
January 12, 2025
የአዲስ አበባ ንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ወ/ሮ መሰንበት ሸንቁጤ
የአዲስ አበባ ንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ለትናንት ጥር 3 ቀን 2017 ዓ.ም. ጠርቶ የነበረው የምክር ቤቱ 18ኛ ጠቅላላ ጉባዔና የቦርድ አባላት ምርጫ በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ንግድና ኢንቨስትመንት ችሎት ታገደ።
የምክር ቤቱ የቦርድ አባል የሆኑት አቶ አበራ አበጋዝ እሸቴ ያቀረቡትን ክስ የተመለከተው የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ንግድና ኢንቨስትመንት ችሎት፣ ምክር ቤቱ የጠራው ጠቅላላ ጉባዔ ቢካሄድ በተጀመረው የዳኝነት ሒደት ላይ የፍትሕ መዛባትን ሊያስከትል እንደሚችል ከግንዛቤ በማስገባት፣ የተጠራው ጉባዔ ለጊዜው እንዳይካሄድ የዕግድ ትዕዛዝ ሰጥቷል።
ለዕግድ ውሳኔው ምክንያት የሆነውን ክስ ያቀረቡት የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የቦርድ አባል የሆኑት አቶ አበራ አበጋዝ እሸቴ ሲሆኑ፣ ክሱን ያቀረቡትም በአንደኛ ተጠሪ የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ እና በሁለተኛ ተጠሪ የምክር ቤት ፕሬዚዳንት ወ/ሮ መሰንበት ሸንቁጤ ላይ እንደሆነ የክስ መዝገቡ ያስረዳል።
በሁለቱ ተጠሪዎች ላይ የቀረበው የመጀመሪያው ክስ፣ የንግድ ምክር ቤቱ አመራሮች ታኅሳስ 8 ቀን 2017 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ጽሕፈት ቤት ውይይት ባደረጉበት ወቅት፣ የክሱ አመልካች አቶ አበራ አበጋዝ እሸቴ ሁለተኛ ተጠሪ የሆኑትን የምክር ቤቱን ፕሬዚዳንት ወ/ሮ መሰንበት ሸንቁጤን መብት የሚነካ ተግባር ፈጽሟል በማለት፣ ፕሬዚዳንቷ በአንደኛ ተጠሪ (በንግድ ምክር ቤቱ) ስም የክሱ አመልካች የሆኑትን አቶ አበራ አበጋዝ ከምክር ቤቱ የቦርድ አባልነት እንዲሁም ሊካሄድ በታቀደው የምክር ቤቱ 18ኛ ጠቅላላ ጉባዔና የቦርዶ አባላት ምርጫ ላይ እንዳይወዳደሩ ታኅሳስ 9 ቀን 2017 ዓ.ም. አግደዋል የሚል ነው።
የንግድ ም/ቤቱ አባል የሆነ ሰው በአባልነቱ ከሚያገኛቸው መሠረታዊ ከሚባሉት መብቶች አንዱ በጠቅላላ ጉባዔ የመገኘት፣ ድምፅ የመስጠት፣ በአስተዳደር አካላት ውስጥ በአባልነት የመመረጥ፣ የመምረጥ መብት እንዳለውና ይኸውም በምክር ቤቱ (የክሱ አንደኛ ተጠሪ) መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 9(2) ሥር በግልጽ የተደነገገ መሆኑን ከሳሽ ባቀረቡት ዝርዝር አቤቱታ አስረድተዋል።
የአመልካች የአባልነት መብት በምክር ቤቱ ደንብ አንቀጽ 11 ሥር በተዘረዘሩት ምክንያቶች እስካልተቋረጠ ድረስ ሊገደብ እንደማይችል የሚደነግግ ቢሆንም፣ ሁለተኛ ተጠሪ የሆኑት ወ/ሮ መሰንበት ሸንቁጤ፣ አንደኛ ተጠሪ የሆነውን የንግድ ምክር ቤቱን ስም በመጠቀም የአመልካች የአባልነት መብት እንዲነፈግ ውሳኔ ያሳለፉት ‹‹ከእኔ ጋር ግጭት ፈጥሯል›› በሚል ግላዊ ምክንያት መሆኑን ያስረዳል።
አመልካች በወቅቱ የተናገሩት ለተቋሙ የሚጠቅምና አባላቱ የሰጡንን ኃላፊነት የመወጣት ተግባር ሆኖ ሳለ፣ ሁለተኛ ተጠሪ ሥልጣናቸውንና የግል ምክንያታቸውን መሠረት በማድረግ፣ የአመልካችን በቦርድ አባልነት የመወዳደር መብት የሚያሳጣ ወይም የሚገድብ ውሳኔ ማሳለፋቸው፣ አዋጁንና መተዳደሪያ ደንቡን የሚጥስ ከሕግ ውጪ ተግባር በመሆኑ ውሳኔው እንዲሻርላቸው ጠይቀዋል።
