ከ 5 ሰአት በፊት
የፓኪስታን ዓለም አቀፍ አየር መንገድ የፈረንሳዩን አይፍል ታወር ሊመታው በሚመስል መልኩ እየተጠጋው ያለ አውሮፕላን ተጠቅሞ ማስታወቂያ መሥራቱ ሰፊ ትችት አስነሳበት።
ማስታወቂያው አየር መንገዱ ወደ ፈረንሳይዋ ርዕሰ መዲና በድጋሚ በረራ መጀመሩን ለማሳወቅ ያለመ ሲሆን “ፓሪስ ዛሬ እየመጣን ነው” የሚል ጽሑፍም ተካቶበታል።
አንዳንድ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ማስታወቂያውን እእአ መስከረም 2001 በአሜሪካ ከደረሰው የሽብርተኞች ጥቃት ጋር እንደሚመሳሰል አስታውቀዋል።
“ይህ ማስታወቂያ ነው ማስጠንቀቂያ” ሲል አንድ ግለሰብ ኤክስ ላይ ጽፏል። ሌላኛው ደግሞ “የማርኬቲንግ ኃላፊውን አባሩት” ሲል ለአየር መንገዱ መልዕክት አስተላልፏል።
ምስሉ ባለፈው ሳምንት ኤክስ ላይ ከተለጠፈ በኋላ ከ21 ሚሊዮን ጊዜ በላይ የታየ ሲሆን ከፍተኛ ትችትም አስተናግዷል።
ጠቅላይ ሚንስትር ሼህበዝ ሻሪፍ በጉዳዩ ዙሪያ ምርመራ እንዲጀመር ትዕዛዝ አስተላልፈዋል። ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ኢሻቅ ዳር ማስታወቂያውን መተቸታቸውን ጂኦ ኒውስ የተባለ የፓኪስታን መገናኛ ብዙኃን ዘግቧል።
- የፋሲል ግንብ እድሳት እንዴት ተካሄደ? የመንጣቱ ምክንያት ምንድን ነው?ከ 6 ሰአት በፊት
- አሜሪካ በሱዳኑ ጦር መሪ አል ቡርሃን ላይ ከሰላማዊ ሰዎች ግድያ ጋር በተያያዘ ማዕቀብ ጣለችከ 5 ሰአት በፊት
- እስራኤል ታጋቾችን የማስለቀቅ ውል ላይ መስማማቷን የኔታንያሁ ቢሮ አስታወቀከ 5 ሰአት በፊት
በአውሮፓውያኑ 2001 ጠላፊዎች በኒው ዮርክ በሚገኙት የአለም የንግድ ማዕከል መንትያ ህንጻዎች እና በዋሽንግተን ዲሲ በሚገኘው ፔንታገን ላይ አውሮፕላኖች እንዲጋጩ በማድረግ ከሦስት ሺህ በላይ ሰዎች ህይወታቸው አልፏል።
የጥቃቱ አቀናባሪ ነው የተባለው ኻሊድ ሼክ ሞሐመድ እአአ በ2003 ፓኪስታን ውስጥ በቁጥጥር ስር ውሏል።
የአልቃይዳ መሪ የነበረው እና ጥቃቱን ያቀደው ኦሳማ ቢን ላደን እአአ በ2011 በአሜሪካ ወታደሮች ፓኪስታን ውስጥ ተገድሏል።
የአየር መንገዱ ማስታወቂያ “የእውነት እንዳስደነገጠው” ፓኪስታናዊው ጋዜጠኛ ኦማር ቁራይሺ ገልጿል።
“የአየር መንገዱ አስተዳደር ጉዳዩን በጥልቀት አላየውም?” ሲልም ጠይቋል።
“አውሮፕላን በመጠቀም ስለተፈጸመው የአሜሪካው ጥቃት አያውቁም? ይህም በተመሳሳይ መንገድ እንደሚተረጎም አጥተውት ነው?” ሲል ጥያቄዎቹን ኤክስ ላይ ጽፏል።
አየር መንገዱ በጉዳዩ ዙሪያ አስተያየት አልሰጠም።
የፓኪስታን አየር መንገድ ውዝግብ ውስጥ ሲገባ የመጀመሪያው አይደለም።
አንዳንድ የኤክስ ተጠቃሚዎች አየር መንገዱ በአውሮፓውያኑ 1979 መንገደኞች አውሮፕላን ጥላ በመንትያ ህንጻዎቹ ላይ አርፎ የሚታይበት ማስታወቂያ አሠርቶ እንደነበር አስታውቀዋል።
በአገሪቱ ታሪክ አሰቃቂ የሚባለው የአየር አደጋ እአአ በ2019 ከተከሰተ በኋላ አየር መንገዱ መጥፎ ዕድሉን ለማባረር በሚል አንድ ሠራተኛው ፍየል ሲያርድ በመታየቱ መሳለቂያ ለመሆን በቅቶ ነበር።
እአአ በ2019 ደግሞ የበረራ አስተናጋጆች ክብደት እንዲቀንሱ ካልሆነ በበረራ ሥራቸው እንደማይቀጥሉ መግለጹ ውዝግብ አስነስቶ ነበር። ሠራተኞቹ “ከመጠን ያለፈ ክብደታቸውን ለመቀነስ” ስድስት ወራት ተስጥቷቸው ነበር።