
January 15, 2025
አሚጎስ የብድርና ቁጠባ ኅብረት ሥራ ማኅበር ከተመሠረተ አሥራ ሁለት ዓመታት ሆኖታል፡፡ በእነዚህ ዓመታት 8,500 አባላትን ማፍራት ችሏል፡፡ አሚጎስ ስለተመሠረተበት ዓላማ፣ እያከናወናቸው ስለሚገኙ ተግባራት፣ የብድርና ቁጠባ ማኅበራት በአገሪቱ እየተጫወቱ ስላለው ሚናና ዘርፉ እያጋጠመው ስላለው ተግዳሮት፣ የአሚጎስ ብድርና ቁጠባ ኅብረት ሥራ ማኅበር መሥራችና ሥራ አስኪያጅ የሆኑትን አቶ ፍፁም አብርሃን የማነ ብርሃኑ አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- አሚጎስ መቼ ተመሠረተ? ለመመሥረቱስ ምክንያቱ ምንድነው?
አቶ ፍፁም፡- አሚጎስ የተመሠረተው በዘጠኝ ሺሕ ብር ካፒታል ጥር 1 ቀን 2005 ዓ.ም. ነው፡፡ ለመመሥረቱም ዋና ምክንያት በትምህርት ያገኘነውን ዕውቀትና የሌሎች አገሮችን ተሞክሮ በመቀመር፣ በሥራ ፈጠራና በሌሎች መስኮች ብዙኃኑን ተደራሽ ለማድረግ ትልቅ ዓላማን በመሰነቅ ነው፡፡ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሆነን በምንተዋወቅ ሦስት ጓደኛማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበሩ የተመሠረተ ቢሆንም፣ ሕጋዊ ለማድረግ የመሥራች አባላቱን ቁጥር ወደ ሃያ ከፍ ማድረግ በማስፈለጉ ይህንን ተከትለን ማኅበሩን ማቋቋም ችለናል፡፡ ሪፖርተር፡- አሚጎስ አሁን ላይ የካፒታል መጠኑስ ምን ያህል ነው?
አቶ ፍፁም፡- ማኅበሩ በአሁኑ ወቅት ከ8,500 በላይ አባላትና ወደ ሦስት ቢሊዮን ብር የሚገመት ሀብት አለው፡፡ አንድ ቢሊዮን ብር የተከፈለ አክሲዮን ያለው ሲሆን፣ እስካሁን 4,500 ለሚሆኑ አባላት ከአምስት ቢሊዮን ብር በላይ ብድር አቅርቧል፡፡
ሪፖርተር፡- ማኅበሩ ለአባላቱ በማቅረብ ላይ የሚገኘው የብድር አገልግሎት የትኞቹ ዘርፎች ላይ ያተኮሩ ናቸው?
አቶ ፍፁም፡- ማኅበሩ ስልሳና ሰባ በመቶ የሚሆነውን የብድር አቅርቦት እየሰጠ የሚገኘው ለመኪና ግዥ ነው፡፡ አባላቱ የዚህ ዕድል ተጠቃሚ ለመሆን ቅድሚያ 30 በመቶ መቆጠብ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በዚህ መነሻነትም ብድሩ የሚመቻች ይሆናል፡፡ መኪናዎችንም እንደ በላይ አብ፣ ኢትዮፒክ ካርና ከመሳሰሉት ኩባንያዎች ጋር ውል በመግባት ለአባላት እናቀርባለን፡፡ መኪናዎቹም በአብዛኛው ለከተማው ማኅበረሰብ የታክሲ አገልግሎት የሚሰጡ ናቸው፡፡
ሪፖርተር፡- አሚጎስ ከብድር አገልግሎት ባሻገር ሌሎች የሚሠራቸው ሥራዎች ይኖሩት ይሆን?
