ከ 1 ሰአት በፊት
ሃያ ኪሎሜትር የሚሸፍን የባሕር ጠረፍ ለመስጠት እና በምላሹም ዕውቅና ለማግኘት ከኢትዮጵያ ጋር የመግባቢያ ስምምነት ፈርማ የነበረችው ራሷን እንደ ነጻ አገር ያወጀችው ሶማሊላንድ ዓይኗን ወደ አሜሪካ እያማተረች ነው።
በርካታ ሶማሊላንዳውያን ተመራጩ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለባለፉት 33 ዓመታት ሶማሊላንድ ስትናፍቀው የነበረውን በዓለም አቀፍ ደረጃ እንደ አገር ዕውቅና የማግኘት ህልሟን እውን ያደርጉታል በሚል ተስፋን ሰንቀዋል።
ሶማሊላንድ ከኢትዮጵያ ጋር በተደረሰው የባሕር በር መግባቢያ ስምምነት ለመጀመሪያ ጊዜ ዕውቅና አገኛለሁ የሚል ተስፋ ነበራት። ሆኖም በዚህ የመግባባቢያ ስምምነት ቁርሾ ውስጥ የገቡት ኢትዮጵያና ሶማሊያ በቅርቡ ልዩነታቸውን ለመፍታት በአንካራ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ተከትሎ የመግባቢያ ስምምነቱ ጥያቄ ውስጥ ገብቷል።
ከሶማሊያ ባለሥልጣናት በኩል ይህ የመግባቢያ ስምምነት እንደተሻረ ቢናገሩም ኢትዮጵያ በይፋ ያለችው ነገር የለም።
በቅርቡ በተደረገ ምርጫ አስተዳደሩን የተረከቡት የሶማሊላንድ ባለሥልጣናት በበኩላቸው ስምምነቱን እንደገና እናጤነዋለን ብለዋል። በዚህም መካከል ነው ከቀናት በኋላ የፕሬዚዳንት ሥልጣን የሚረከቡት ዶናልድ ትራምፕ ለሶማሊላንድ የመጀመሪያውን ዕውቅና ይሰጣሉ የሚሉ ወሬዎች እየተነገሩ ያሉት።
“ዶናልድ አዳኛችን ነው። ብልህ እና የተግባር ሰው ነው። አምላክ አሜሪካን ይባርክ” ስትል የዩኒቨርስቲ ተማሪ የሆነችው አይሻ ኢስማኤል ዕውቅና እናገኛለን በሚል ተስፋ ድምጿ በደስታ ተሞልቶ ለቢቢሲ ተናግራለች።
በሶማሊላንድ መዲና ሐርጌሳ ነዋሪ ለሆነችው አይሻ ይህ ዕውቅና የማግኘት ተስፋ ደስታን የሚያመጣ ቢሆንም በተቃራኒው ለሞቃዲሾ ተቀባይነት የሌለው ጉዳይ ነው።
ሶማሊያ፣ ራሷን በነጻ አገር ለባለፉት ሦስት አስርት ዓመታት የመራችውን ሶማሊላንድን አንድ የግዛቷ አካል አድርጋ ነው የምትቆጥራት።
“ዶናልድ ትራምፕ ሶማሊላንድ የት እንዳለች ማወቅ ቀርቶ ምን እንደሆነች ያውቃል የሚለውን እጠራጠራለሁ” በማለት ነበር በንዴት ድምጹ መንቀጥቀጥ የጀመረው በሞቃዲሾ የሚገኝ የመረጃ ተንታኝ አብዲ መሐመድ ለቢቢሲ የተናገረው።
አክሎም “ተቃጥያለሁ” አለ።
አብዲን ያናደደው የሶማሊላንዳውያን ተስፋ ሳይሆን ኃያላን እና ተደማጭነት ያላቸው ሪፐብሊካኖች የሶማሊላንድን ዕውቅና የማግኘት ፍላጎት በአሜሪካ ፖለቲካ ውስጥ አጀንዳ ማድረጋቸው ነው።
