
15 ጥር 2025
በቅርቡ በሰሜን ቻይና የኤችኤምፒቪ ቫይረስ መስፋፋት ስጋት ፈጥሯል።
Human Metapneumovirus ወይም HMPV የሚባለው ቫይረስ የመጣው ዓለም በኮኖናቫይረስ ከተወረረች ከአምስት ዓመታት በኋላ ነው።
በቻይና ሰባት ሚሊዮን ሰዎች በኮሮናቫይረስ ሞተዋል።
የቻይና ባለሥልጣናት እንዳሉት ዕድሜያቸው ከ14 ዓመት በታች ያሉ እና በኤችኤምፒቪ ቫይረስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው።
ሆኖም ግን ሆስፒታሎች በህሙማን ተጨናንቀዋል የሚለውን አስተባብለዋል።
በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች በሕንድም ተገኝተዋል።
ኤችኤምፒቪ አዲስ ቫይረስ ነው?
የበሽታ መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ተቋም ሲዲሲ እንደሚለው፣ በአሜሪካ ቫይረሱ የተገኘው በአውሮፓውያኑ 2001 ቢሆንም ከዚያ በፊትም ሳይኖር እንደማይቀር ይገመታል።
ምልክቶቹ ከጉንፋን ወይም ብርድ ጋር ይመሳሰላሉ። ሳል፣ የሰውነት ሙቀት መጨመር፣ የአፍንጫ መታፈን፣ ትንፋሽ ማጠርን ያካትታሉ።
ከዚህ ከፍ ያሉ ምልክቶችም ሊታዩ ይችላሉ።
የበሽታ መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ተቋም እንዳለው ቫይረሱ በሁሉም ዕድሜ ክልል እንደ ብሮንካይተስ እና ኒሞኒያ ያሉ የላይኛው እንዲሁም የታችኛው መተንፈሻ አካላት ህመምን ያስከትላል።
በአብዛኛው ቫይረሱ የሚታየው በልጆች፣ በአዛውንቶች እና እቅተኛ በሽታ የመከላከል አቅም ባላቸው ሰዎች ላይ ነው።
ቫይረሱ በሰውነት ውስጥ ገብቶ ምልክት እስከሚያሳይ ድረስ ከሦስት እስከ ስድስት ቀናት ይወስዳል።
የህመሙ ጥንካሬ ያህል የሚያሳየው ምልክትም ይለያያል። ከሌሎች የመተንፈሻ አካላት ህመሞች ጋር ተመሳሳይ ነው።
በቅዝቃዜ ወቅት የበለጠ ቫይረሱ የመስፋፋት ዕድል እንዳለው የበሽታ መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ማዕከል ሲዲሲ ገልጿል።
- ከቢቢሲ አማርኛ ዜና እና ታሪኮች በቀጥታ እንዲላክልዎ የዋትስአፕ ቻናላችን አባል ይሁኑ5 ታህሳስ 2024
- በሎስ አንጀለስ ሰደድ እሳት የተጎዱ ሰዎችን የምትረዳው ትውልደ ኢትዮጵያዊት14 ጥር 2025
- የኢትዮጵያዊቷን ሬስቶራንት በእንግሊዝ አረጋውያን ተወዳጅ ያደረገው ምንድን ነው?14 ጥር 2025
ቫይረሱ እንዴት ይተላለፋል?
ቫይረሱ ካለበት ሰው ወደ ጤናማ ሰው የሚተላለፈው በሳል እና በማስነጠስ አማካይነት ነው።
እንደ መጨበጥ ባሉ በሌሎች የሰውነት ንክኪዎች እንዲሁም ቫይረሱ ያለበትን እቃ ከነኩ በኋላ አፍ፣ አፍንጫ እና ዓይንን በመንካትም ይተላለፋል።
ሰዎች በብዛት ቤት በሚያሳልፉበት ቀዝቃዛ ወቅት ይሰራጫል።
ልጆች እና አዛውንቶች ለምን በቫይረሱ ይያዛሉ?
አንድ ሰው በተደጋጋሚ በቫይረሱ ሊያዝ ይችላል። ለመጀመሪያ ጊዜ በቫይረሱ መያዝ የበለጠ ህመም ያስከትላል ሲሉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ከዚያ በኋላ ሰውነት በሽታ የመከላከል አቅሙን ስለሚያዳብር እምብዛም በቫይረሱ አይጎዳም።
በኤችአይቪ፣ በካንሰር ወይም በሌላ ህመም በሽታ የመከላከል አቅማቸው የደከሙ ሰዎች ግን ቫይረሱ ይጠናባቸዋል።
ከአምስት ዓመት በታች ያሉ እና ከ65 ዓመት በላይ ባሉ ሰዎች ላይ ቫይረሱ የሚጠናበት ምክንያት በሽታ የመከላከል አቅማቸው ጠንካራ ስላልሆነ ነው።
ቫይረሱ ለዓመታት የኖረ ስለሆነ በዓለም ላይ የጋራ በሽታ የመከላከል አቅም መገንባቱን ባለሙያዎች ያምናሉ።

ለምን በቻይና ተከሰተ?
በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ በቻይና ሆስፒታሎች የአፍ እና አፍንጫ ጭምብል ያጠለቁ ሰዎች ምሥሎች እየታዩ ነው።
ሆስፒታሎች በኤችኤምፒቪ ቫይረስ በተያዙ ሰዎች ተጨናንቀዋል የሚለው ወሬ የመጣውም ከዚህ ነው።
የቻይና የበሽታ መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ተቋም ኃላፊ ካን ቢዎ እንዳሉት በአገሪቱ በቀዝቃዛ ወቅቶች በቫይረሱ ሰዎች ይያዛሉ።
እንዲሁም ከ14 ዓመት በታች ያሉ እና በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር መጨመሩን ተናግረዋል።
በአውሮፓውያኑ 2024 በመተንፈሻ አካል ህመም የተያዙ ሰዎች ካለፉት ዓመታት አንጻር ቁጥራቸው መቀነሱን ኃላፊው ተናግረዋል።
ሴንተር ፎር ኢፒደሚክ ሪስፖንስ የተባለው ማዕከል የመሠረቱት ፕሮፌሰር ቱሊዮ ደ ኦሊቬራ እንደሚሉት፣ ኤችኤምፒቪ በቻይና በቅዝቃዜ ወቅት ህመም ከሚያስከትሉ አራት ቫይረሶች አንዱ ነው።
ሳይኒክቲል ቫይረስ፣ ብርድ አና ኢንፍሉዌንዛም በቅዝቃዜ ወቅት ህመም ያስከትላሉ።
በቻይና ያለውን ቅዝቃዜ እና የአራቱን ቫይረሶች ሥርጭት ከግምት በማስገባት የሆስፒታሎች መጨናነቅ የሚጠበቅ ነው ብለዋል ባለሙያው።
ቻይና መነሻው ምን እንደሆነ ያልታወቀ ኒሞኒያን የሚያጠና ቡድን ማቋቋሟን አስታውቃለች።
በመተንፈሻ አካል ህመም የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በዚህ ወቅት እንደሚጨምርም ተገልጿል።
ኮሮናቫይረስ ከአምስት ዓመት በፊት ሲነሳ አሁን ያለው ዝግጁነት አልነበረም።