
15 ጥር 2025, 08:01 EAT
ተሰናባቹ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ሽብርተኝነትን በመንግሥት ደረጃ ስፖንሰር ታደርጋለች በሚል የተፈረጀችውን ኩባ ከዝርዝሩ ሊያስወጧት እንደሆነ ተናገሩ።
ኩባን ከዚህ የሽብር ዝርዝር የሚያስወግዷት እስረኞችን ለመፍታት በተደረገ የስምምነት አካል እንደሆነ ዋይት ሃውስ አስታውቋል።
የባይደንን ውሳኔ ተከትሎ ብዙም ሳይቆይ ኩባ “በተለያዩ ወንጀሎች” ያሰረቻቸውን 553 እስረኞች እንደምትፈታ አስታውቃል። ከሚፈቱት መካከል ከአራት ዓመታት በፊት በነበረው የኩባ ጸረ-መንግሥት ተቃውሞ ተሳታፊዎች እንደሚጨምር ተስፋ ተጥሏል።
ተመራጩ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በአውሮፓውያኑ 2021 የፕሬዚዳንት ዘመናቸው የመጨረሻ ቀናት ኩባን ወደ አሸባሪነት ፍረጃ በመመለስ እና የአሜሪካን የምጣኔ ኃብት እርዳታ እና የጦር መሳሪያ ወደ አገሪቱ መላክን አግደው ነበር።
ነገር ግን በዚህ ሳምንት ማክሰኞ የባይደን አስተዳደር ባለስልጣን ስለ ሁኔታው በተደረገ ግምገማ አገሪቱን እንደገና በሽብርተኝነት ለመፈረጅ የሚያደርግ “ምንም መረጃ” አልቀረበም ብለዋል።
ኩባ በበኩሏ የባይደን እርምጃ የሚሸፍነው “ውስን ቢሆንም” በትክክለኛው አቅጣጫ አንድ እርምጃ ነው ብላለች።
- እስራኤል እና ሐማስ ከስምምነት ለመድረስ ተቃርበዋል፤ የተኩስ አቁም ምንድን ነው? ጦርነትን ያስቆማል?15 ጥር 2025
- የነዳጅ መኪኖችን አስቀርታ የኤሌክትሪክ መኪኖችን በመጠቀም ቀዳሚ የሆነችው ኖርዌይ15 ጥር 2025
- በቻይና የተከተሰው አዲሱ ቫይረስ እንዴት ይተላለፋል? ለምንስ ልጆች እና አዛውንቶችን ያጠቃል?15 ጥር 2025
“ይህ ውሳኔ በኩባ የምጣኔ ኃብትን በማንኮታኮት በህዝቡ ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትሉ የማስገደድ እርምጃዎችን የሚገታ ነው” ሲል የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባወጣው መግለጫ አትቷል።
በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን አደራዳሪነት በኩል የተደረሰውን ስምምነት ተከትሎ በመቶዎች የሚቆጠሩ እስረኞች “ቀስ በቀስ ይፈታሉ” ሲል ከሰዓታት በኋላ በተለየ መግለጫ ተጠቅሷል።
ስለ እስረኞቹ ዝርዝር መግለጫ ያልተጠቀሰ ቢሆንም ስምምነቱ በአውሮፓውያኑ 2021 የአገሪቱን የምጣኔ ኃብት ቀውስ ተከትሎ በኩባ በተነሳው ጸረ መንግሥት ተቃውሞ የታሰሩ ግለሰቦችን እንዲፈቱ ያደርጋል የሚል ተስፋ ተጥሏል።
ኩባ አሜሪካ መንግሥታቸውን አሸባሪ ብላ ከፈረጀቻቸው ሰሜን ኮሪያ፣ ሶሪያ እና ኢራን ጋር አንድ ላይ ተቀምጣለች።
አሜሪካ እነዚህ አገራትን “አለም አቀፍ የሽብርተኝነት ድርጊቶችን” በተደጋጋሚ ድጋፍ ያደርጋሉ ስትል ትከሳቸዋለች።
ኩባ የተጣለባት የሽብርተኝነት ፍረጃ በአውሮፓውያኑ 2015 በፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ተነስቶ የነበረ ቢሆንም ዶናልድ ትራምፕ ወደ ዝርዝሩ መልሰዋታል።
ዶናልድ ትራምፕ ኩባን ወደዚህ ፍረጃ በመመለስ ረገድ የኮሚኒስቷን አገር የቬንዙዌላ መሪ ኒኮላስ ማዱሮ ድጋፍን ጠቅሰዋል።
በወቅቱ ይህንን የትራምፕ እርምጃ ኩባ ፖለቲካዊ እና “አስመሳይ” እና ስትል ጠርታው ነበር።
እስረኞች እንዲፈቱ እድል ከማመቻቸቱ በተጨማሪ ይህ ውሳኔ በኩባ እና በአሜሪካ ያለውን ግንኙነት ወደ መደበኛ ሁኔታ ለማምጣት እንደ አንድ እርምጃ ሊታይ ስለሚችል ጠቃሚነቱ ከወዲሁ እየተነገረ ነው።
ባይደን እቅዶቻቸውን ለአሜሪካ ኮንግረስ ማሳወቅ የሚኖርባቸው ሲሆን በተጨማሪም በአንዳንድ ኩባውያን ላይ ትራምፕ የጣሉትን የፋይናንስ ገደቦችን መቀልበስንም እንደሚጨምር የዋይት ሃውስ መግለጫ ጠቁሟል።
ከቀናት በኋላ ወደ ስልጣን የሚመለሱት ትራምፕ ይህንን ውሳኔ ይሽሩት ይሆን የሚለው ግልጽ አይደለም።