
Saturday, 18 January 2025 21:58
Written by Administrator
• በሰላም ስም የሚደረጉ ሸፍጦች ይቁሙ ተባለ
በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል፣ መተከል ዞን፣ ግልገል በለስ ከተማ የሚገኝ አንድ ኬላ ለዜጎች ሞት ምክንያት መሆኑ ተገለፀ። ከግድያ በተጨማሪ፣ በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች የዕገታ ተግባር እንደሚፈጽሙ ተነግሯል።
ከግልገል በለስ ከተማ በቅርብ ርቀት በሚገኘውና “ቻይና ካምፕ” ተብሎ በሚጠራው ኬላ ላይ በርካታ ዜጎች በማንነታቸው እየተለዩ መገደላቸውን እናት ፓርቲ ባለፈው ሰኞ ጥር 5 ቀን 2017 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። የአካባቢው ነዋሪዎች በተደጋጋሚ “የኬላው መኖር ምክንያታዊ ያልሆነና አላስፈላጊ ነው” የሚል ቅሬታ ሲያቀርቡ ቢቆዩም፣ ሰሚ ሊያገኙ አለመቻላቸውን ፓርቲው በመግለጫው ላይ አመልክቷል።
ኬላው ላይ ተሽከርካሪዎችን በማስቆም ታጣቂዎቹ ተሳፋሪዎችን በማንነት እየለዩ እንደሚሰውሩ፣ እንዲሁም በአሰቃቂ ሁኔታ እንደሚገድሉ ነዋሪዎች መናገራቸውን ፓርቲው የጠቀሰ ሲሆን፣ ነዋሪዎች “በአጠቃላይ የግልገል በለሱ “ቻይና ካምፕ” ኬላ የዜጎች ድብቅ ግድያ ‘ማመቻቻ ነው’ ብሎ መደምደም ይቻላል” ማለታቸውንም አክሎ አትቷል።
ታህሳስ 24 ቀን 2017 ዓ.ም. ከቀኑ ስድስት ሰዓት አካባቢ ወደ ግልገል በለስ ከተማ ይገባ የነበረውን የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ ቻይና ካምፕ ኬላ ላይ ታጣቂዎቹ አስቁመው ለስራ ይጓዝ የነበረን አንድ ወጣት “የዓይንህ ቀለም አላማረንም” በሚል ምክንያት ከቆመው ተሽከርካሪ አስወርደው “በአሰቃቂ ሁኔታ” መግደላችውን እናት ፓርቲ ገልጿል። የተፈጸመውን ግድያ የተመለከቱ ተሳፋሪዎች በከተማው ውስጥ ለሚገኘው መከላከያ ሰራዊት ስለሁኔታው ቢያስታውቁም፣ “ትዕዛዝ አልተሰጠንም” በሚል እርምጃ ከመውሰድ መታቀባቸውን የጠቆመው ፓርቲው፣ “’ቻይና ካምፕ’ እና ‘ኪዳነምሕረት ሰፈር’ በተባሉ አካባቢዎች ተገቢ ማጣራት ቢደረግ፣ ሌሎች የግድያ መረጃዎች ይገኛሉ። ነገር ግን መሰል ድርጊቶች እንዳይጋለጡ ከፍተኛ ርብርብና ማድበስበስ አለ” በማለት አስረድቷል።
ይህንን የግድያ ድርጊት “ፈጽመዋል” የተባሉት ታጣቂዎች ከዚህ ቀደም ጫካ ውስጥ ሲንቀሳቀሱ እንደ ነበሩና ከክልሉ መንግስት ጋር ዕርቅ ማውረዳቸውን እናት ፓርቲ ጠቅሶ፣ እነዚሁ ታጣቂዎች ከ”ቻይና ካምፕ” ኬላ አካባቢ ወታደራዊ ካምፕ ተሰጥቷቸው ሰፍረው እንደሚገኙ አብራርቷል። በተጨማሪም ፓርቲው “በሰላም ስም ቡድኖችን እየቀለቡ ማንነት ተኮር ጭፍጨፋና እገታ ይፈጽማሉ” በማለት በክልሉ መንግስት አካላት ላይ ነቀፌታውን አሰምቷል።
“በሰላም ስም የሚደረጉ ሸፍጦች ይቁሙ” ሲል ጥሪ ያቀረበው እናት ፓርቲ፣ የድርጊቱ ፈፃሚዎች ለሕግ እንዲቀርቡ ጠይቋል። ፓርቲው አያይዞም፣ የግልገል በለስ ከተማ ነዋሪዎችን “ለከባድ ሰቆቃ እየዳረገ ነው” ሲል የጠቀሰውን ቻይና ካምፕ ኬላ “ሕዝቡን በማወያየት” በአስቸኳይ እንዲነሳ ተማጽኗል።
ተጨማሪ ድብቅ መቃብሮች “አሉባቸው” ተብለው በአካባቢው ነዋሪዎች የሚጠረጠሩ እንደ ”ቻይና ካምፕ” እና “ኪዳነምሕረት ሰፈር” ዓይነት ስፍራዎች በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንና መሰል ተቋማት ምርመራ ተደርጎባቸው ውጤቱ ለሕዝብ ይፋ እንዲሆን እናት ፓርቲ አሳስቧል። እንዲሁም “አንዳንድ የመንግስት ባለስልጣናት ያላቸው ሚና የምርመራው አካል እንዲሆን እንጠይቃለን።” ብሏል፣ ፓርቲው በመግለጫው።