
ከ 9 ሰአት በፊት
የአዲስ አበባ ከተማ አውቶብስ አገልግሎት ድርጅት “በድልድል እና ምደባ” 400 የሚሆኑ ሠራተኞችን ከጥር ጀምሮ ከሥራ ማሰናበቱን ሠራተኞች እና ድርጅቱ ተናገሩ።
በ2015 ዓ.ም. “የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት” በሚል ከ70 ዓመታት በላይ ለአዲስ አበባ የትራንስፖርት አገልግሎት ሲሰጥ የነበረው አንበሳ ባስ እና ሸገር ብዙኃን ትራንስፖርት ተዋህደው የልማት ድርጅት ተመሥርቷል።
ይህን ተከትሎ “ሪፎርም” ማድረግ የጀመረው ድርጅቱ፤ባከናወነው ድልድል እና ምደባ ሠራተኞች “ያለአግባብ” እና “በዘፈቀደ” ከሥራ ተባረናል ሲሉ ይናገራሉ።
የአዲስ አበባ ከተማ አውቶብስ አገልግሎት ድርጅት የብቃት ፈተና እና ውድድር ያላለፉ ሠራተኞችን ከሥራ መቀነሱን በመግለፅ “የሪፎርም ባሕሪ ነው” ሲል ለቢቢሲ በጉዳዩ ላይ ምላሽ ሰጥቷል።
ድርጅቱ ባለፈው ዓመት “የሥራ መሪዎች እና ሠራተኞች የድልድል እንዲሁም ምደባ አፈፃፀም” የተባለ መመሪያ ያወጣ ሲሆን፤ በዚህ መመሪያ መሠረትም “በጥናት” አዲስ መዋቅር ስለማዘጋጀቱ ሠራተኞች ተናግረዋል።
ለሠራተኞቹ መመሪያውን ሲያስተዋውቅ የብቃት ፈተና ሰጥቶ ፈተናውን ባያልፉ እንኳ አንድ የደረጃ እርከን ዝቅ ተደርገው ሥራቸውን እንደሚቀጥሉ መተማመኛ መስጠቱን ተናግረዋል።
ተቋሙ ይህን ቢልም ፈተናውን ያለፉም ያላለፉም፤ የትምህርት እና የሥራ ልምድ ያላቸው ሠራተኞችን “ያለምንም ማስጠንቀቂያ” ከሥራቸው እንዳባረረ ስድስት ሠራተኞች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ከሥራ የተሰናበቱት ሠራተኞች ቁጥር 480 እንደሚሆን ሠራተኞች ቢናገሩም፤ ድርጅቱ ግን 382 ሠራተኞች ናቸው ብሏል።
ከሥራ የተሰናበቱት ሠራተኞች ከፅዳት እና የጥበቃ ሠራተኞች ጀምሮ በተቋሙ ለአስርት ዓመታት ያገለገሉ እና የጡረታ ዕድሜያቸው የተቃረቡ ሠራተኞችም እንደሚገኙበት ተናግረዋል።
“ምደባ ያላገኛችሁ ችግር የለውም ቦታ ይኖረናል፤ ትመደባላችሁ” እየተባልን ቆየን የሚሉ እና ከተባረሩ ሠራተኞች መካከል አንዷ የሆኑት ሠራተኛ፤ ታኅሣሥ 24/ 2017 ዓ.ም. በአስቸኳይ ስብሰባ ማስተባበያ በመስጠት ከሥራ እንደተሰናበቱ ገልፀዋል።
“የትምህርት ዝግጅት ችግር ነው እንዳይባል፤ ድግሪ ያለን ብዙዎች አለን። የሥራ ልምድም እንዳይባል እስከ 34 ዓመት ድረስ በተቋሙ የሠሩ ከእኛ ጋር አሉ” በማለት አላግባብ ከሥራ እንደተሰናበቱ ተናግረዋል።
የተሰጣቸው የስንብት ደብዳቤ “መስፈርቱን ስላላሟሉ” እንደሚል የተናገሩት ሠራተኛዋ፤ ስድስት ዓመት ከሠሩበት ተቋም “ማስጠንቀቂያ ባልተሰጠበት” ሁኔታ በመባረራቸው ግር እንደተሰኙ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
