ቲክቶክ እንደማይሰራ የሚያሳይ መልዕክት ያለፈው ከስልክ ላይ ፎቶ

ከ 8 ሰአት በፊት

ቲክቶክ እንዲዘጋ የሚያዘው ሕግ ተግባራዊ ከመደረጉ ከሰዓታት በፊት መተግበሪያው አሜሪካ ውስጥ አገልግሎት መስጠት ማቆሙ ታውቋል።

ተጠቃሚዎች ስልካቸውን ሲከፍቱ መተግበሪያው አሜሪካ ውስጥ ጥቅም ላይ እንዳይውል በመታገዱ ምክንያት “ለጊዜው ቲክቶክን መጠቀም አትችሉም” የሚል መልዕክት ያሳያል።

አክሎ “ፕሬዝደንት ትራምፕ ሥልጣን ሲይዙ ከእኛ ጋር በመሥራት ቲክቶክ ድጋሚ ክፍት እንዲሆን መጠቆማቸው ዕድለኛ ያደርገናል” ሲል ይነበባል።

ኩባንያው የፕሬዝደንት ዳይደን አስተዳደር ቲክቶክ እንደማይታገድ ማስረገጫ ካልሰጡ ከእሑድ ጀምሮ አገልግሎት መስጠት እንደሚያቆም አስጠንቅቆ ነበር።

ተመራጩ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ከዚህ ቀደም ሰኞ ሥልጣን ከያዙ በኋላ ለቲክቶክ የ90 ቀናት የእፎይታ ጊዜ እንደሚሰጡት ተናግረው ነበር።

ትራምፕ ቅዳሜ ኤንቢሲ ኒውስ ለተሰኘው ጣቢያ “የ90 ቀናት ማራዘሚያው መካሄዱ የሚቀር አይደለም፤ ምክንያቱም ትክክለኛው እምጃ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

“ይህን ለማድረግ ከወሰንሰኩ ሰኞ ዕለት የማደርገው ይሆናል።”

ዋይት ሐውስ በሰጠው መግለጫ የቲክቶክ ዕጣ ፈንታ በመጪው አስተዳደር እርምጃ ላይ የሚወሰን ነው ብሏል።

የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት አርብ ዕለት ቲክቶክ ያቀረበውን ይግባኝ ውድቅ በማድረግ ባለፈው ሚያዚያ የፀደቀው ሕግ እንዲፀና ወስኗል።

ተጠቃሚዎች እንደሚሉት ቲክቶክ ከአፕል እና ጉግል መተግበሪያ ማውረጃ ቋቶች እንደተወገደ ተመልክተዋል።

በተጨማሪም መተግበሪያው ቪድዮ ማሳየት አቁሟል።

ባለፈው የአውሮፓውያኑ ዓመት ነው የአሜሪካ ሕግ አውጭዎች ቲክቶክ ከቻይና መንግሥት ጋር ግንኙነት ስላለው መታገድ አለበት ሲሉ አዋጅ ያፀደቁት።

ቲክቶክ በተደጋጋሚ በሰጠው ቃል ለቤይዢንግ አስተዳደር መረጃ አሳልፎ እንደማይሰጥ አስታውቋል።

ባለፈው ዓመት ሚያዚያ የፀደቀው ሕግ እንደሚለው መቀመጫውን ቻይና ያደረገው ባይትዳንስ የአሜሪካውን ቲክቶክ መሸጥ አለበት ካልሆነ ግን አሜሪካ ውስጥ ይታገዳል።

ቲክቶክ ይህ ሕግ የንግግር ነፃነትን የሚጥስ ነው በማለት ተከተራክሯል።

ቲክቶክ አሜሪካ ውስጥ 170 ሚሊዮን ተጠቃሚዎች አሉት።

መተግበሪያው ከመታገዱ ከጥቂት ሰዓታት በፊት አሜሪካ የሚገኙ ታዋቂ የቲክቶክ ተጠቃሚዎች ለተከታዮቻቸው የስንብት መልዕክት በቪድዮ ቀርፀው ለጥፈዋል።

የቲክቶክ ‘ኮንቴንት ክሬተር’ የሆነችው ኒኮል ብሎምጋርደን ቲክቶክ መታገዱ ትልቅ የደመወዝ ቅነሳ ያስከትላል ስትል ለቢቢሲ ትናገራለች።

ሌላኛዋ ተጠቃሚ ኤሪካ ቶምፕሰን ደግሞ በቲክቶክ የሚለቀቂ ትምህርታዊ ይዘቶች መታገዳቸው ለማኅበረሰቡ “ትልቅ ኪሳራ” ነው ትላለች።