ለማስተዋወቅ እየሠራ እንደሚገኝ ይገልጻል፡፡ በአዲስ አበባ የገና ባዛር ሲዘጋጅ የገና ጨዋታን ይዞ ላለፉት አራት ዓመታትም ቀርቧል፡፡ የግል ሥራ ቢኖረውም፣ ገና በዓል በመጣ ቁጥር የገና ጨዋታ በትውልዱ ዘንድ ጨርሶ እንዳይረሳና እንዲታወስ ለማድረግ በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል መግቢያና መውጫው ሆኖ በሚያገለግለው ሥፍራ በመሆን፣ በሳጥን ጎል በማዘጋጀት ጎብኚዎች ጨዋታውን እንዲጫወቱ ያደርጋል፡፡ ከባህሉ ጋር የተያያዙ የተለያዩ ጽሑፎችን በመለጠፍ ግንዛቤ ያስጨብጣል፡፡ሥራውን በተመለከተ ምሥራቅ ደረጄ አነጋግራዋለች፡፡

ሪፖርተር፡- የገና ጨዋታን በዚህ መልኩ ለማስተዋወቅ ምን አነሳሳህ?

ወጣት ናትናኤል፡- ይሄ ሐሳብ የመጣልኝ ከዛሬ አራት ዓመታት በፊት እዚሁ ኤግዚቢሽንና ባዛር ውስጥ እህቴ ሌላ ሥራ ስትሠራ ላግዛት በመጣሁበት ጊዜ ነበር።  የተጣለ ኩባያ አንስቼ ነበር ለምን ኳስ ኩባያ ውስጥ ማስገባት አላጫውትም ብዬ ያሰብኩት፡፡ እህቴ የምትሠራበት ፊት ለፊት  መሬት ላይ ኩባያዋን አስቀምጨ ኳስ  ማስገባት በሚል የዛኑ ቀን እያስከፈልኩ ማጫወት ጀመርኩ። በጣም ብዙ ሰው ተሰበሰበ፡፡ በሰዓቱ አዘጋጆቹ የሰውን መሰብሰብ አይተው መጡ፡፡ እዚያ ቦታ ላይ እንደማይቻልና ከፈለኩ ውጭ ማጫወት እንደምችል ነገሩኝ።  ውጭ ላይም እጅግ በጣም ብዙ ሰው ነበር ሊጫወት የመጣው፡፡ የዛን ሰዓት  ለምን ይህንን ጨዋታ ባህልን ለማስተዋወቅና እንዳይረሳ ለማድረግ አልጠቀምበትም አልኩ። በዚያች ኩባያ መነሻ ነው ይሄን ሐሳብ የጠነሰስኩት፡፡

ሪፖርተር:-  በመጀመርያ የሰው ተቀባይነት ምን ይመስል ነበር?

ወጣት ናትናኤል:- የሰው ተቀባይነት እጅግ በጣም አዎንታዊና ደስ የሚል ነበር።  በተለይ ከተማ ላይ የገና ጨዋታ ያልተለመደና  አዲስ ስለሆነ፣ አባቶቻችንም ተጫወትን ይሉናል እንጂ ሲጫወቱ ዓይተን ስለማናውቅ ሰው በጣም ደስተኛ ሆኖ ነበር የሚጫወተው፡፡ ሕዝቡም ተሰብስቦ ሚጫወተውን ሰው ማየት ያስደሰተው ነበር፡፡ እስከ ማታ 3 ሰዓትና 4 ሰዓት ድረስ የስልክ ፍላሽ ሁሉ እየተበራ ሰው ይጫወት ነበር። እንዳሁኑ መስቀል አደባባይ በሰፊው ሳይሠራ ማለት ነው። አንድ ጊዜ እንደዚህ ካጫወትኩ በኋላ መስቀል አደባባይ ፈርሶ እንደ አዲስ ተሠራ። ከተሠራም በኋላ ጨዋታው ትውልዱን በማዝናናት ባህሉን አንዳይረሳ ለማድረግ አንደሆነ ሐሳቡን አቅርቤ ‹ጥሩ ነው› በሚል እንድቀጥል አድርገወኛል። እኔም በማጫውትበት ጊዜ ሰው የፎቶ ማስተወሻ እንዲወስድ አደርጋለሁ፡፡ ይህም ባህሉ በሰው አዕምሮ ውስጥ እንዲቀር ያደርገዋል ብዬ አስባለሁ። በአሁኑም እንደዚያ አድርጌያለሁ፡፡ ሰውም በደስታ  ለመሞከር ይመጣል።

ሪፖርተር፡- ሐሳቡ ከመጣልህ ወዲያ ይህንን ጨዋታ ወደ ሕዝቡ ይዘህ ለመምጣት ምን ዓይነት ሒደቶችን አሳለፍክ?

