ከ 5 ሰአት በፊት
ታጋቾችን ለማስለቀቅ ከሐማስ ጋር ስምምነት ላይ መደረሱን የጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ ቢሮ አስታወቀ።
ኔታንያሁ ሐሙስ ዕለት ድምጽ እንደሚሰጥበት ሲጠበቅ የነበረውን የጋዛን የተኩስ አቁም ስምምነት ‘ሐማስ በመጨረሻ ሰዓት ሃሳቡን ለመለወጥ እየፈለገ ነው’ በማለት ስምምነቱን ለማፅደቅ የሚሰጠውን የምክር ቤት ድምፅ እንዲዘገይ አድርገው ነበር።
ሆኖም አርብ ጥዋት፣ ጥር 9/ 2017 ዓ.ም ተደራዳሪው ቡድን ስምምነት ላይ መደረሱን ለኔታንያሁ እንዳሳወቃቸው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ገልጿል።
ይህንንም ተከትሎ ኔታንያሁ የፖለቲካ እና የፀጥታ አባላት ያሉበት ምክር ቤት አርብ እንዲሰበሰቡ ትዕዛዝ የሰጡ ሲሆን በዚያም ስምምነቱ እንደሚያፀድቅ የኔታንያሁ ቢሮ አስታውቋል።
የታጋቾች ቤተሰቦችም ከሐማስ ጋር ስምምነት ላይ መደረሱ እንደተነገራቸው ቢሮው ጨምሮ ገልጿል።
በዶሃ የተገኙት የእስራኤል ፣ የሐማስ፣ የአሜሪካ እና የኳታር ተወካዮችም ስምምነቱ ላይ መፈረማቸውን የእስራኤል መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
- የተኩስ አቁም ስምምነት በተደረሰባት ጋዛ እስራኤል በፈጸመችው የአየር ጥቃት 73 ሰዎች ተገደሉ16 ጥር 2025
- የእስራኤል እና ፍልስጤማውያን ፍጥጫ እና ጦርነት መነሻ ምንድን ነው?ከ 6 ሰአት በፊት
- እስራኤል እና ሐማስ የጋዛን ጦርነት ለማቆም ከስምምነት ደረሱ16 ጥር 2025
የተኩስ አቁም ስምምነቱ በአሜሪካ እና በኳታር አሸማጋዮች መጀመሪያ ላይ የተገለጸው ረቡዕ ዕለት ነበር።
የኳታር ጠቅላይ ሚኒስትር ሼክ ኦሐመድ ቢን አብዱል ራህማን አል ታኒም ስምምነቱ ከመጪው እሁድ ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚሆን ተናግረዋል።
በወቅቱም ኔታንያሁ የስምምነቱ የመጨረሻ ዝርዝር እየተሰራበት እንደሆነ ገልጸው የነበረ ሲሆን፣ነገር ግን ሐማስ የስምምነቱን አንዳንድ ክፍሎች “እንደሻረ” በመግለጽ “የመጨረሻ ደቂቃ ቀውስ” እንዲፈጠር አድርጓል ሲሉ ስምምነቱን ለማጽደቅ የሚሰጠውን የካቢኔ ድምፅ እንዲዘገይ አድርገዋል።
ሐማስ ስምምነቱን ሙሉ በሙሉ እስካልተቀበለ ድረስም ካቢኔው እንደማይሰበሰብም ጽህፈት ቤታቸው ገልጾ ነበር።
ሐማስ በበኩሉ ለስምምነቱ ቁርጠኛ መሆኑን የገለጸ ሲሆን በስምምነቱ መሠረት በእስራኤል የሚፈቱ ፍልስጤማውያን ዝርዝር ውስጥ የተወሰኑ አባላቱን ማካተቱን ቢቢሲ ተረድቷል።
ምንም እንኳን የእስራኤል ተደራዳሪዎች ለወራት ሲካሄድ በነበረው ስምምነት ቢስማሙም በእስራኤል ምክር ቤት ካልጸደቀ ተግባራዊ ሊሆን አይችልም።