ማኅበራዊ ኢትዮጵያዊቷ ተማሪ የ2025 የሁዋዌ ዓለም አቀፍ አምባሳደር ሆና ተመረጠች

ምሕረት ሞገስ

ቀን: January 15, 2025

የሥላሴ ዩኒቨርሲቲ አራተኛ ዓመት የኮምፒዩተር ሳይንስ ተማሪ አሲያ ከሊፋ የሁዋዌ የ2025 የሲድስ ፎር ዘ ፊውቸር ዓለም አቀፍ አምባሳደሮች አንዷ ሆና ተመረጠች፡፡

ኢትዮጵያዊቷ ተማሪ የ2025 የሁዋዌ ዓለም አቀፍ አምባሳደር ሆና ተመረጠች | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
ተማሪ አሲያ ከሊፋ

ሁዋዌ ከመረጣቸው 12 አምባሳደሮች መካከል ኢትዮጵያን በመወከል አንዷ የሆነችው አሲያ ለሪፖርተር እንደገለጸችው፣ በሲድስ ፎር ዘፊውቸር ፕሮጀክት በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚያዘጋጃቸው መድረኮች በመሳተፍ በኢትዮጵያ በቴክኖሎጂው ዘርፍ ያሉ ተማሪዎችን የምትወክል ይሆናል፡፡

ሲድስ ፎር ዘ ፊውቸር ፕሮግራም ለኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ይዞ የመጣውን ዕድል ማስተዋወቅ፣ የፕሮግራሙ ተሳታፊ እንዲሆኑ መቀስቀስና ማገዝም የአምባሳደርነት ሥራዋ አካል እንደሚሆን ተናግራለች፡፡

ማኅበራዊ ሚዲያዎችንና ሁዋዌ የሚያዘጋጃቸውን የተግባቦት መድረኮች በመጠቀም ዓለም አቀፍ የሆኑ የፕሮጀክት ፕሮግራሞችን ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ማስተዋወቅና ተማሪዎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስቻልም የሥራዋ አካል መሆኑን አክላለች፡፡

ከተለያዩ አገሮች ከተመረጡት የሁዋዌ ሲድስ ፎር ዘ ፊውቸር አምባሳደሮች ጋር በበይነመረብና በአካል አብሮ ለመሥራት የሚያስችል ዕድል መፈጠሩን፣ ከዚህም ልምድ በመቅሰም ለኢትዮጵያውያን ተማሪዎች የምታካፍል መሆኑንም ገልጻለች፡፡

የሲድስ ፎር ዘ ፊውቸር ዓላማ በዓለም ዙሪያ ያሉ ወጣት ተማሪዎች በአጭር ጊዜ ሥልጠና የዲጂታል ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን አረዳዳቸውን ማሳደግ ነው። ለዚህም አጫጭር ሥልጠናዎችን ይሰጣል፣ ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ያዘጋጃል የተመራቂዎች ማኅበር እንቅስቃሴዎች (አልሙናይ) ተሳትፎ እንዲጎለብት ይሠራል።

የባህል ልውውጦች አስፈላጊነትና የሥራ ፈጣሪነት መንፈስ ማዳበር ላይም ትኩረት ያደረገ ሲሆን፣ ከተሳታፊዎች መካከልም ከአንድ ሦስተኛ በላይ የሚሆኑትን ሴቶች ማድረግ በአሳታፊነት የሚሠራ መሆኑን ሁዋዌ ለሪፖርተር በላከው መግለጫ አስታውቋል።

እንደ ሁዋዌ፣ አሲያ ዓለም አቀፍ አምባሳደር ሆና ለመመረጧ በሁዋዌ ሲድስ ዘ ፊውቸር 2024 ፕሮግራም፣ ስኬታማ ተሳትፎ ማድረጓ አስተዋጽኦ ያደረገ ሲሆን፣ ይኸውም እ.ኤ.አ. በ2025 በቻይና ውስጥ በሚካሄደው የአይሲቲ ታለንት ዲጂታል ጉብኝት በአካል እንድትሳተፍና የተግባር ልምድ እንድታገኝ እንዲሁም በሌሎች ትልልቅ ዓለም አቀፍ ዝግጅቶች ላይ ተገኝታ የቴክኖሎጂ ተግባራዊ ዕውቀት እንድትካፈል ዕድል የሚሰጣት ይሆናል።

የዓለም አቀፍ አምባሳደር ፕሮግራም የተቀረፀው የሲድስ ፎር ዘ ፊውቸር እ.ኤ.አ. ከ2008 ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ ያሉትን የፕሮግራሙን ተሳታፊዎች ግንኙነት ለማጠናከር ነው።

የፕሮግራሙን ዓለም አቀፍ ተደራሽነት ለማስፋትና የተሳታፊዎችን የመማማር የትስስር ዕድሎችን ለመፍጠር ያተኮረው ፕሮግራሙ፣ ወጣቶች፣ የፕሮግራሙ ዋና እሴቶች የሆኑትን ዲጂታላይዜሽን፣ ፈጠራ፣ ሥራ ፈጠራና ዘላቂነትን እንዲላበሱ የሚሠራ ነው።

አስያ የዓለም አቀፍ አምባሳደር ሆና መመረጧ፣ በፕሮግራሙ ውስጥ ለኢትዮጵያውያን ተማሪዎች መሰል ተሳትፎ ትልቅ ምዕራፍ እንደሚሆንና በማኅበረሰቧና ከዚያም በላይ ዲጂታል ቴክኖሎጂንና ፈጠራን ለማሳደግ ያላትን ቁርጠኝነት እንደሚያሳይ ሁዋዌ ገልጿል።