ከአንድ ዓመት በላይ በተካሄደ ጦርነት የወደመችው ጋዛ
የምስሉ መግለጫ,ከአንድ ዓመት በላይ በተካሄደ ጦርነት የወደመችው ጋዛ

25 ነሐሴ 2024

ተሻሽሏል 15 ጥር 2025

የባሕረ ሰላጤዋ አገር ኳታር አደራዳራዳሪዎች እንደሚሉት እስራኤል እና ሐማስ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመድረስ ከጫፍ ደርሰዋል።

እስራኤል በሐማስ የተፈጸመባትን ድንገተኛ ጥቃት ተከትሎ በጋዛ ላይ እያካሄደችው ያለው መጠነ ሰፊ ወታደራዊ ዘመቻ 15 ወራትን ሊያስቆጥር በተቃረበበት ጊዜ ነው ሁለቱ ወገኖች ከስምምነት ለመድረስ መቃረባቸው የተነገረው።

እስራኤል ሐማስን አጠፋለሁ ብላ በጋዛ ላይ በከፈተችው ጥቃት ግዛቲቱ ከሞላ ጎደል ሙሉ ለሙሉ የወደመች ሲሆን፣ ከ45 ሺህ በላይ ሰዎች መገደላቸውን የጋዛ ጤና ሚኒስቴር አሳውቋል።

አሜሪካ እና ግብፅን ጨምሮ በዋናነት በኳታር አማካኝነት ባለፉት ወራት በጋዛ ተኩስ አቁም እንዲደረስ ሲጥሩ ቆይተዋል። ቢሆንም ግን ውጤታማ ሳይሆኑ አስካሁን ዘልቀዋል።

አሁን በእስራኤል እና በሐማስ መካከል ይደረሳል ተብሎ ተስፋ የተደረገበት ተኩስ አቁም በመጀመሪያ ጊዜያዊ እንደሚሆን እና በሂደት ወደ ዘላቂ የሰላም ስምምነት እንሚሸጋገር እየተነገረ ነው።

በዚህ ሂደት አሸማጋይ የሚሆኑት አገራት ሁለቱ ወገኖች ተቀራርበው ከስምምነት ላይ በመድረስ ጋዛን ከአንድ ዓመት በላይ ያወደመውን ጦርነት የሚያስቆም መቋጫ ላይ እንዲደረስ እየጣሩ ነው።

ከዚህ ቀደም በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ተፋላሚ ወገኖች ጦርነትን ለማስቆም የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ደርሰዋል። በተኩስ አቁም በዘላቂነት ሰላም ያመጡ እንዳሉ ሁሉ፣ ከተወሰነ ጊዜ ሰላም በኋላ ወደ ግጭት ያመሩም አሉ።

ለመሆኑ የተኩስ አቁም ስምምነት ምንድን ነው? የተኩስ አቁም ስምምነት ግጭትን በዘላቂነት ያስቆማል? ወይንስ ለተወሰነ ጊዜ ብቻ ፋታን የሚሰጥ ነው?

በጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ የሚጠይቁ ሰልፈኞች
የምስሉ መግለጫ,በጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ የሚጠይቁ ሰልፈኞች

የተኩስ አቁም ምን ማለት ነው?

እንደተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከሆነ “ተኩስ አቁም” ለሚለው ቃል ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያለው ፍቺ የለም። ቃሉ የመጣው “ተኩስ ማቆም” ከሚለው ወታደራዊ ትዕዛዝ የመጣ ሲሆን፣ “ተኩስ መጀመር” ከሚለው ትዕዛዝ ተቃራኒ ነው።

ሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች በድርድሩ ላይ እንደሚወስዱት ትርጉም ሊሆን ይችላል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት “ተኩስ አቁም” እና “ግጭት ማቆም” በሚሉት ቃላት መካከል ብዙ ጊዜ ልዩነት እንዳለ ገልጿል።