አመልካች በክሳቸው ያቀረቡት ሌላው አቤቱታ፣ ሁለቱ ተጠሪዎች ለትናንት ጥር 3 ቀን 2017 ዓ.ም. የጠሩት የንግድ ምክር ቤቱ 18ኛ ጠቅላላ ጉባዔ ሕግንና የምክር ቤቱን መተዳደሪያ ደንብ የሚጥስ በመሆኑ፣ የተጠራው 18ኛ ጠቅላላ ጉባዔ ሊደረግ አይገባም ተብሎ እንዲወሰንላቸው የሚጠይቅ ነው።
አመልካች በአቤቱታቸው፣ ሁለቱ ተጠሪዎች በምክር ቤቱ ደንቦችና አግባብነት ባላቸው ሕጎች የተከለከለ ሕገወጥ ውሳኔ በመስጠት፣ 18ኛው ጠቅላላ ጉባዔ እንዲጠራና በዚህ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ከሕግና ከመተዳደሪያ ደንቡ ውጪ የምክር ቤቱ አባል ያልሆኑ ነጋዴዎች በጉባዔው ላይ እንዲሳተፉ መወሰናቸውን ዘርዝረዋል።
በመሆኑም ፍርድ ቤቱ የተጠራው ጉባዔ ሊካሄድ አይገባም በማለት እንዲወሰንላቸው ጠይቀዋል።
አክለውም፣ ሁለቱ ተጠሪዎች በንግድ ምክር ቤቱ የተሰጣቸውን ኃላፊነት ለሌላ አካል በማስተላለፍ፣ የምርጫ ማጣራትም ሆነ ምርጫ የሚያደርግ እንዲሁም ሊካሄድ በታቀደው የጠቅላላ ጉባዔ ላይ የአባላት ምዝገባ የሚያደርግ ሌላ አካል እንዲቋቋም አድርገው ከሆነም፣ ይህ አካል ሕገወጥና በመተዳደሪያ ደንቡ ላይ የተመለከተውን የጣሰ በመሆኑ እንዲፈርስና እንዲከለከል የፍርድ ቤቱን ዳኝነት ጠይቀዋል።
የቀረበውን ክስ የተመለከተው የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ንግድና ኢንቨስትመነት ምድብ ችሎት ታኅሳስ 30 ቀን 2017 ዓ.ም. የተለያዩ ትዕዛዞችን ሰጥቷል።
ፍርድ ቤቱ በቀዳሚነት የሰጠው ትዕዛዝም፣ የፍትሐብሔር ክርክሮችን በመደበኛ ፍርድ ቤት መመልከት ከሚወሰደው የጊዜ ርዝመት፣ ከሚያስከትለው የገንዘብና የጉልበት ወጪ እንዲሁም በተከራካሪ ወገኖች ዘላቂ ግንኙነት ላይ ከሚያስከትለው አሉታዊ ተፅዕኖ አኳያ አለመግባባቶችን (ክሶችን) በስምምነት መቋጨት ተቀዳሚነት የሚሰጠው ጉዳይ በመሆኑና ይኸውም በአዋጅ ቁጥር 1234/2013 አንቀፅ 45፣ በፍትሐ ብሔር ሕግና በሥነ ሥርዓት ሕጉም ጭምር ተቀባይነት ያለው መሆኑን ጠቅሶ፣ የተከራካሪ ወገኖች ጉዳይ በችሎት ከመታየቱ በፊት በአስማሚ አካል አጋዝነት በስምምነት እንዲፈቱ የሚል ነው።
በዚሁ መሠረትም የቀረበውን ክስ በፍርድ ቤቱ አስማሚ ቢሮ (ማዕከል) ለማየት ተጠሪዎች ለጥር 14 ቀን 2017 ዓ.ም. እንዲቀርቡ ፍርድ ቤቱ ቀጠሮ ሰጥል። አክሎም፣ ጉዳዩ በስምምነት የሚያልቅ ከሆነ የስምምነት ሰነድ ለመቀበል፣ ጉዳዩ በስምምነት ያላለቀ ከሆነ ደግሞ ክሱን በመደበኛው ችሎት ለመስማት ለጥር 23 ቀን 2017 ዓ.ም. ሌላ ቀጠሮ ሰጥቷል።
በሌላ በኩል፣ ፍርድ ቤቱ በከሳሽ በኩል የቀረበውን የዕግድ አቤቱታ ተመልክቶ ተጨማሪ ተዕዛዞችን ሰጥቷል።
ፍርድ ቤቱ፣ ‹‹የዕግድ አቤቱታውን ከተጠየቀው ዳኝነት አንፃር በመርመር ተጠሪዎች አስተያየት ሰጥተው ተለዋጭ ቀጠሮ እስኪሰጥበት ድረስ ለጊዜው ዕግድ መሰጠት ያለበት ሆኖ ተገኝቷል፤›› በማለት ተዕዛዞችን ሰጥቷል።
በዚህም መሠረት አመልካች ያቀረቡት የዕግድ አቤቱታ ለተጠሪዎች እንዲደርስና ተጠሪዎች በአጭር ቀጠሮ አስተያየታቸውን በጽሑፍ እንዲያቀርቡ አዟል። ተጠሪዎች በዕግድ አቤቱታው ላይ በጽሑፍ የሚያቀርቡትን አስተያየት ለመቀበልም ፍርድ ቤቱ ለጥር 2 ቀን 2017 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቶ ነበር።
ፍርድ ቤቱ አክሎም፣ ‹‹ተጠሪዎች በቀረበው የዕግድ አቤቱታ ላይ አስተያየታቸውን በጽሑፍ እንዲያቀርቡ የተሰጠው ትዕዛዝ ተፈጽሞና ፍርድ ቤቱ የተከሳሾችን አስተያየት ተመልክቶ ተገቢውን ትዕዛዝ እስኪሰጥ ድረስ፣ አንደኛ ተጠሪ የሆነው የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ሊያደርገው ያሰበው 18ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔና የቦርድ አመራሮች ምርጫ ለጊዜው ታግዶ እንዲቆይ፤›› በማለት ተዕዛዝ ሰጥቷል፡፡