

ማኅበራዊ አገልግሎት የማይሰጡና 32 ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው ምግብና የንፅህና መጠበቂያ ምርቶች ተወገዱ
ቀን: January 15, 2025
ባለፉት ስድስት ወራት ከ32 ሚሊዮን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው፣ የተበላሹ ምግቦችና የንጽሕና መጠበቂያ ምርቶች መወገዳቸውን፣ የአዲስ አበባ ከተማ ምግብና መድኃኒት አስተዳደር ቁጥጥር ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡
ባለሥልጣኑ ይህንን ያስታወቀው ሰኞ ጥር 5 ቀን 2017 ዓ.ም. በጥምቀት በዓል ወቅት ኅብረተሰቡ መንገድ ላይ ስለሚጠቀማቸው ምግብ ነክ ምርቶች አስመልክቶ፣ መደረግ ስላለበት ጥንቃቄ ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሲሰጥ ነው፡፡
የባለሥልጣኑ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ እንጋ እርቃታ፣ በ2017 በጀት ዓመት በስድስት ወራት በተደረገ ዳሰሳ ከ32,627,459 ብር ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የምግብና ጤና ነክ ምርቶች እንደተወገዱ ተናግረዋል፡፡
በባለሥልጣኑ 11 ቅርንጫፎችና በማዕከል በ26,552 የምግብና የጤና ነክ አምራች ኢንዱስትሪዎች ላይ የቁጥጥር ሥራ መከናወኑን ገልጸው፣ የተለያዩ ችግር ያሉባቸው ምርቶች እንደተያዙና ይዘው በተገኙት ላይም ሕጋዊ ዕርምጃ መወሰዱን ገልጸዋል፡፡
ሕገወጥ ዕርድ፣ ምንጫቸው ያልታወቀ የዕርድ ውጤቶች፣ ጊዜ ያለፈባቸው ምርቶች፣ ከሌሎች ባዕድ ነገሮች ጋር መቀላቀልና ሌሎችም ችግሬች በክትትል ወቅት እንደተገኙ አስረድተዋል፡፡
ባለፉት ስድስት ወራት በተከናወኑ የቁጥጥር ሥራዎች በ466 ተቋማት ላይ አስተዳደራዊ ዕርምጃ መወሰዱን፣ የተያዙት ምርቶችም መወገዳቸው ተናግረዋል፡፡
ዕርምጃ ከተወሰደባቸው ተቋማት ውስጥ ለ372 ተቋማት የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ፣ በ92 ተቋማት ላይ ጊዜያዊ እሸጋ፣ ሁለት ተቋማት ከተፈቀደላቸውና ከተሰጣቸው የብቃት ውጪ ማረጋገጫ ሲሠሩ በመገኘታቸው ፈቃዳቸው እንዲሰረዝ መደረጉን ገልጸዋል፡፡
የባለሥልጣኑ ዋና ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ሙሉመቤት ታደሰ በበኩላቸው፣ ሰሞኑን በሚከበረው የጥምቀት በዓል ኅብረተሰቡ የታሸጉና በመደበኛነት የሚቀርቡ ምግብና መጠጦችን በጥንቃቄ እንዲጠቀም አሳስበው፣ ባለሥልጣኑም ተገቢውን ቁጥጥር ያደርጋል ብለዋል፡፡
ከጥምቀት በዓል ጋር ተያይዞም ኅብረተሰቡ የሚጠቀማቸውን ምግቦችንና የፋብሪካ ውጤቶችን ጥራትና የመጠቀሚያ ጊዜ ያላለፈባቸው መሆን አለመሆናቸውን ማረጋገጥ እንዳለበት አሳስበው፣ የተበላሹ ምርቶችን የሚሸጡ ተቋማት ሲያጋጥሙ ጥቆማ እንዲሰጥ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ወ/ሮ ሙሉመቤት፣ ደኅንነቱ የተጠበቀ የምግብና የመድኃኒት አቅርቦት እንዲኖር የቁጥጥርና የክትትል ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሆነ፣ ባለሥልጣኑ በተሰጠው ኃላፊነት ምርቶቹን የማስወገድና የተጠያቂነት ሥራ እያከናወነ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ቁጥጥር በሚደረግበት ወቅትም ከተገኙ ሕገወጥ ድርጊቶች መካከል ከቄራ ውጪ ዕርድ ማከናወን፣ ከበርበሬ ጋር ባዕድ ነገሮችን ቀላቅሎ ለገበያ ማቅረብ፣ ምንጫቸው የማይታወቁ ምርቶችን ለገበያ ማቅረብና የመሳሰሉ ድርጊቶች እንደሚገኙበት አክለዋል።
ነጋዴው ለማኅበረሰቡ የፍጆታ ምርቶችን ጥራትና ደኅንነት በመጠበቅ የማቅረብ ኃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።