“የግጭትን ማቆም” ጦርነትን ለማቆም የሚደረግ መደበኛ ያልሆነ ስምምነት ነው ይላል።

“የተኩስ አቁም” የበለጠ መደበኛ ነው። በተጨማሪም ይህ የተኩስ አቁም ዓላማን፣ በቀጣይ የሚኖርን የፖለቲካ ሂደት፣ መቼ ተግባራዊ እንደሚሆን እና የሚሸፍነውን አካባቢም የሚያካት ነው።

ምን ዓይነት ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች እንደሚፈቀዱ እና እንደማይፈቀዱ እንዲሁም የተኩስ አቁሙ እንዴት ክትትል እንደሚደረግበት ሊገልጽ ይችላል።

የላይቤሪያ አማጺያን
የምስሉ መግለጫ,በላይቤሪያ የተካሄደውን የእስር በርስ ጦርነት እንዲቆም በተዋጊዎች መካከል የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት ጠቅሟል

ለምሳሌ የላይቤሪያ የእርስ በርስ ጦርነት በአውሮፓውያኑ 1993 እንዲጠናቀቅ ያደረገው የብሔራዊ ጊዜያዊ መንግሥቱ ከላይቤሪያ አርበኞች ግንባር እና ከተባበሩት የነጻነት ዘመቻ ጋር ስምምነት መድረሱ ነው።

ሁለቱም ወገኖች የጦር መሳሪያ ማስመጣት እንዲያቆሙ፤ ወታደራዊ ቦታዎችን ላለመቀየር ወይም ላለማጥቃት፣ ተጨማሪ ጦርነት ላለመቀስቀስ እና ፈንጂዎችን እና ተቀጣጣይ መሳሪያዎችን ላለመጠቀም ተስማምተዋል።

የተኩስ አቁም ቋሚ ነው ወይስ ጊዜያዊ?

ሁለቱም ሊሆን ይችላል ይላል የመንግሥታቱ ድርጅት።

አንዳንድ ጊዜ በጦርነት ውስጥ ያሉት ሁለቱ ወገኖች ጊዜያዊ ወይም የመጀመሪያ ደረጃ የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ ይስማማሉ።

ይህ የሚደረገው ጥቃትን ለመቀነስ ወይም ሰብአዊ ቀውስን ለማቃለል ሊሆን ይችላል።

በኅዳር ወር በእስራኤል እና በሐማስ በሚመሩ ታጣቂ ቡድኖች መካከል ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ ከስምምነት ሲደረስ፤ ሐማስ 105 ታጋቾችን ሲለቅ እስራኤል በበኩሏ 240 የሚሆኑ እስረኞችን ፈትታለች።

የመጀመሪያ ደረጃ የተኩስ አቁም ቀጣይ ድርድርን የሚያግዝ እና ለዘላቂ የተኩስ አቁም መንገድ ለመክፍት የሚረዳ ካባቢን ሊፈጥር ይችላል።

የኢትዮጵያ እና የኤርትራ መሪ ስምምነቱን በፈረሙ ጊዜ
የምስሉ መግለጫ,በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል የተደረገው የድንበር ጦርነትን ለማስቆም በአልጀርስ ስምምነት ተፈራርመዋል

እአአ በ2000 ኢትዮጵያ እና ኤርትራ በመካከላቸው ያላቸውን ግጭት ለማቆም ስምምነት ተፈራርመዋል። ይህም ለዘላቂ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመድረስ እንዲቻል ነበር። በዚህም የሁለቱን አገራት ጦርነት ያቆመው የአልጀርስ ስምምነት ተፈርሟል።