ባለፈው ወር የአሜሪካ የምክር ቤት አባል ስኮት ፔሪ አሜሪካ ለሶማሊላንድ መደበኛ እውቅና እንድትሰጥ ረቂቅ ሕግ አቅርበዋል። ይህ ረቂቅ በአውሮፓውያኑ ሚያዝያ 2023 ሁለተኛውን የትራምፕ የፕሬዚዳንትነት የሥልጣን ዘመንን በማስመልከት የወጣውን ፍኖተ ካርታ የተከተለ ነው።
‘ፕሮጀክት 2025’ የሚል ስያሜ የተሰጠው ይህ ፍኖተ ካርታ በቀኝ አክራሪው ሄሪቴጅ ፋውንዴሽን በተሰኘው እና ከ100 በላይ ወግ አጥባቂ ድርጅቶች የተነደፈ ነው።
ሰነዱ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት ውስጥ ሁለት አገራትን ብቻ ይጠቅሳል፣ ሶማሊላንድ እና ጂቡቲን። “አሜሪካ በጂቡቲ ያላትን ተጽእኖ ማሽቆልቆል ለመቋቋም ሶማሊላንድን እንደ አገርነት ዕውቅና መስጠት” የሚል ነው።
በዚህ ከ900 በላይ ገጾች ባሉት ሰነድ ከሰሃራ በታችን የተመለከተው ክፍል ከሁለት ገጾች በታች መሆኑ አህጉሪቱ የሚሰጣት ቦታ በጣም ዝቅተኛ እንደሆነ የሚያሳይ ነው ተብሏል። ሆኖም መጪው አስተዳደር ይህንን ፍኖተ ካርታ ይጠቀመዋል ለሚለው ምንም ዋስትና የሌለው ሲሆን አንዳንዶቹን ሃሳቦች ትራምፕ ቀደም ብለው ውድቅ ማድረጋቸው ተገልጿል።
- “ዕውቅና ለማግኘት ሲባል ወደ ሲኦል አናመራም” የሶማሊላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር6 ጥር 2025
- እንደ አገር ዕውቅና ማግኘትን አጀንዳቸው ያደረጉት ዕጩዎች የሚፎካከሩበት የሶማሊላንድ ምርጫ13 ህዳር 2024
- ኢትዮጵያና ሶማሊያ በአዲሱ የሰላም አስከባሪ ተልዕኮ ላይ በትብብር ለመስራት ተስማሙ3 ጥር 2025
ሆኖም አንድ ነገር ግልጽ ነው። አሜሪካ በሶማሊላንድ ላይ የያዘችውን አቋም መቀየር ጀምራለች። ከዚህ ቀደም በሞቃዲሾ ላይ ያተኮረ “አንድ ሶማሊያ” ፖሊሲን እየተወችው ለመሆኑ አመላካች ነው።
አሜሪካ ሽብርተኝነትን እዋጋለሁ በሚል በሶማሊያ በ1990ዎቹ የተለያዩ ጥቃቶችን በመፈጸም በርካቶች አልቀዋል።
በዚህም ወቅት የሶማሊያ ተዋጊዎች አንድ የአሜሪካ ሄሊኮፕተር መትተው በመጣል የ18 ወታደሮችን አስከሬኖችን በሞቃዲሾ ጎዳናዎች መጎተታቸው ይታወሳል።
ጦሯን በተለያዩ አገራት በማስገባት ለበርካቶች ሞት ምክንያት የሆነችው አሜሪካ “ብላክ ሃውክ ዳውን” በመባል በሚታወቀው በዚህ የሶማሊያ ፍልሚያ ከቬትናም ጦርነት ወዲህ አሜሪካ የደረሰባት የከፋ ሽንፈት ተብሏል።
“ሶማሊላንድን በነጻ አገርነት ዕውቅና የመስጠት እርምጃ የሶማሊያን ሉዓላዊነት የሚጻረር ብቻ ሳይሆን ቀጣናውን አለመረጋጋት ውስጥ የሚከት አደገኛ ሁኔታ ነው” ነው ሲሉ የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ አሊ መሐመድ ኦማር ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የአፍሪካ ኅብረት እና ሌሎች ዓለም አቀፍ ኃይሎች የግዛት አንድነትን ማስጠበቅ ቅድሚያ የሚሰጡት ጉዳይ ነው።