- በሎስ አንጀለስ ሰደድ እሳት የተጎዱ ሰዎችን የምትረዳው ትውልደ ኢትዮጵያዊት14 ጥር 2025
- እስራኤል እና ሐማስ ከስምምነት ለመድረስ ተቃርበዋል፤ የተኩስ አቁም ምንድን ነው? ጦርነትን ያስቆማል?15 ጥር 2025
- ናይጄሪያውያን በዘማሪ ጓደኛዋ ተቀልታ ለተገደለችው ሴት ሐዘናቸውን እየገለጹ ነው15 ጥር 2025
የብቃት ፈተናውን አልፈው “የትምህርት ዝግጅታችሁ አይጋብዝም” በሚል እንደተሰናበቱ የተናገሩ ሌላ ሠራተኛም፤ “ዱብእዳ” እንደሆነባቸው ገልፀዋል።
“ዝቅ ብላችሁ ትሠራላችሁ ብለው ሊያማክሩን ነው ብለን ስንጠብቅ [ጥር] ከአንድ ጀምሮ ውላችሁ ተቋርጧል የሚል መርዶ ነው የደረሰን” ብለዋል።
“ቅፅበታዊ ምት” ሲሉ የሥራ ስንበታቸውን የገለፁ ሌላ ሠራተኛ በበኩላቸው ፈተናውን ማለፋቸውን ጠቁመው፤ የደሞዝ እድገት ሲጠብቁ ከሥራ መሰናበታቸውን ተናግረዋል።
“[የተባልነው] ፈተናውን ያለፈ በመረጠው ቦታ ይመደባል፤ ፈተናውን የወደቀ ደግሞ ከደረጃው አንድ ዝቅ ተደርጎ ይሠራል ነው እንጂ የሥራ ዋስትናችንን እንስከምናጣ ድረስ አልጠበቅንም” ሲሉ ፈተናው የይስሙላ እንደነበር ጠቁመዋል።
በድርጅቱ ለ15 ዓመታት በጥበቃ ሥራ እንዳገለገሉ የተናገሩ ሌላ ተሰናባች ሠራተኛም የብቃት ፈተናውን ቢያልፉም “አትመጥኑም” ተብለው ከሥራ መሰናበታቸውን ገልፀዋል።
ከሥራ መባረራቸውንም “ጥቅም ለማግኘት” የተደረገ እርምጃ ነው ብለውም ያምናሉ።
“[ድርጅቱ] ጥበቃውን በኤጄንሲ ነው ያደረገው። ኤጄንሲ አምጥቶ ቀጠረበት። ኤጄንሲዎች ከእነርሱ ጋር [ትስስር] ስላላቸው ጥቅም ለማግኘት ነው” ሲሉ ከሰዋል።
ድርጅቱ በተባረሩ ሠራተኞች መደብ “ከኤጄንሲዎች” ሠራተኞችን መቅጠሩን አንድ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የድርጅቱ የሥራ ኃላፊ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
ሠራተኞች ባልጠበቁት ሁኔታ እና ባለው የኑሮ ውድነት ከሥራ መሰናበታቸው ሕይወታቸው ላይ ጫና ማሳደሩንም ገልፀዋል።
“ደሞዛችን ምንም ትንሽ ብትሆንም እሷን አብቃቅተን ነበር የምንኖረው። አሁን ግን በጣም ይከብዳል። . . . የቤት ኪራይ አለ፤ ከእኔ በላይ የባሱ [ሰዎች] አሉ። ባልና ሚስት ሆነው የተባረሩም አሉ” ሲሉ የአራት ልጆች አባት እንደሆኑ የተናገሩ ሠራተኛ ያሉበትን ሁኔታ ተናግረዋል።
“ይቺም ደሞዝ ሆና የቤት ኪራይ ከፍዬ ሳገኝ በልቼ ነበር የምኖረው። አሁን ላይ ግን ቤት ኪራይ መክፈል የምችለው ነገር የለም” ያሉ ሌላ ሠራተኛም “ውስብስብ ነው ያለብኝ” ብለዋል።