ሆኖም ግን በተስማሚዎቹ መካከል የሚጠበቀው እርምጃ ካልተወሰደ የተኩስ አቁም ስምምነት መጣስ፣ አለመሳካት እና በመሳሰሉት ምክንያቶች ጦርነቶች ሊቀጥሉ ይችላሉ።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሊባኖስ የእርስ በርስ ጦርነትን ለማስቆም ተከታታይ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ እአአ በ1978፣ 1981 እና 1990 ሞክሯል። ከእያንዳንዱ ስምምነት በኋላ ጦርነት አገርሽቷል። በኋላም በ1975 የተጀመረው ጦርነት እስከ 1990 ዘልቋል።

የአይአርኤ ታጣቂዎች
የምስሉ መግለጫ,በሰሜን አየር ላንድ የአይአርኤ ታጣቂዎች በደረሱት ስምምነት ትጥቅ ፈትተዋል

በአንዳንድ ሁኔታዎች ደግሞ አንደኛው ወይም ሁለቱም ተፋላሚ ወገኖች በመሬት ላይ ያላቸውን አቋም ለማጠናከር የተኩስ አቁሙን ሊጠቀሙበት ሊፈልጉ ይችላሉ።

በሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች መካከል የተሳካ የሠላም ንግግሮችን ተከትሎ ጊዜያዊ ወይም ቋሚ የተኩስ አቁም ሊደረግ ይችላል።

ለምሳሌ በአውሮፓውያኑ 1998 በሰሜን አየርላንድ የተደረገው የጉድ ፍራይዴይ ስምምነት አይአርኤ እና ታማኝ ቡድኖቹ መሳሪያቸውን “ከጥቅም ውጪ” ለማድረግ መስማማታቸውን ያካትታል።

ስምምነቱ ቀጣይነት ያለው ሰላም እና ስምምነትን ለማበረታታት የታቀዱ አንቀጾችንም ይዟል።

ሐማስ እና እስራኤል ከወራት በፊት ለአጭር ጊዜ በደረሱት የተኩስ አቁም ታጋቾች እና እስረኞች ተለቀዋል
የምስሉ መግለጫ,ሐማስ እና እስራኤል ከወራት በፊት ለአጭር ጊዜ በደረሱት የተኩስ አቁም ታጋቾች እና እስረኞች ተለቀዋል

ምን ዓይነት የተወሰነ የተኩስ አቁም ዓይነቶች አሉ?

እስራኤል እና ሐማስ በኅዳር 2023 የደረሱትን ጊዜያዊ የተኩስ አቁም “የሰብዓዊ ተኩስ አቁም” ብለው ጠርተውታል።

ሰብዓዊ ተኩስ አቁም ግጭቱን ለመቀነስ ወይም ሰብዓዊ ቀውስን ለማቃለል አንዳንድ ጊዜ ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል።

ለምሳሌ የሱዳን መንግሥት በዳርፉር የተካሄደውን ጦርነት ለ45 ቀናት በማስቆም የሰብዓዊ ዕርዳታ እንዲደርስ ከሱዳን ነፃ አውጪ ንቅናቄ እና ከፍትህ እና የእኩልነት ንቅናቄ ጋር የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ደርሷል።

በ2004 ኢንዶኔዥያ በሱናሚ ከተመታች በኋላ በአካባቢው እርዳታ እንዲደርስ የኢንዶኔዥያ መንግሥት እና የፍሪ አቼ ንቅናቄ የተኩስ አቁም አውጀዋል።

መልክዓ ምድራዊ የተኩስ አቁም ተብሎ የሚጠራው ደግሞ በተወሰነ አካባቢ ላይ የሚደረጉ የተኩስ አቁም ስምምነቶች ሊሆኑ ይችላሉ።

እአአ በ2018 ደግሞ በተባበሩት መንግሥታት አደራዳሪነት የየመን መንግሥት እና ሁቲዎች በቀይ ባሕር ሆዴይዳ ወደብ ዙሪያ የሚደረገውን ጦርነት በማስቆም የአካባቢውን ሕዝብ ለመጠበቅ ስምምነት ላይ ደርሰዋል።