ከ 5 ሰአት በፊት
የአሜሪካ መንግሥት በሱዳን ጦር መሪ እና የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ተደርገው በሚቆጠሩት ጄነራል አብደል ፈታህ አል ቡርሃን ላይ ማዕቀብ መጣሉን የግምጃ ቤት ሚኒስቴር አስታወቀ።
ለ21 ወራት በዘለቀው ደም አፋሳሹ የሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት ከሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች አንዱ የሆነው ጦሩ መሪ ናቸው ጄነራል አል ቡርሃን።
ጦርነቱ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት ቀጥፏል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በዓለማችን እጅግ የከፋ መፈናቀል ብሎ በጠራው ቀውስ ከ12 ሚሊዮን በላይ ሲፈናቀሉ አገሪቱ በከፋ ረሃብ ላይ ትገኛለች።
ጄነራል አል ቡርሃን “ሱዳንን አለመረጋጋት ውስጥ በመክተት እና የዲሞክራሲ ሽግግርን ቀልብሰዋል” ስትል አሜሪካ በሰጠችው አጭር መግለጫ ከሳለች።
የአሜሪካ ማዕቀብ የተሰማው በቅርቡ በዋድ ማዳኒ በሰላማዊ ዜጎች ላይ ተፈጽሟል የተባለውን ግድያ ተከትሎ ቢሆንም መግለጫው ይህንን ግድያ አልጠቀሰም። ባለፈው ሳምንት ከጦሩ ጋር እየተፋለመ ያለው የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መሪ መሃመድ ሃምዳን ደጋሎ ወይም ሄምቲ በአሜሪካ ማዕቀብ ተጥሎባቸዋል።
አሜሪካ የደጋሎ ፈጥኖ ደራሽ ኃይል በሱዳን ጦርነት የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈጽሟል ሲል ከሷል።
ሐሙስ ዕለት በቡርሃን ላይ የተጣለውን ማዕቀብ አስመልክቶ ይፋ በተደረገበት ወቅት እርሳቸው የሚያዙት ጦር “ትምህርት ቤቶችን፣ ገበያዎች እና ሆስፒታሎችን” ኢላማ አድርጓል እንዲሁም “በሰላማዊ ሰዎች ላይ ግድያን ፈጽሟል” ተብሏል።
- የፋሲል ግንብ እድሳት እንዴት ተካሄደ? የመንጣቱ ምክንያት ምንድን ነው?ከ 6 ሰአት በፊት
- የእስራኤል እና ፍልስጤማውያን ፍጥጫ እና ጦርነት መነሻ ምንድን ነው?ከ 6 ሰአት በፊት
- በጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት ያልተመለሱ ጥያቄዎች16 ጥር 2025
የአሜሪካ መንግሥት በተጨማሪም የአል ቡርሃን ጦር “ሆን ብሎ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦትን በመከልከል እንዲሁም የምግብ እጦትን እንደ ጦር ስልት በመጠቀም ተጠያቂ ነው” ሲል ክስ አቅርቧል።
በግጭቱ የመጀመሪያ አመት ላይ ጦሩ፣ የጦር ወንጀሎችን እንደፈጸመ የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ተናግረዋል።
ቀደም ሲል ጄነራል አል ቡርሃን ወታደሮቻቸው የጌዚራ ግዛት መዲና፣ ዋድ ማዳኒን ተፋላሚያቸውን በማሸነፍ መልሰው ከተቆጣጠሩ በኋላ ሰፊ ጥሰቶችን ፈጽመዋል በሚል በቀረበባቸው ክስ ላይ ምርመራ እንዲካሄድ ትዕዛዝ አስተላልፈው ነበር።
ጦራቸው ዋድ ማዳኒን ከያዘ በኋላ የውጭ ዜጎችን ጨምሮ ሰላማዊ ዜጎች መግደሉን በሰፊው ሪፖርት ከተደረገ በኋላ ነው አል ቡርሃን ምርመራ እንዲደረግ ትዕዛዝ የሰጡት።
ጎረቤት ደቡብ ሱዳን “በንጹሃን ዜጎቻችን ላይ የደረሰውን የሕይወት ጥፋት” እንቃወማለን ስትል ረቡዕ ዕለት በአገሯ የሚገኙ የሱዳን አምባሳደርን ጠርታ አናግራለች።
ከሱዳን መዲና ካርቱም 140 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው ዋድ ማዳኒ ከአንድ ዓመት በፊት በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ቁጥጥር ስር ወድቃ ነበር። ጦሩ ባለፈው ቅዳሜ መልሶ ተቆጣጥሯታል።
ዋድ ማዳኒ በርካታ ግዛቶችን የሚያገናኝ ቁልፍ አውራ ጎዳናዎች ያላት እና በስልታዊ ማዕከላዊ ከተማነቷም ተጠቃሽ ናት።
ጦሩ ጣይባ በተሰኘችው መንደር ቢያንስ 13 ሰላማዊ ሰዎችን እንደገደለ የሱዳን ሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ቡድን አስታውቋል።
በሱዳን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ እርዳታ ኃላፊ ክሌመንት ንክዌታ ሳላሚ በገዚራ በሰላማዊ ሰዎች ላይ “በማንነት ላይ” ተመስርቶ የተፈጸመ የአጸፋ ጥቃት ሪፖርቶች እጅጉን እንዳሳሰቧቸው ተናግረዋል።
በሱዳን የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ቶም ፔሪየሎ በበኩላቸው ሪፖርቱን “ዘግናኝ” በማለት የጠሩት ሲሆን ጦሩ እና አጋር አካላት ጉዳዩን አጣርተው ተጠያቂ አካላትን እንዲያቀርቡ ጥሪ አድርገዋል።
ጄነራሉ በካምፕ ጣይባ ተፈጸመ የተባለውን ግድያ የሚያጣራ ኮሚቴ እንዳቋቁሙና በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ሪፖርት እንዲያደርግ ጠይቀዋል።