የቤተሰብ አስተዳዳሪ እንደሆኑ የተናገሩ አንድ ሠራተኛ፣ እርሳቸውን ጨምሮ ሌሎች ከሥራ የተሰናበቱ ሠራተኞች “ከባድ” ሁኔታ ውስጥ መሆናቸውን ተናግረዋል።
“ሁሉ ነገር ሰማይ ነው” ሲሉ የኑሮ ውድነቱን የገለፁ ሌላ ሠራተኛም፣ የሥራ ስንብቱን ዳፋ ሲናገሩ “ወይ ወደ ጎዳና ነው እያስወጣን ያለው፤ ወይም ወደ ውንብድና ነው” ሲሉ ከባድ ሁኔታ ላይ መውደቃቸውን አመልክተዋል።
ተቋሙ ሠራተኞችን ያባረረበት ምክንያት ጥያቄ እንደሆነባቸው የሚናገሩም ሲሆን፤ ከእርከናቸው እስከ አምስት ደረጃም ዝቅ የተደረጉ እና ወርሃዊ ደሞዛቸው በግማሽ የተቀነሰባቸው ሠራተኞችም እንደሚገኙ ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አውቶብስ አገልግሎት ድርጅት ምክትል ሥራ አስኪያጅ ሰብስባቸው መንግሥቴ ድርጅቱ በኮተቤ ዩኒቨርስቲ በኩል የሰጠውን የምዘና ፈተና እና በመዋቅር ላዘጋጃቸው መደቦች ተወዳድረው ያላለፉ ሠራተኞችን መቀነሱን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“አንድ የሥራ መደብ ላይ ስምንት ሰው የሚፈልግ ከሆነ መደቡ የሚጋብዘውን ስምንት ሰው ብቻ ነው የምናስገባው። የትምህርት ዝግጅቱ፣ የሥራ ልመዱ በቀጥታ የሚጋብዘው ሰው እንዲወዳደር ነው የሚፈለገው” ብለዋል።
“የሪፎርም ባሕሪ ነው” በማለት የሠራተኞችን ቅነሳ ከአቅም እና ከውድድር ጋር ያያዙት ምክትል ሥራ አስኪያጁ፤ “ሰዎችን አወዳድሮ በተገቢው ቦታ የማሠራት ሥራ ነው የተሠራው” ሲሉ የተቋሙን እርምጃ ገልፀዋል።
ለዚህም ማሳያ ሲያነሱ “ኧርባን ማኔጅመንት ቦታ ላይ የተወዳደሩ ሰዎች የያዙት ትምህርት ዝግጅት ሌላ ሊሆን ይችላል። በትምህርት ዝግጅቱ ቀረብ ያለ ሰው ሲገኝ ያን ሰው የማስቀደም ሥራ ተሠርቷል” ሲሉ “በመዋቅር ጥናት” መመራታቸውን ተናግረዋል።
ድርጅቱ ሠራተኞችን ከማሰናበቱ በፊት ወደ ሌሎች መደቦች ማዘዋወርን ጨምሮ አማራጮችን ስለመቃኘቱ ሲጠየቁ፤ ተቋሙ የልማት ድርጅት መሆኑን በማንሳት “ሌላ አማራጭ ማየት አልተቻለም” ብለዋል።
የተሰናበቱት ሠራተኞች መብታቸውን ለማስከር የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም እና የሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌደሬሽን ማመልከታቸውን ተናግረዋል።
“ሠራተኞች ይቀነሳሉ” የሚል መረጃ ብቻ እንደደረሳቸው ለቢቢሲ የተናገሩት የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌደሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ ኮንፌዴሬሽኑ የሥራ ስንብቱን አግባብነት እንደሚመለከተው ገልጸዋል።