በአደጋው የሞቱ ሰዎች

ከ 6 ሰአት በፊት

ወደ ባሕር ለመጥለቅ ጥቅም ላይ የሚውል ጀልባ በግብፅ መገልበጡን ተከትሎ ከአደጋው የተረፉ ሰዎች ባለሥልጣናትን ከሰዋል።

ጀልባው የተገለበጠው ቀይ ባሕር ላይ ነበር። ከአደጋው የተረፉ ሰዎች እንዳሉት አረብኛ ማንበብ ባይችሉም በአረብኛ የተጻፈ የዓይን እማኞች ሰነድ ላይ እንዲፈርሙ ተገደዋል።

ጀልባውን ያከራየው ድርጅት “ተጠያቂ አይደለም” የሚል ጽሑፍ ላይም ያለዕውቅናቸው እንዲፈርሙ መደረጋቸውን ተናግረዋል።

ከአደጋው የተረፉ 11 ሰዎች እንዳሉት አደጋው የተከሰተው በባሕር ወጀብ ምክንያት ነው በሚል የአደጋውን መንስዔ ለመሸፋፈን የግብፅ መንግሥት ሞክሯል።

ጀልባው 46 ሰዎች አሳፍሮ ሲጓዝ ነበር።

ባለፈው ኅዳር በደረሰው አደጋ የሞቱ አራት ሰዎች አስክሬን ሲገኝ ሁለት ብሪታኒያውያን ባሕር ጠላቂዎችን ጨምሮ የተቀሩት ሰባት ሰዎች እስካሁን አልተገኙም።

የግብፅ መንግሥትም የጀልባው ባለቤት ድርጅትም ለቢቢሲ ምላሽ አልሰጡም።

የዓይን እማኞች እንደሚሉት፣ የደኅንነት ጥበቃ በአግባቡ አልተረገም። የባሕር ጥናት ባለሙያ ጀልባቸው በወጀብ ተመቷል ለማለት አይቻልም ብለዋል።

ከአደጋው የተረፉት ሰዎች ሆስፒታል አልጋ ላይ ሳሉ “ምርመራ እንደተደረገባቸው” ተናግረዋል።

ምርመራውን ያደረጉት ግለሰቦች ዳኞች መሆናቸው ነው የተገለጸላቸው።

ሆስፒታል ያልገቡ እና ጉዳት ያልደረሰባቸው ከአደጋው የተረፉት ሰዎችም ተመሳሳይ ጫና እንደተደረገባቸው ተናግረዋል።

በዩናይትድ ኪንግደም ብሔራዊ የጤና አገልግሎት የምትሠራው ዶ/ር ሳራ ማርቲን “ሁሉም ሰው ቃሉን ሳይሰጥ ከሆቴል መውጣት አትችሉም ተባልን” ትላለች።

አደጋው ላይ የተካሄደውን ምርመራ ማን እየመራ እንዳለ ግልጽ እንዳልነበረ የዓይን እማኞቹ ተናግረዋል።

ምስክርነታቸው ያለ ዕውቅናቸው ወደ አረብኛ መተርጎሙ መርኅ እንደሚጥስ ገልጸዋል።

ስፔናዊው ባሕር ጠላቂ ሒሶራ ጎንዛሌዝ “ይሄ ወረቀት ምን እንደሆነና ለምን እንደምፈርም ንገሩኝ አልኳቸው” ብሏል።

ሊሳ ውልፍ
የምስሉ መግለጫ,ሊሳ ውልፍ

ቃላቸውን የተቀበላቸው እና በአረብኛ ተርጉሞ ለመርማሪዎች ያስገባው የጀልባ አከራይ ድርጅቱ መሆኑን ስታውቅ እንደደነገጠች ሊሳ ውልፍ ተናግራለች።

“ዳኛ እንዴት የሌላን ሰው ምስክርነት አስተርጉሞ ይወስዳል” ብላለች።

ከአደጋው የተረፈች ኖርዌያዊ መርማሪ ፍሮይዲስ አዳምሰን “ወረቀቱ ላይ የፈለጉትን ጽፈው ይሆናል። ከፈረምኩ በኋላ ፊርማዬ ሥር ጽሑፉ ምን እንደሚል እንደማላውቅ ጻፍኩ” ብላለች።

