ስድስት ኪሎ ዩኒቨርሲቲ አካባቢ

ማኅበራዊ ለከተራና ጥምቀት በዓላት ትኩረት የሚሹት ለኮሪደር ልማት የተቆፋፈሩ መንገዶች

አበበ ፍቅር

ቀን: January 15, 2025

የዘንድሮ የጥምቀት በዓል በተለይ በአዲስ አበባ ለየት ባለ ጥበቃ የሚከበር ስለመሆኑ የአዲስ አበባ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ አስታውቋል፡፡ የደንብ ማስከበር ባለሥልጣንና ሌሎች አካላትም በዓሉ በሰላም ተጀምሮ እንዲጠናቀቅ ቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን ገልጸዋል፡፡

የፀጥታ ሁኔታውን ለመቆጣጠር በዘመናዊ ቴክኖሎጂና በድሮን የተደገፈ ጥበቃ የሚደረግ መሆኑ የዘንድሮውን የበዓል አከባበር ለየት ያደርገዋል፡፡ ወጣቶችና የፀጥታ አካላት በድሮን ታግዘው በዓሉ በሰላም እንዲከበር እየሠሩ መሆኑን ቢሮው አስታውቋል፡፡

በሌላ በኩል የዘንድሮው የጥምቀት በዓል የሚከበረው በመዲናዋ በተለያዩ አካባቢዎች በኮሪደር ልማት ምክንያት በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ለዓመታት ጥምቀቱንና ሌሎች በዓላትን ካከበሩበት ደብር ርቀው በሄዱበት ቢሆንም፣ በመሠራት ላይ ያሉ የኮሪደር ልማቶች ያልተጠናቀቁ መሆናቸው ከሚኖረው ከፍተኛ የሕዝብ ፍሰት አንፃር ከወዲሁ ካልተስተካከሉ የምዕመኑ እንቅስቃሴ ላይ ሥጋትና አደጋዎች የሚያስከትሉ ይሆናሉ፡፡

በዓሉ በርካታ ሰዎች አደባባይ ወጥተው የሚያከብሩት በመሆኑ፣ መንገዶች ሥርዓተ ጥምቀቱ የሚደረግባቸው ቦታዎች ከወዲሁ ዝግጁ ካልሆኑ በበዓሉ ወቅት ችግር መፍጠራቸው አይቀሬ ነው፡፡

ከአሥራ ሦስት ታቦታት በላይ ተሰባስበው የሚከትሙበትና እጅግ በርካታ ምዕመናን የሚገኙበት የጃንዳሜ ባህረ ጥምቀት ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነው የቅድመ ዝግጅት ሥራ መጠናቀቁን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሊቀ ትጉሃን እስክንድር ገብረክርስቶስ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ታቦተ ሕጉን ለማክበር የሚወጡ ምዕመናን በኮሪደር ልማቱ በተቆፋፈሩና በተዘጋጉ መንገዶች እንዳይቸገሩ ከከተማ አስተዳደሩ ጋር ምክክር እንደሚያደርጉ የተናገሩት ሊቀ ትጉሃን እስክንድር፣ በዚህም የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት የወዳደቁ ብረቶችን እንደሚያስተካክሉና ያልተዘጉ ትቦዎችን እንደሚደፍኑ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡

ለዚህም ቤተ ክርስቲያኗ ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በሚደረግ ውይይት ‹‹መንገዶች እንዲስተካከሉ›› የሚል እንደምታነሳ ተናግረዋል፡፡

በዓሉ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የተመዘገበ በመሆኑ፣ መንግሥትና ሕዝብ በጋራ ባህላዊና ሃይማኖዊ ይዘቱን በጠበቀና ባማረ ሁኔታ እንዲከበር ርብርብ ሊያደርጉ ይገባል፡፡

በኮሪደር ልማቱ ለዕድሳት የፈረሱ መንገዶች በበዓል ወቅት ኅበረተሰቡ ላይ ጉዳት ሊፈጥሩ የሚችሉ ሥጋቶችን ለመመልከት ሪፖርተር ከአራት ኪሎ ወደ ሽሮ ሜዳ የሚሠራውን መንገድ ለመመልከት ሞክሯል፡፡

