

የሚኒስትሮች ምክር ቤት 41ኛ መደበኛ ስብሰባ
ዜና የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ሙሉ በሙሉ ፈረሰ
ቀን: January 15, 2025
የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ሙሉ በሙሉ በሕግ ፈርሶ መብቶቹንና ግዴታዎቹ ወደ ዕዳና ሀብት አስተዳደር ኮርፖሬሽን መተላለፉን፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት አስታወቀ፡፡
ምክር ቤቱ ማክሰኞ ጥር 6 ቀን 2017 ዓ.ም. ባካሄደው 41ኛ መደበኛ ስብሰባ፣ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደርን ለማፍረስ በቀረበ ረቂቅ ደንብ ላይ ተወያይቶ ውሳኔ ማሳለፉን አስታውቋል፡፡ በመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ሥር የነበሩ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች፣ ወደ ኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ በይፋ የተቀላቀሉት ባለፈው ወር 2017 ዓ.ም. ነበር፡፡
አስተዳደሩ ከመፍረሱ በፊት የኢትዮ ፖስታ፣ የኢትዮ ኢንጅነሪንግ ግሩፕ፣ የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅት፣ የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን፣ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልና በኢትዮ ፋርማ ግሩፕ ሥር ተጠሪ የሆኑት የብሔራዊ የእንስሳት ጤና ጥበቃ ኢንስቲትዩትና ሺልድ ቫክስ የተሰኙ ድርጅቶችን ሲያስተዳድር ነበር፡፡
አስተዳደሩ የፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲና የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን ይባሉ የነበሩ ሁለት ተቋማት ተዋህደው በ1996 ዓ.ም. መመሥረቱ ይታወሳል፡፡ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር በ2011 ዓ.ም. በወጣ አዋጅ በድጋሚ እንደ አዲስ ተቋቁሞ ነበር፡፡
የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ተቋም በመንግሥት በጀት ይተዳደደር የነበረ ሲሆን፣ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ውጤታማ፣ ተወዳዳሪና አትራፊ እንዲሆኑ ዘመናዊ የኮርፖሬት አስተዳደርና ኮርፖሬት ፋይናንስ ሥርዓት መዘርጋትና ሥራ ላይ መዋሉን የሚከታተል ተቋም ነበር፡፡
በተጨማሪም የድርጅቶችን አመራርና አስተዳደር መከታተል፣ በአክሲዮን ማኅበራት ውስጥ መንግሥትን በመወከል የመንግሥት የባለቤትነት መብት ማስከበር የሚሉት ኃላፊነቶቸ ተሰጥተውት ነበር፡፡
የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር የፕራይቬታይዜሽን ሥራዎች ወደ ዕዳና የሀብት አስተዳደር ኮርፖሬሽን ተላልፈው እንዲከናወኑ ለማስቻል፣ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደርን በሕግ አፍርሶ መብቶቹንና ግዴታዎቹን ለኮርፖሬሽኑ ማስተላለፍ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፣ ደንቡ መውጣቱ አስፈላጊ መሆኑን፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በውሳኔው አስታውቋል፡፡ የአስተዳደሩ ሠራተኞች ወደ ተለያዩ ተቋማት መመደባቸውም ተገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ማሻሻያ አካል ሆኖ የተመሠረተው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ በሥሩ 40 የልማት ድርጅቶችን በባለቤትነት እያስተዳደረ ይገኛል፡፡
የሚኒስትሮች ምክር ቤት በተመሳሳይ ባደረገው ስብሰባ የኢትዮጵያ መንግሥት ከዓለም ዓቀፍ የልማት ማኅበር ጋር ለኢትዮጵያ ዘመናዊ የመንግሥት አገልግሎት ማሻሻያ ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የሚውል 69 ሚሊዮን ዶላር፣ እንዲሁም ለፋይናንስ ዘርፍ ማጠናከሪያ ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የሚውል 681 ሚሊዮን ዶላር የፋይናንስ ድጋፍና የብድር ስምምነቶችን ማፅደቁን አስታውቋል፡፡
ሁለቱም ብድሮች ከወለድ ነፃ፣ እንዲሁም 0.75 በመቶ የአገልግሎት ክፍያ የሚከፈልባቸው ሆኖ የስድስት ዓመት የችሮታ ጊዜን ጨምሮ በ38 ዓመታት ውስጥ ተከፍለው የሚጠናቀቁ ናቸው ተብሏል፡፡
ምክር ቤቱ የኢንቨስትመንት ማበረታቻ ደንብን ለማሻሻል በወጣ ደንብ ላይ የተወያየ ሲሆን፣ በሥራ ላይ ባለው አዋጅ ደንቡ ከመውጣቱ በፊትም ሆነ ከዚያ በኋላ በተለያዩ ዘርፍ የተሰማሩ ኩባንያዎች የአፈጻጸም ችግር እያጋጠማቸው በመሆኑ፣ ድንጋጌዎች ግልጽ እንዲሆኑ ለማድረግ ታስቦ የተዘጋጀ ማሻሻያ መሆኑ ተገልጿል፡፡