የዓይን እማኞች እንዳሉት፣ ዳይቭ ፕሮ ሊቬያቦርድ የተባለው የጀልባ አከራይ ድርጅት ከአደጋው የተረፉ ሰዎች ድርጅቱ ተጠያቂ አይደለም ብለው እንዲፈርሙም አስገድዷል።

አሜሪካዊው ባሕር ጠላቂ ጀስቲን ሆግስ እንዳለው ምስክርነታቸውን ሲሰጡ ድርጅቱን ከተጠያቂነት ነጻ የሚያደርግ ሰነድም ተሰጥቷቸዋል።

ይህንን ሰነድ ያቀረቡት አመራሮች ሳይሆኑ ድርጅቱ ነበር።

“ከባለሥልጣናት ጋር ሆኖ የድርጅቱ ሠራተኛ መጣ። ከተጠያቂነት ለማምለጥ ያደረጉት ጥረት አስደነቀኝ” ይላል።

የዓይን እማኞቹ የሰነዱ ቅጂ አልተሰጣቸውም። አንዳንዶቹ አረብኛውን በስልካቸው ለመተርጎም ሞክረዋል።

ጀልባው ሲገለበጥ ጠንካራ ወጀብ ባይኖርም ባለሥልናት ግን አደጋውን በወጀብ ምክንያት የተከሰተ ብለው ማለፍ እንደሚፈልጉ የዐይን እማኞች ገልጸዋል።

የባሕር ጥናት ባለሙያ ለቢቢሲ እንዳረጋገጡትም አደጋው በወጀብ የተነሳ አይደለም።

ሳራ እንዳለችው በአደጋው እጃቸው ያለባቸውን ሰዎች ማንነት ባታውቅም ወንጀል ተፈጽሟል።

በአደጋው ወቅት ፓስፖርቶቻቸው ጠፍተው ነበር። ከካይሮ ለመውጣት ሲሞክሩ ጀልባውን ያከራያቸው ድርጅት ከአገር መውጫ ሰነዶች ናቸው በሚል ድርጅቱን ከተጠያቂነት ነጻ የሚያደርግ ሰነድ ሊያስፈርማቸው ሞክሯል።

አሜሪካዊው ባሕር ጠላቂ ጀስቲን ሆግስ
የምስሉ መግለጫ,አሜሪካዊው ባሕር ጠላቂ ጀስቲን ሆግስ

አንደኛው የዓይን እማኝ “ወረቀቱ ከተጠያቂነት ነጻ እንደሚያደርጋቸው አወቅኩ። ሌሎቹን ከአደጋው የተረፉ ሰዎችም ነገርኳቸው። የሰነዱን ምንነት ስንረዳ ወዲያው በሌላ ይፋዊ ወረቀት ለወጡት። በጣም ነው የሚያናድደው” ብሏል።

ብሪታኒያውያኑ ጄኒ ካውሰን እና ታሪግ ሲንዳ አሁንም ድረስ እንደጠፉ ነው።

ጓደኛቸው አንዲ ዊልያምሰን “በጣም ደስ የሚሉ ጥንዶች ነበሩ” ስትል ገልጻቸዋለች።

ከአደጋው የተረፉ ሰዎች ጀልባው እንደተገኘ ቢነገራቸውም ኋላ ላይ በአደጋው መውደሙ ሲገለጽም ሰምተዋል። በይፋ ግልጽ ምርመራ እንዲደረግ ነው ጥያቄያቸው።

ከአደጋው የተረፈች ኖርዌያዊ መርማሪ ፍሮይዲስ አዳምሰን
የምስሉ መግለጫ,ከአደጋው የተረፈች ኖርዌያዊ መርማሪ ፍሮይዲስ አዳምሰን

“የግብፅ መንግሥት ጉዳዩን ሸፋፍኖ የቱሪዝም ኢንዱስትሪው እንዳይጎዳ ማድረግ ነው የሚፈልገው” ትላለች አንዲ።

ማሪታይም ሰርቬይ ኢንተርናሽናል የሚባል ተቋም በቀይ ባሕር የሚንቀሳቀሱ ጀልባዎች ላይ ፍተሻ አድርጓል።

አሁን አደጋው የደረሰበት ጀልባ አከራይ ድርጅት ባይካተተም በአጠቃላይ ጀልባዎቹ ዕድሳት እምብዛም እንደማይደረግላቸው ተቋሙ አስታውቋል።

ጀልባዎቹ ከደኅንነት ጥበቃ አንጻርም ብዙ ጉድለቶች እንዳሏቸው ተገልጿል።