ለሶማሊላንድ ዕውቅና መስጠት በዓለም ዙሪያ ዕውቅና ለማግኘት የሚሹ ተገንጣዮችን ጉዳይ እንደገና የሚያነሳሳ እንደሚሆን ይጠቀሳል።
የአል ቃይዳ አጋር የሚባለውን አልሻባብን ሲዋጉ የነበሩ አብዛኞቹ የአሜሪካ ወታደሮች በትራምፕ የመጀመሪያ አስተዳደር ወቅት ከሶማሊያ የወጡ ሲሆን፣ በሁለተኛውም የሥልጣን ዘመን ይሄው ሊደገም እንደሚችል ስጋታቸውን ሚኒስትር ዲኤታው አጋርተዋል።
በተሰናባቹ ጆ ባይደን የፕሬዚዳንትነት ዘመን ወደ 500 የሚጠጉ የአሜሪካ ወታደሮች በሶማሊያ ሰፍረዋል። እነዚህ ወታደሮች ዳናብ (መብረቅ) የተባለውን የሶማሊያን ልዩ ጦር አሰልጥነዋል። ይህ ጦር ከመደበኛው የሶማሊያ ጦር በተሻለ አልሻባብን በመዋጋት ረገድ ውጤታማ ነው ተብሏል።
አሜሪካውያኑ ከሞቃዲሾ በስተሰሜን ምዕራብ በምትገኘው ባሌዶግሌ የጦር ሰፈር ያላቸው ሲሆን፣ የአልሻባብ ይዞታ ናቸው በሚሏቸው ስፍራዎች ላይ ተከታታይ የአየር ጥቃቶችን ይፈጽማሉ። “የወታደሮቹ መውጣት ከፍተኛ የሆነ የፀጥታ ክፍተት ይፈጥራል። አሸባሪ ቡድኖችን በማበረታት የሶማሊያን ብቻ ሳይሆን ሰፊውን የአፍሪካ ቀንድ መረጋጋት አደጋ ላይ የሚጥል ነው” ይላሉ።
ሚኒስትሩ ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ የገቡትን የባሕር በር ስምምነትን አስመልክቶ በሚናገሩበት ድምጸት ቢሆንም የዚያን ጊዜ በቁጣ ተሞልተው ነበር።
ኢትዮጵያ በዚህ ስፍራ የባሕር ኃይል ሰፈር እንደምታቋቁም እና በምትኩም ለሶማሊላንድ ዕውቅና ትሰጣለች መባሉን ተከትሎ እንደ ግዛቷ አካል የምታያት ሶማሊያ ጉዳዩን ወደ መንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት መውሰዷ ይታወሳል። በምላሹም ኢትዮጵያ ለሶማሊላንድ ዕውቅና ለመስጠት እንዲሁም ከልማት ተቋማቷ ድርሻ ይኖራታል የሚል ነው።
ሶማሊያ እና ኢትዮጵያ የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ያቋረጠ ቁርሾ ውስጥ ከገቡ በኋላ በቱርክ አደራዳሪነት ስምምነት ላይ ደርሰዋል።
አሁን ሶማሊያ ከትራምፕ አስተዳደር ጋር ያለው ግንኙነት ስላሳሰባት አንድ ወትዋች (ሎቢ) ቡድን ቀጥራለች። ሶማሊያ በዋሺንግተን መቀመጫውን ላደረገው ቢጂአር ለተሰኘው የሎቢ ድርጅት 600 ሺህ ዶላር ለመክፈል ተስማምታለች።
ባለፈው ወር የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት አዲሱ የአፍሪካ ኅብረት የሶማሊያ ድጋፍ እና ማረጋጋት ተልዕኮ (ኤዩሶም) የአፍሪካ ኅብረት የሶማሊያ የሽግግር ተልዕኮን (አትሚስ) እንዲተካ ድምጽ በተሰጠበት ወቅት አሜሪካ ድምጸ ተአቅቦ አድርጋለች።