አቶ ፍፁም፡- የማኅበሩ አባላት የሆኑ፣ ከትንሽ ደረጃ ተነስተው በሚሊዮን ብር ደረጃ የሚያንቀሳቅሱና ትልቅ ደረጃ ላይ የሚገኙ ግለሰቦች አሉ፡፡ ለእነዚህ አባላት ሥልጠና በመስጠት፣ መደገፍና አሁን ካሉበት የተሻለ ከፍታ ላይ እንዲደርሱ የምንሠራቸው ሥራዎች ይኖራሉ፡፡ በኢንዱስትሪ፣ በግብርናና በአገልግሎት ሰጪ ዘርፎች ላይ የተሰማሩ አባላትን ለማብቃት የሥልጠናና የማማከር ሥራ እንሠራለን፡፡
ሪፖርተር፡- ማኅበሩ በየትኞቹ አካባቢዎች ላይ ይሠራል? ምን ያህል ሠራተኞችስ አሉት?
አቶ ፍፁም፡- አሚጎስ በአዳማና በመቀሌ ከተሞች ቅርንጫፎቹን ከፍቶ እየሠራ ይገኛል፡፡ በአዲስ አበባም ሦስት ቅርንጫፎች አሉት፡፡ በቀጣይ አድማሱን በማስፋት በተለያዩ የኢትዮጵያ ክልሎች ተደራሽ ለመሆን በመሥራት ላይ ነው፡፡ አሁን ላይ ተቋሙ 120 ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድልን ፈጥሯል፡፡ በተጨማሪም አያት አካባቢ 625 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ ጂ+7 ሕንፃ ያለው ሪል ስቴት እየገነባ ነው፡፡ ይህም የማኅበሩ አባላት በረዥም ጊዜ ክፍያ የቤት ባለቤት እንዲሆኑ የሚያስችል ነው፡፡
ሪፖርተር፡- የኅብረት ሥራ ማኅበሩ አባል ለመሆን የሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎች ምንድናቸው?
አቶ ፍፁም፡- የመጀመሪያው መታወቂያ ነው፡፡ አንድ ሰው መታወቂያ ካለው ሁለት ሺሕ ብር ለመመዝገቢያ፣ የአክሲዮን 10 ሺሕ ብርና የቁጠባ 13 ሺሕ ብር፣ በአጠቃላይ 25 ሺሕ ብር በመክፈል አባል መሆን ይችላል፡፡ ከዚያ በኋላ በየወሩ እንደ ሰውዬው አቅም ከአንድ ሺሕ ብር ጀምሮ በመቆጠብ ኅብረት ሥራ ማኅበሩ የሚያቀርበውን የብድር አገልግሎት ተጠቃሚ መሆን የሚችል ይሆናል፡፡
ሪፖርተር፡- ማኅበሩ ለአባላቱ የሰጠው ብድር ሳይመለስ ቢቀር ብድሩን ለማስመለስ የሚጠቀመው መንገድ ምንድነው?
አቶ ፍፁም፡- አብዛኛውን ጊዜ ገንዘብ ስታበድር ገንዘቡ የት ላይ እንደሚውል ቀድመህ ታውቃለህ፡፡ ይህ ስለሆነም ገንዘቡ ይመለሳል አይመለስም የሚለው ብዙም አያሳስብህም፡፡ ብዙውን ጊዜ የምንሰጠው ብድር 70 በመቶ ያህሉ ትራንስፖርት ዘርፍ ላይ ነው፡፡ ከተማ ውስጥ የፈረስ፣ የራይድና በሌሎችም ማኅበር ለታቀፉና የታክሲ አገልግሎት ለሚሰጡ ግለሰቦች ብድር ስንሰጥ ቆይተናል፡፡ ለእነኚህ አባላትም አቅማቸውን ያገናዘበ ብድር የምንሰጥ በመሆኑ ለመክፈል አይቸገሩም፡፡ ተቋማችን ዓላማ ላላቸውና በሥራ ለመለወጥ ለሚፈልጉ ግለሰቦች የሚያበድር በመሆኑ ያጋጠመውና ይህ ነው ተብሎ ሊገለጽ የሚችል ችግር እስካሁን የለም፡፡
ሪፖርተር፡- አንዳንድ የብድርና የቁጠባ ማኅበራት ውጤታማ መሆን ባለመቻላቸው ብዙ ርቀት ሳይጓዙ ሲፈርሱ ይስተዋላል፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ምንድነው?