በዚህም በርካታ ምዕመን ታቦታቱን በማጀብ የሚያልፉባቸው ከአራት ኪሎ፣ አምስት ኪሎና ስድስት ኪሎ ወደ ሽሮ ሜዳ የሚወስዱ መንገዶች ገና በመሠራት ላይ ያሉና በተለይ ግራና ቀኙ የተቆፈረ በመሆኑ ለመተላለፍ እንደሚያስችግር መመልከት ተችሏል፡፡

መንገዱ ታቦታት ከተለያዩ አቅጣጫዎች በመነሳት ወደ ጃንሜዳ የሚያልፉበት በመሆኑ የበለጠ ጥንቃቄ የሚያስፈልገውም ነው፡፡

የመንገዱ ክፍሎች እየተሠሩ ቢሆንም፣ የወዳደቁና ሰው ቢወድቅባቸው ለከባድ አደጋ የሚያጋልጡ የቆሙ ብረቶች፣ በመንገዱ ግራና ቀኝ ለግንባታ የተደፉ የአሸዋና የአፈር ቁልሎች መንገዱን ዘግተውታል፡፡

ሪፖርተር ባደረገው ምልከታ፣ ሌሎች አካባቢዎችም ለአብነት ከ22 ጎላጉል በድንበሯ እንግሊዝ ኤምባሲ የሚወጣው መንገድ መሰል ችግሮች ስላሉባቸው ሊያጋጥሙ የሚችሉ ጉዳቶችን ለመግታት ከወዲሁ ጥንቃቄ የሚያስፈልገው መሆኑን ታዝቧል፡፡

ለውኃ መውረጃ የተቆፈሩ ትልልቅ ጉድጓዶችና ሌሎችም መንገዱን የዘጉት ሲሆን፣ ምናልባት እነዚህ መንገዶች በምዕመን ላይ ጉዳት እንዲያደርሱ ለበዓሉ የታሰበላቸው ጊዜያዊ መፍትሔ ካለ በሚል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊና ከአራት ኪሎ፣ ሽሮ ሜዳ፣ እንጦጦ፣ ጉለሌ፣ የዕፅዋት ማዕከል ያለውን የኮሪደር ልማት አስተባባሪ ጀማሉ ጀንበር (ዶ/ር) ለማነጋገር ቢሯቸው ድረስ ብንሄድም ሌላ ሥራ መያዛቸው በጸሐፊያቸው በኩል ስለተነገረን ማግኘት አልተቻለም፡፡

የጥምቀት በዓልን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለማክበር ቤተ ክርስቲያኗ ከ21 በላይ ንዑሳን ኮሚቴዎችን በማቋቋም ወደ ሥራ መግባታቸውን የተናገሩት ሊቀ ትጉሃን እስክንድር፣ ኮሚቴው በጃንሜዳ ባደረገው ግምገማ በዓሉን ለማክበር ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ከወዲሁ መመልከት ተችሏል ብለዋል፡፡

የዘንድሮው ተረኛ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም መሆኗን ጠቅሰው፣ በበዓሉ ወቅት የሚቀርቡ ዝማሬዎችና መንፈሳዊ ዝግቶች፣ አልባሳትና የአሠላለፍ ሥርዓቶች ምን መሆን እንዳለበት መገምገማቸውን ተናግረዋል፡፡

የጃንሜዳ ባህረ ጥምቀት ከ21 በላይ የፀበል መርጫዎች እንዳሉት የተናገሩት ዋና ኃላፊው፣ ባህረ ጥምቀቱ የሚከወንበት ቦታ ከሳምንት በፊት የፅዳትና ውበት ኮሚቴ ተቋቁሞለት ገንዳውንና አካባቢውን የማፅዳት ሥራ መሠራቱን አክለዋል፡፡

የመብራትና ሌሎች ቀሪ ሥራዎችም ከከተራ በፊት እንደሚጠናቀቁና በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ 72 የበዓለ ጥምቀት ማክበሪያ ቦታዎች እንዳሉም ነግረውናል፡፡