ወጣት ናትናኤል፡- በመጀመርያ  ኩባያ በማስቀመጥ ጎን ለጎን ድንጋይ ደግፌ እሷ ውስጥ ኳስ በአንጨት መቶ በማስገባት ነበር የጀመርኩት፡፡ ኳስ ገባች አልገባች የሚለው  ሁሉንም ያሳስባል። ኳስ ሲገባና ሽልማት ሲሰጥ ሰው በጣም በስሜታዊነት ይጮሃል፣ ይዝናናል። ስለዚህ ይህንን ነገር ትኩረት ሰጥቼ ለመሥራት አሰብኩ፡፡ ምክንያቱም እኔ ባጫወትኩባቸው ጊዜያት ማንም ይህንን ጨዋታ ለማጫወት የሞከረ አልነበረም፡፡ የሰውን ተቀባይነት ለማግኘት በተሻለ መልኩ  ለምን አላዘጋጅም አልኩና አነስ ያለች ሳጥን አዘጋጀሁ፡፡  በሳጥኑ ሥር ቀዳዳ አደረኩና ወደ ጎን ሳይሆን ወደ ፊት መተው እንዲያስገቡና ጨዋታው እንደዚያ እንዲሆን አደረኩ፡፡ ፊቴ ላይ የአባባ ገናን ፂም አደረኩ፣ በርኖሱን ለበስኩ፣ ተነፋነፍ አደረኩ፣ ሙሉ የአባባ ገናን አለባበስ እራሴ ላይ ሠራሁ። ጨዋታውን ሰው እንዲያውቅልኝና እንዲመጣ አሲና በል አሲና ገናዬ እዮሀ አሲና በል እያልኩ እየጨፈርኩ እንቅስቃሴ አደርጋለሁ፡፡ እኔም ደስ እያለኝ በጣም ጥሩ ስሜት እየተሰማኝ ባህሉን በአደባባይ አከብራለሁ። ይሄንን ማድረግ የምጀምረው ከበዓሉ አሥር ቀናት በፊት ጀምሮ ነው፡፡ ወደ ኤግዚቢሽን የሚገባ ሰው ሁሉ ያየኛል፡፡  ሊጫወት የመጣ ሰው ጎሏን ከሳተ 60 ብር ይከፍላል። ያልሳተና በቀዳዳዋ ውስጥ ያሰገባ ደግሞ የተለያዩ ሽልማቶችን ተሸልሞ ከአባባ ገና ጋር ፎቶ ተነስቶ  ይሄዳል።

ሪፖርተር፡- ትውልዱ ባህሉን እንዲያውቅ በምን መልኩ ታስተላልፋለህ?

ወጣት ናትናኤል:- ሳጫውት በደንብ ለማስረዳት እሞክራለው፡፡ ከጨዋታው መነሻ  ጀምሮ በስፋት ገለጻ አድርጌ ሁሉም ሰው እንዲረዳውና እንዲያውቀው የበኩሌን እሞክራለሁ። ከጨዋታውና ከባህሉ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን የወረቀት ጽሑፎች በሳጥኑ ላይ እንዲሁም በመሬት ላይ እለጥፋለሁ። ሩርዋን ወይም ኳሷን ሲመቱ ደግሞ ትክክለኛ የዱላ አያያዝን፣ እንዴት አድርገው መምታት እንዳለባቸውና ባህላችን መሆኑን አስረዳለሁ። ትውልዱ ለጨዋታው እንደቀደመው ዓይነት በሰፊ ሜዳ የመጫወት ዕድሉን ባያገኝም፣ በዚህ መልኩ እንኳን ባህሉን እንዲያውቅ ይረዳዋል። ከኛ ባህል ጋር ለማይገናኙ ተግባራት ልክ እንደ ገና ዛፍ፣ የገና አባት ወይም ሳንታ ለምንላቸው ትኩረት ከመስጠት ይልቅ ታሪካቸውን እንዲያውቁ ያግዛቸዋል፡፡

ሪፖርተር:- ይህንን ጨዋታ ስታጫውት ምን ዓይነት ተግዳሮቶች አጋጥመውህ ነበር?