በሪፐብሊካን ፓርቲ የአፍሪካ ጉዳዮች መሐንዲስ የሚባሉት በተለይም በሶማሊያ ላይ የሚጠቀሱት እና የቀኝ ክንፍ ተቋም የሆነው ሃድሰን ኢንስቲትዩት ባልደረባው ጆሹዋ መሰርቬይ በበኩላቸው “የሶማሊላንድ ጉዳይ የአሜሪካን ቀልብ የሚይዝ ነው” ይላሉ።
“የእውቅና ጥያቄው በውይይቶች እንደሚነሳ እርግጥ ነው” ሲሉም ያሰረዳሉ።
በትራምፕ የቀድሞ አስተዳደር ወቅት በአፍሪካ ጉዳዮች የቀድሞ ረዳት ፀሐፊ እና በኢትዮጵያ በአምባሳደርነት ያገለገሉት ቲቦር ናዥ እና የአፍሪካ ልዩ መልዕክተኛ ፒተር ፋም የሶማሊላንድን ነጻነት በከፍተኛ ሁኔታ የሚያቀነቅኑ ናቸው።
የሶማሊላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አብዲራህማን ዳሂር አደን በበኩላቸው ከአሜሪካ ጋር ያላቸውን ግንኙነት የሚያዩት ለአገራቸው ከሚሰጠው ጥቅም አንጻር ነው።
“ስምምነቱ ለእኛ ጥሩ ከሆነ እንቀበለዋለን። አሜሪካ እዚህ የጦር ሰፈር ከፈለገች እንሰጣታለን” ብለዋል።
ሚኒስትሩ ከኢትዮጵያ ጋር የተገባውን የባሕር በር መግባቢያ ስምምነት በተመለከተ ለዕውቅና ሲሉ አላስፈላጊ ሁኔታ ውስጥ መግባት እንደማይፈልጉ ተናግረዋል።
“ለዕውቅና ስንል ሁሉንም ነገር እናደርጋለን፤ ነገር ግን ለዕውቅና ሲባል ወደ ሲኦል አናመራም እንዲሁም ሕዝባችንን አናጠፋም። ዕውቅናው የሶማሊላንድን ጥቅም እና የዚያችን አገር [ዕውቅናውን የምትሰጠው አገር] ጥቅም ባጣጠመ መልኩ ሊሆን ይገባዋል” ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል።
የሶማሊላንድ ዕውቅና ማግኘት አለባት የሚሉ አካላት አገሪቷ በምጣኔ ሀብት፣ በወታደራዊ እና በስትራቴጂካዊ አቀማመጧ አሜሪካ የምትፈልገው ነው ሲሉ ይከራከራሉ።
ጆሹዋ መሰርቬይ አክለውም ሶማሊላንድ የዲሞክራሲ መርሆችን በማክበሯ እንዲሁም በውጭ እርዳታ ላይ አለመተማመኗ እንዲሁም መንግሥት ያላት መሆኗ “የሚያስመሰግናት” እንደሆነ ይገልጻሉ።
ሶማሊላንድ ረጅም የባሕር ዳርቻ ያላት ሲሆን፣ ይህም በዓለማችን ላይ በጣም የተጨናነቁ የሟጓጓዣ መስመሮችን ይሸፍናል።
ከሦስት ዓመታት በፊት በጂቡቲ ትልቅ የጦር ሰፈር ላቋቋመችው አሜሪካ በአፍሪካ ቀንድ የጦር ሰፈሮችን ለመያዝ የውጭ አገራት የሚያደርጉት ሸኩቻ ስጋቷ እንደሆነ ይነገራል።
ሩሲያ በሱዳን ወደብ ላይ ዓይኗን የጣለች ሲሆን፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የየመኑን ሁቲን ለመምታት የአሰብን ወደብ ተጠቅማለች።
