ፕሬዚዳንት ዮን ሱክ ዮል

15 ጥር 2025, 08:21 EAT

የደቡብ ኮሪያ ባለስልጣናት ወታደራዊ አገዛዝን ካወጁ በኋላ አመጽ አነሳስተዋል የተባሉትን ፕሬዚዳንት ዮን ሱክ ዮልን ከጠባቂዎቻቸው ጋር ለሰዓታት ከቆየ አስገራሚ ፍጥጫ በኋላ በቁጥጥር ስር አዋሉ።

በዚህም በስልጣን ላይ እያሉ በቁጥጥር ስር የዋሉ የመጀመሪያው የደቡብ ኮሪያ ፕሬዝዳንት ለመሆን በቅተዋል።

ዮን ወደ ሙስና ምርመራ ቢሮ መወሰዳቸው ታውቋል።

“ምርመራውን ህገወጥ” ሲሉ የገለጹት ፕሬዝዳንቱ “ያልተፈለገ ደም መፋሰስን ለማስቀረት በሚል” ለምርመራው መስማማታቸውን ገልጸዋል።

የእስር ማዘዣው ተግባራዊ ለማደረግ ባለስልጣናት ለሰዓታት ከዮን ጠባቂዎች እና ደጋፊዎች በተደረገ ፍጥጫ ጫና ቢደረግባቸው መሰላል እና የሽቦ መቁረጫ ተጠቅመው ወደ መኖሪያ ግቢያቸው መግባታቸው ታውቋል።

መርማሪዎች ዮንን በቁጥጥር ስር ለማዋል ለሳምንታት ሙከራ ቢያደርጉም ፕሬዝዳንቱ በመደበቃቸው ሳይሳካላቸው ቀርቷል።

ዮንን ከስልጣን ለማውረድ በቀረበው ሃሳብ ዙሪያ ትላንት እንዲካሄድ በተያዘው መርሐ ግብር ላይ ባለመገኘታቸውም ሂደቱ ሳይከናወን ቀርቷል።

ዮን ከሳምንታት በፊት ባወጁት ወታደራዊ አገዛዝ ምክንያት ከስልጣናቸው እንዲወገዱ መደረጋቸው ይታወሳል።

የአገራቸውን ዴሞክራሲ ከሰሜን ኮሪያ ሰርጎ ገቦች ለመከላከል በሚል ያወጡት አዋጅ መሆኑን በመጥቀስ ለአጭር ጊዜ የቆየውን ወታደራዊ አገዛዝ ተከላክለዋል። ተቃዋሚዎች ግን አመጽ ማነሳሳት ነው በሚል ገልጸውታል።

የቀድሞውን የመከላከያ ሚንስትር ኪም ዮንግ-ሁንን ጨምሮ ወታደራዊ አዛዦችና በርካታ ከፍተኛ ባለስልጣናት ከአዋጁ ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር ውለዋል።

ከአንድ ወር በፊት ደግሞ ተቃዋሚዎች በበላይነት የያዙት የአገሪቱ ፓርላማ ፕሬዝዳንቱ ስልጣን እንዲለቁ ሲል ሃሳብ መቅረቡን ተከትሎ ዮን ስልጣን ለቀዋል።

ዮንን በመተካት ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት በመሆን የተሾሙት ሃን ደክ-ሶ የተቃዋሚዎችን ሃሳብ ባለማሟላታቸው ከስልጣን እንዲወርዱ ተደርጓል።

ዮን በቁጥጥር ስር ከመዋላቸው በፊት ተቀርጾ ይፋ በተደረገ ቪዲዮ፤ መርማሪዎችን ለማቆም ያልፈለጉት አመጽ እንዳይቀጣጠል በማሰብ መሆኑን ገልጸዋል።

“ህገ ወጥ ምርመራ ቢሆንም ግን አላስፈላጊ ደም መፋሰስን ለማስወገድ በማሰብ ዛሬ ግቢውን መውረራቸውን ስመለከት ወደ ሙስና ምርመራ ቢሮ ለመሄድ ወሰንኩኝ” ብለዋል።

የዮን ፒፕል ፓወር ፓርቲ (ፒፒፒ) አባላት እስሩን ህገወጥ ሲሉ ማውገዛቸውን የአገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

መርማሪዎች የፕሬዝዳንቱ ግቢ እንዳይገቡ ለመከላከል መኖሪያቸውን ሲጠብቁ ከነበሩት መካከል የፒፒፒ አባላት ይገኙባቸዋል።

የፒፒፒ አባል የሆኑት ክዌን ሴዮንግ-ዶንግ በተፈጠረው ነገር “ማዘናቸውን” ለፓርላማው ተናግረዋል።

ፕሬዝዳንቱን በቁጥጥር ስር ለማዋል በነበረው ሂደት ለተጎዱ ዜጎች መርማሪዎች እና ፖሊሶች ተጠያቂ እንደሚሆኑም ተስፋቸውን ገልጸዋል።

የአገሪቱ የከፍተኛ ባለስልጣናት ሙስና ቢሮ ፕሬዝዳንቱ ባለፈው ወር ካወጁት የወታደራዊ አገዛዝ አዋጅ ጋር በተያያዘ በአመጽ እና ስልጣንን ያለአግባብ በመጠቀም እንደሚጠይቃቸው ታውቋል።