ወጣት ናትናኤል፡- የመጀመርያዎቹ ሁለት ዓመታት ፈታኝና ከቦታ እስከ መነሳት የደረስኩባቸው ነበሩ፡፡ ‹ይሄማ ባህል አይደለም› እስከመባል ደረስኩበት ወቅትም አለ፡፡ እኔም በጣም ከፍቶኝ ሰው እንዴት ባህሉን ይረሳል በሚል በጣም ተከራክሬ ነው ጨዋታውን የመለስኩት። አሁን ላይ ይህ ችግር የለም፡፡ ጥሩ ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ሆኖም ከአንዳንድ ሰዎች የሚመጣ የነቀፋ አስተያየት አለ፡፡ አንተ ራስህ ተጫወት! ዓይነት ስላቅ ያጋጥማል፡፡ ከጨዋታ በዘለለ የሚተላለፈውን መልእክት አያዩትም፡፡ ‹‹ባህላችንን አንርሳ›› የሚል ጽሑፍ በአማርኛና በእንግሊዝኛ ለጥፌ ነው የምሠራው፡፡  ከዚህ በተጨማሪ ከአዘጋጆች የሚጠየቀው ከፍተኛ ክፍያ ከባድ ነው፡፡ ለኔም ትልቅ ተግዳሮት ነው። አንደኛው ዓመት ላይ 100 ሺሕ ብር ተጠይቄያለሁ። ሌላኛው ዓመት ላይ ደግሞ አዘጋጆች ‹አንተ ይሄንን ካደረክ እኛ ምን እንጠቀማለን› የሚል ጥያቄ ሲያነሱልኝ 18 ሺሕ ብር ወጪ በማድረግ ሰው ፎቶ የሚነሳበት ከእንጨት የተሠራ ግርግም አቅርቤያለሁ። ቁም ነገሩ መልዕክቱን አስተላልፎ መሄድ ስለሆነ፣ ከምጠየቀው ከፍተኛ ክፍያና ከመጥፎ ወይም ቅስም ከሚሰብሩ አስተያየቶች ይልቅ በጎውን እወስዳለሁ። 

ሪፖርተር:-  የማትረሳውና ደስ የሚያሰኝህ ገጠመኝ ምንድን ነው?

ወጣት ናትናኤል፡- ዓምና አጫውቻቸው የነበሩ ሰዋች ድጋሚ ሳገኛቸው፣ ‹እንዴት ነህ? አባባ ገና ባለፈው ዓመት እንደዚህ ተጫውቼ ተሸልሜያለሁ፣ አሁንም አሸንፋለሁ ልሞክር› ሲሉኝ በጣም ደስ ይለኛል። ይህ በተሻለና ሰፋ ባለ መልኩ ለመምጣት  የሚያነሳሳ ነው። ሰው ስለ ባህሉ ራሱ አውቆ ለልጆቹ ካሳወቀ ወደፊት ጥሩ ነገር ይሆናል  ብዬ አስባለሁ፡፡

ሪፖርተር:- ባህል የማስተዋወቅ ሥራውን በምን ያህል ልታሳድገው ታስባለህ?

ወጣት ናትናኤል፡- በሰፊው ባህልን የማስተዋወቅ ሥራ ለመሥራት አስቤያለሁ፡፡ ለዚህ ግን ብዙ አጋሮች ያስፈልጋሉ። የሚመለከታቸው አካላት ይህንን ባህል ማስተዋወቅ አለባቸው ብዬ አስባለሁ፡፡ ጭፈራው፣ ጨዋታው ጥሩ የሆነ ድባብም ይፈጥራል። ባህልና ቱሪዝምም ብዙ አልሰራበትም ብዬ አስባለሁ፡፡ እንደ ስፖርት አድርጎ የማጫወት ነገርም የለም። ውጪዎች ይሄንን ጨዋታ ወደ ገንዘብ ቀይረውታል፡፡ እኛ ጭራሽ እረስተነዋል፡፡ ወደፊት በመስቀል አደባባይም ቢሆን ቦታ ተዘጋጅቶለት ጨዋታው ቢሰፋ ብዬ ለመሥራት አስቤያለሁ፡፡