በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኧርቪን ማሲንጋ

ዜና መንግሥትና ታጣቂዎች በየትኛውም ቦታና ሰዓት ለመነጋገር ዝግጁ ሲሆኑ ለማገዝ ዝግጁ መሆኗን አሜሪካ…

ሲሳይ ሳህሉ

ቀን: January 15, 2025

‹‹በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች መንግሥትና ታጣቂዎች ገንቢ በሆነ መንገድ በየትኛውም ቦታና ጊዜ ሰላማዊ ንግግር ለማድረግ ዝግጁ ሲሆኑ ለማገዝ ዝግጁ ነን፤›› ሲሉ፣ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኧርቪን ማሲንጋ አስታወቁ፡፡

አምባሳደሩ ‹‹ለኢትዮጵያ ሕዝብ የተላለፈ መልዕክት›› በሚል ሰኞ ጥር 5 ቀን 2017 ዓ.ም. ባወጡት መግለጫ፣ ‹‹በችግርና በድል ውስጥ ሆኖ 120 ዓመታት በዘለቀው የሁለቱ አገሮች ግንኙነት ኩራት ይሰማኛል፤›› ብለዋል፡፡

በአማራ ክልል ተጀምሮ የነበረው የሰላም ካውንስል መልካም ጅማሮ እንደነበር የገለጹት አምባሳደሩ፣ የፕሪቶሪያ ስምምነት ሙሉ በሙሉ እንዲፈጸምና የኢትዮጵያ ሕዝብ የሰላም ትሩፋቱን እንዲቀዳጅ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

‹‹የትግራይ ክልል የፖለቲካ መሪዎች በሕዝቡ ጥቅም ላይ ያተኩራሉ የሚለው ጉዳይ ብዙዎቹ የትገራይ ተወላጆች የሚጋሩት ተስፋ ነው፤›› ያሉት አምባሳደሩ፣ ‹‹ከኢትዮጵያ ውጪ ያሉ ከፋፋይና መርዛማ ንግግሮችን የሚለቁ አካላት ሊያቆሙ ይገባል፤›› ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ይፋዊና ይፋዊ ባልሆነ መንገድ የአገራዊ ምክክሩንና የብሔራዊ ተሃድሶ ሒደትን በተመለከተ ንግግር ማድረጋቸውን ያስታወሱት አምባሳደሩ፣ አሜሪካ ለመልሶ ማቋቋምና ለብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ሥራ ማከናወኛ የሚሆን 16 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ማድረጓን አስታውቀዋል፡፡

በአማራ፣ በኦሮሚያና በሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች ግጭት ውስጥ የገቡ አካላት ንፁኃንን እንዲጠብቁ፣ ሰብዓዊ መብቶችን እንዲያከብሩና ለሰላማዊ ድርድር ዝግጁ እንደሆኑ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች ባለው ግጭት የወንጀልና የዕገታ ድርጊቶች መበራከታቸውን ጠቅሰው፣ ድርጊቶቹ በሰላማዊ የሰዎች ዝውውር፣ በኢኮኖሚ ዕድገት፣ እንዲሁም በዕርዳታ ሥርጭት ላይ መሰናክል መፍጠሩን ተናግረዋል፡፡

ሰብዓዊ ቀውሱ በከፍተኛ መጠን መጨመሩን የገለጹት አምባሳደሩ፣ ሕፃናት ከትምህርት ቤት ውጪ መሆናቸውን፣ የጤና አገልግሎት አቅርቦት መገደቡን፣ እንዲሁም አርሶ አደሮች ሰብል መዝራት አለመቻላቸውን ዘርዝረዋል፡፡

 የሀብት ብዝበዛ በተለይም ሕገወጥ ማዕድን ማውጣትና የደን ምንጣሮ መኖሩን፣ ይህም ጦርነቱን የሚያባብስና የተፈጥሮን ምኅዳር የሚጎዳ ነው ብለዋል፡፡

እ.ኤ.አ. በ2024 ስምንት የዕርዳታ ሠራተኞች መገደላቸውን የገለጹት አምባሳደሩ፣ የስድስቱ ግድያ በአማራ ክልል መፈጸሙን አብራርተዋል፡፡

የሲቪክ ምኅዳሩ የተጠበቀ እንዲሆንና የመገናኛ ብዙኃን በነፃነት እንዲሠሩ ሁሉም ባለድርሻዎች ኃላፊነት አለባቸው ብለዋል፡፡

የአሜሪካ የግል ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት በመሳተፍ ቁልፍ ሚና እየተጫወቱ መሆኑን ጠቅሰው፣ ለአብነት ቦይንግ ኩባንያና የኢትዮጵያ አየር መንገድ በተጠናቀቀው ዓመት የፈጸሙት 127 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት የ87 ቦይንግ አውሮፕላኖች ግዥ አስታውሰዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ከዓለም አቀፍ ወዳጆች በተለይም ከዓለም የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) እና ከዓለም ባንክ ጋር፣ በጋራ ለማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙ ስኬት መሥራቱን ጠቅሰዋል፡፡

በኢትዮጵያ የትምህርት ጥራትን ለማሳደግ እንዲረዳ፣ የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ከአሜሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር የማስተሳሰር ሥራ መከናወኑን ተናግረዋል፡፡

በጤናው ዘርፍ አሜሪካ ባደረገችው ኢንቨስትመንት የቲቢና ተያያዥ በሽታዎች ሞት እንዲቀንስ፣ የሴቶችን ቅድመና ድኅረ ወሊድ የጤና አገልግሎት እንዲስፋፋ፣ ከ2.1 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ከወባ በሽታ ለመከላከል መሠራቱን ተናግረዋል፡፡ በተለይም በዓለም አቀፍ የጤና ደኅንነት ፕሮግራም አማካይነት በኢትዮጵያ የጤና ዘርፍ የመከላከልና የመቆጣጠር ሥራ በስፋት ይቀጥላል ብለዋል፡፡

ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት በአሜሪካ ዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅት (USAID) አማካይነት ለጤናው ዘርፍ አራት ቢሊዮን ብር፣ እንዲሁም ፔፋር በሚባለው የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ፕሮግራም ሦስት ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስት መደረጉን አክለዋል፡፡

በቀጣናው ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ስደተኞች አስተናጋጅ ለሆነችው ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ2024 በተለይም ለስደተኞችና ለተቀባይ ማኅብረሰብ ክፍሎች የአገር ውስጥ ተፈናቃዮችን ጨምሮ፣ ለሰብዓዊ አገልግሎት ለሚደረገው ሥራ  150 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ መደረጉን አስረድተዋል፡፡

የአሜሪካ መንግሥት በ676 ሚሊዮን ዶላር በግጭት፣ በድርቅና በምግብ እጥረት ለተጎዱ ዜጎችና ወሳኝ የሰብዓዊ ዕርዳታ ለሚፈልጉ ዜጎች በተያዘው ዓመት ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም 114 ሚሊዮን ዶላር ለሴፍቲኔት ፕሮግራም፣ ዩኤስአይዲ ከጀመራቸው የ251 ሚሊዮን ዶላር ፕሮግራሞች ውስጥ 48 ሚሊዮን ዶላር ለአስቸኳይ ጊዜ አደጋ ፕሮጀክት መመደቡን ገልጸዋል፡፡