በጂቡቲ ትልቁን ወደብ የምታስተዳድረው እና የጦር ሰፈርን ጨምሮ ያላትን ቻይናን ጨምሮ የተለያዩ አገራት የጦር ሰፈሮች አላቸው። የቱርክ ከአገሯ ውጪ ያላት ትልቁ የጦር ሰፈር በሶማሊያ፣ ደቡባዊ ሞቃዲሾ ይገኛል።
በአህጉሪቱ ውስጥ ያለው የቻይና ኃያልነት ለትራምፕ ዋነኛ ቅድሚያ የሚሰጡት ጉዳይ ነው።
አሜሪካ በጂቡቲ ባለው የአየር ኃይል ፓይለቶቿ ላይ ዓይናቸው ላይ ሌዘር ጨረር በቀጥታ በማብራት ወደ ሌላ ስፍራ እንዲዛወሩ ጫና በማሳደር ቻይና በእንቅስቃሴዎቼ ላይ ጣልቃ እየገባች ነው ስትል ከሳለች።
አብዛኛውን አፍሪካን የሚሸፍነውን የቻይና ቤልት የመንገድ ጅማሮን አሜሪካ ማደናቀፍ ትፈልጋለች።
ሌላኛው እንደ አማራጭ የሚነሳው የሶማሊላንድ የበርበራ ወደብ ጉዳይ ነው። ቻይና በሶማሊላንድ ጉዳይ ውስጥ የለችም፤ ነገር ግን ታይዋን ከአምስት ዓመታት በፊት ከሶማሊላንድ ጋር ግንኙነት መፍጠሯ አስቆጥቷል።
የአሜሪካ ቁልፍ አጋር የሆነችው የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በቅርቡ የተስፋፋውን ወደብ የምታስዳድር ሲሆን፣ ከጂቡቲ ጋር እንደሚወዳደር ተስፋ ተጥሎበታል።
በባይደን አስተዳደር ወቅት የዩኤስአ አፍሪካ ኮማንድ (አፍሪካ) አዛዥን ጨምሮ ከፍተኛ የአሜሪካ ባለሥልጣናት የበርበራ ወደብን ጎብኝተዋል።
በኋላ ላይ ለአሜሪካ የጠፈር መንኮራኩሮች ድንገተኛ ማረፊያ ተብሎ መለየቱም ተነግሯል።
ከሦስት ዓመታት በፊት የአሜሪካ የመከላከያ ‘አውቶራይዜሽን አክት’ ተብሎ የሚጠራው የፀጥታ ትብብርን በማጎልበት ለጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ እና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት መንገድ ይከፍታል በሚል ሶማሊላንድ እንድትካተት ተሻሸሏል።
የሶማሊላንድ ዕውቅናን የሚደግፉ ሪፐብሊካኖች ትራምፕ ዕውቅና እንዲሰጧት ‘ፕሮጀክት 2025’ በተሰኘው ፍኖተ ካርታ ላይ አቅርበውላቸዋል።
በአሜሪካ ተቀማጭነታቸውን ያደረጉ የሶማሊላንድ ዲፕሎማት “እውቅናውን መስጠትን በተመለከተ ትራምፕን የሚያሳምኑበት ሁኔታ ይወስነዋል። ሆኖም ዕውቅና መስጠቱ አፈንጋጭ ነኝ ለሚሉት ትራምፕ” የሚስማማ አጀንዳ ሊሆን እንደሚችልም ይጠቅሳሉ።
በአውሮፓውያኑ 2018 የአፍሪካ አገራትን በአጸያፊ ስድብ የጠቀሱት ትራምፕ ሕጋዊ ሰነድ የሌላቸውን ሶማሊዎች፣ ጥገኝነታቸው ተቀባይነት ያላገኙ እና ወንጀለኞችን ወደ ሶማሊያ እልካለሁ ማለታቸው ይታወሳል።
በአሁኑ ወቅት የሶማሊላንድ ግዛት የእነዚህ ስደተኞች “መጣያ” እንድትሆን እና በምላሹም አሜሪካ እውቅና እንድትሰጣት ንግግሮች እየተደረጉ መሆናቸው የተነገረ ሲሆን፣ ዋነኛው ጉዳይ ግን ትራምፕ በሶማሊያ እና ሶማሊላንድ የሚከተሉት ፖሊሲ ጉልህ ለውጦች የሚታዩበት ነው ተብሏል።