አቶ ፍፁም፡- ተቋማችን በአሥራ ሁለት ዓመታት የሥራ ቆይታው ስኬታማ ለመሆን ችሏል ብለን እናምናለን፡፡ ካፒታላችንንም ከዘጠኝ ሺሕ ወደ ሦስት ቢሊዮን ብር ለማሳደግ በቅተናል፡፡ ከትንሽ ነገር በመነሳት ከፍ ያለ ቦታ መድረስ አንድ የጤነኛ ቢዝነስ ባህሪ ነው፡፡ ከሦስት ሠራተኛ ወደ 120 ሠራተኛ ቀጥሮ ማሠራት መቻልም ስኬትን ያመላክታል፡፡ መንግሥት ለማኅበረሰቡ በተለይም ለወጣቱ ክፍል በማሰብ እነዚህ ተቋማት እንዲስፋፉና እንዲጠናከሩ ሰፊ ሜዳ አመቻችቷል፡፡ አሁን ላይ የብድርና የቁጠባ ተቋማት በቀላሉ ማኅበር በመመሥረትና ካፒታል በማዋጣት በቀላሉ ሊመሠረቱ የሚችሉ ናቸው፡፡ ሆኖም ግን በአሁኑ ወቅት በማኅበር ስም አንዳንድ ግለሰቦች ገንዘብ በመሰብሰብ ለግል ጥቅማቸው ሲያውሉ በሰፊው ይታያል፡፡ በዚህም ምክንያት አንዳንድ ግለሰቦች በደል እንደደረሰባቸው ሲናገሩ ይደመጣል፡፡ በመሆኑም እነኚህን መሰል ማኅበራት ከችግር እንዲወጡ ቅድሚያ ገና ከምሥረታቸው የጠራ ግብና ዓላማ ይዘው መነሳት ይኖርባቸዋል፡፡ በተጨማሪም ጠንካራ፣ ብቁና በዘርፉ ልምድ ባላቸው ሰዎች ሊመሩ ይገባል፡፡ ይህን ተከትለው የሚሠሩ ከሆነ ውጤታማ የማይሆኑበት ምክንያት የለም፡፡
ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ የብድርና ቁጠባ ተቋማት የት ደረጃ ላይ ይገኛሉ?
አቶ ፍፁም፡- በኢትዮጵያ የብድርና ቁጠባ ተቋማት በሚገባቸው ልክ እየተንቀሳቀሱ ነው ለማለት አያስደፍርም፡፡ አገራችን በዘርፉ ከአፍሪካ አገሮች በቀዳሚነት የምትጠቀስ ናት፡፡ በ1850ዎቹ በእነ እንግሊዝና ጀርመን የተጀመረው የኅብረት ሥራ ማኅበር በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን አገራችን ሊደርስ ችሏል፡፡ ሆኖም የዘርፉ ዕድገት አዝጋሚ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ዛሬ ከእኛ ልምድና ተሞክሮ የቀሰሙ እንደ ኬንያ ያሉ አገሮች በዘርፉ ስኬት እያስመዘገቡ ይገኛሉ፡፡ አሁን ላይ የኬንያን 50 በመቶ ኢኮኖሚ የሚሸፍኑ እነኚህ ተቋማት ሆነዋል፡፡ የእኛን አገር ተመሳሳይ ተቋማት ያየን እንደሆነ በኢኮኖሚው ላይ በአምስት በመቶ ድርሻ የላቸውም፡፡ በቁጥር ደረጃ ግን ከአፍሪካ አገሮች በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ፡፡ ከ20 ሺሕ በላይ የብድርና የቁጠባ ተቋማት በአገራችን እንደሚገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ሆኖም ግን የቁጥራቸውን ያህል ጠንካራ ሥራ ሲሠሩ አይታይም፡፡ በመሆኑም እነኚህ ማኅበራት በአገር ኢኮኖሚ ላይ ከፍ ያለ አስተዋጽኦ ማበርከት እንዲችሉ፣ ከአደረጃጀታቸው ጀምሮ ትኩረት፣ ክትትልና ድጋፍ ሊደረግላቸው ይገባል፡፡